ዋልያዎቹ አንድ ተጫዋች ቀንሰው ነገ ጠዋት ወደ ደቡብ አፍሪካ ያመራሉ

ከሰዓታት በፊት በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከደቡብ አፍሪካ ጋር የተጫወተው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ማክሰኞ ለሚደረገው ጨዋታ ነገ ጠዋት ወደ ስፍራው ያመራል።

በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ኳታር ለምታስተናግደው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የምድብ ጨዋታዎችን እያደረገ እንደሆነ ይታወቃል። ቡድኑም ዛሬ 10 ሰዓት በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የደቡብ አፍሪካ አቻውን በምድብ ሦስተኛ ጨዋታ አስተናግዶ 3-1 ተረቷል። ቀጣዩን የምድብ አራተኛ ጨዋታውን ከደቡብ አፍሪካ ጋር ከሦስት ቀናት በኋላ (ማክሰኞ) የሚያደርገው ቡድኑም ነገ ጠዋት 2 ሰዓት ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚያቀና ይሆናል።

ለነገ ጠዋቱ ጉዞ ቡድኑ በአሁኑ ሰዓት ከባህር ዳር ወደ አዲስ አበባ ባለው የዕለቱ የመጨረሻ በረራ ወደ መዲናው ጉዞ እያደረገ ሲሆን አዳሩንም በጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል ያደርጋል። ከዛም ጠዋት 2 ሰዓት ወደ ደቡብ አፍሪካ በረራውን የሚያደርግ ይሆናል።

ከቡድኑ ጋር በተያያዘ ታፈሠ ሰለሞንን ተክቶ ስብስቡን ተቀላቅሎ የነበረው በዛብህ መለዮ ወደ ደቡብ አፍሪካ ከሚያመራው ልዑክ ውጪ እንደሆነ ታውቋል። ከበዛብህ ውጪ የሚገኙት 23 ተጫዋቾች እንዲሁም የአሠልጣኝ ቡድን አባላት በአጠቃላይ 35 ልዑካን ቡድን ወደ ደቡብ አፍሪካ እንደሚያቀናም ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

 

ያጋሩ