15ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ላይ ባህር ዳር ከተማ መከላከያን ረቶ የዋንጫ ባለቤት ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ በመለያ ምት ጅማ አባጅፋርን አሸንፎ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
ጅማ አባጅፋር 2-2 ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-5)
ለደረጃ የተደረገው የጅማ አባጅፋር እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ መመጣጠን የታየበት ፍልሚያ ሲያስተናግድ ነበር። ጨዋታው ገና ሩብ ሰዓት ሳያስተናግድ ደግሞ መሪ አግኝቷል። በዚህም በ12ኛው ደቂቃ ቤካም አብደላ ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች በሚገባ ማፅዳት ተስኗቸው ያገኘውን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮት ጅማን መሪ አድርጓል።
በአንፃራዊነት ግብ ካስተናገዱ በኋላ በተሻለ ለመንቀሳቀስ የሞከሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተከታታይ ሙከራዎችን ማድረግ ይዘዋል። በቅድሚያም በ20ኛው ደቂቃ አላዛር ከመዓዘን ምት መነሻን ያደረገ ኳስ ከሳጥኑ ጫፍ ተቀብሎ አንድ ተከላካይ በማለፍ ወደ ግብ የመታው ኳስ ዒላማውን ስቶ ወደ ውጪ ወጥቶበታል። በቀጣይ ግን ቡድኑ አቻ የሆነበትን ጎል አግኝቷል። በዚህም በ27ኛው ደቂቃ የቡድኑ አዲሱ ፈራሚ በረከት ወልዴ ከወደ ቀኝ ባደላ ቦታ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ በድንቅ ሁኔታ መረብ ላይ አርፏል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ምስጋናው መላኩ ከግብ ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ የተገናኘበትን ኳስ ለመጠቀም ጥሮ ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል ለማግኘት ቢሞክርም ታምራት ዳኜ በጥሩ ቅልጥፍና አምክኖበታል።
አሁንም ጫና መፍጠራቸውን የቀጠሉት ጊዮርጊሶች በግራ መስመር ወደ ጅማ ግብ በመሄድ በዳግማዊ አርዓያ አማካኝነት ሌላ ጥቃት ሰንዝረው ተመልሰዋል። ነገርግን መሪ ሆነው አጋማሹን ማገባደድ ሳይችሉ ቀርተዋል። ጅማዎች በበኩላቸው እንደ አጀማመራቸው መዝለቅ ተስኗቸው የመጀመሪያውን አጋማሽ አገባደዋል።
በአንፃራዊነት እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ጅማሮ ተጭነው መጫወት የጀመሩት ጅማዎች በ53ኛው ደቂቃ ያገኙትን የቅጣት ምት በኢዳላሚን ናስር አማካኝነት ለመጠቀም ጥረው መክኖባቸዋል። ከዘጠኝ ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ መሐመድኑር ናስር ጥፋት ተሰርቶበት የተገኘን የቅጣት ምት የግራ መስመር ተከላካዩ አስናቀ ሞገስ መሬት ለመሬት ወደ ግብ በመምታት ግብ አስቆጥሯል።
ግብ ካስተናገዱ በኋላ ዳግም አቻ ለመሆን መታተር የቀጠሉት ጊዮርጊሶች በዳግማዊ እና ፀጋዬ አማካኝነት አደገኛ ዕድሎችን ፈጥረው ነበር። በተለይ 64ኛው ደቂቃ ላይ ፀጋዬ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ሳጥን ውስጥ ይዞ የገባውን ኳስ እጅግ ዘግይቶ ለአጋሩ በማቀበል አመከነው እንጂ ያለቀለት አጋጣሚ ነበር ያገኘው። ግብ ካገኙ በኋላ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ጋብ አድርገው መጫወት የቀጠሉት ጅማዎች በ72ኛው ደቂቃ በቀይሮ በገባው በላይ አባይነህ የቅጣት ምት መሪነታቸውን ከፍ ሊያደርጉ ነበር።
ጨዋታው 78ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ደግሞ ጊዮርጊሶች በቁጥር በዝተው ወደ ጅማ የግብ ክልል በማምራት አቻ ሆነዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም ምስጋናው ሳጥን ውስጥ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ ሲመታው ቋሚው ሲመልስ በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ፀጋዬ አግኝቶት ግብ አድርጎታል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ በተጨመረው ደቂቃ ደግሞ የጊዮርጊሱ አጥቂ ምስጋናው የጨዋታውን የመጨረሻ ያለቀለት ሙከራ አስመልክቶ ጨዋታው ተጠናቋል።
አሸናፊውን ለመለየት በተሰጠው የመለያ የፍፁም ቅጣት ምት አስራ አራት ምቶች ተመተዋል። ከተመቱት መለያዎች አድናን ረሻድ፣ ተስፋዬ መላኩ እና እዮብ አለማየሁ በጅማ በኩል በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ደግሞ አማኑኤል ተረፉ እና ዳግማዊ አርዓያ አምክነዋል። ይህ ቢሆንም ፈረሰኞቹ 5-4 አሸንፈው ሦስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል። የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ደግሞ በረከት ወልዴ ተሸልሟል።
ባህር ዳር ከተማ 1-0 መከላከያ
ጥሩ የሜዳ ላይ ፉክክር ማስመልከት የጀመረው የባህር ዳር እና መከላከያ ጨዋታ በ12ኛው ደቂቃ ጥሩ የግብ ማግባት ሙከራ ማስተናገድ ይዟል። በዚህ ደቂቃም በጥሩ ቅብብል መከላከያ የግብ ክልል የደረሱት ባህር ዳሮች ግርማ ዲሳሳ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመታው ኳስ ቀዳሚ ሊሆኑ ነበር። በጥሩ የቡድን ስራ አጥቅተው የሚመለሱት መከላከያዎች ደግሞ ከደቂቃ በኋላ በኦኩቱ ኢማኑኤል አማካኝነት ሌላ ጥቃት አስመልክትዋል።
በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ደቂቃ በደቂቃ እድገት እያሳዩ የመጡት ባህር ዳር ከተማዎች በ27ኛው ደቂቃ በቅጣት ምት ፍፁም ዓለሙ ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦ ነበር። በመልሶ ማጥቃት አደገኛ ኳሶችን ወደ ግብ ማድረስ የቀጠሉት የአሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ተጫዋቾች በ29ኛው ደቂቃ ሰመረ ሐፍታይ በግራ መስመር እየገፋ ሄዶ በሞከረው ኳስ ግብ ሊያገኙ ነበር። ለዚህ ጥቃት ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ያሰቡ የሚመስሉት ባህር ዳሮች የግራ መስመር ተከላካዩ አህመድ ረሺድ በሞከረው የሰላ ኳስ ክሌመንት ቦዬን ፈትነዋል።
ለዐይን ሳቢ የሆነው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አሁንም ጥሩ ጥሩ የግብ እድሎችን ማስመልከት ቀጥሏል። በ37ኛው ደቂቃም ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ኤርሚያስ ከሳጥኑ ጫፍ ሆኖ ለጠበቀው ላርዬ ኢማኑኤል አመቻችቶት ላርዬ አክርሮ የመታውን ኳስ ተከላካዮች ተረባርበው አወጡት እንጂ ለግብ የቀረበ አጋጣሚ ነበር። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ግን መሪ አልባው የፍፃሜ ጨዋታ ግብ አስተናግዷል። በተጠቀሰው ደቂቃም ተመስገን ደረሰ መሐል ለመሐል የደረሰውን የመሬት ለመሬት ኳስ ተከላካይ አታሎ በማለፍ መረብ ላይ አሳርፎታል። አጋማሹም በጣና ሞገዶቹ መሪነት ተጠናቋል።
አጋማሹን በጥሩ ተነሳሽነት የጀመሩት መከላከያዎች በ49ኛው ደቂቃ የሰላ ጥቃት ፈፅመው አቻ ለመሆን ተቃርበው ነበር። በ61ኛው ደቂቃ ደግሞ ባህር ዳር ከተማዎች የመከላከያ ተጫዋቾችን ስህተት ተጠቅመው ወደ ፊት በመሄድ በግርማ ዲሳሳ አማካኝነት ሙከራ አድርገዋል።
ድንቅ ፉክክር ማስመልከት የቀጠለው ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ ብዙም የግብ ሙከራዎች ባይመለከቱበትም ቶሎ ቶሎ ኳስ መነጣጠቆች እና እልህ አስጨራሽ የመሐል ሜዳ ፍትጊያዎች ነበሩበት። በ71ኛው ደቂቃ ግን ግርማ ዲሳሳ የአጋማሹን ለግብ የቀረበ ጥቃት ፈፅሞ ተመልሷል።ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ተቀይሮ የገባው አብዱልከሪም ንኪማ የግብ ጠባቂውን መውጣት ተከትሎ ከመሐል ሜዳ ረጅም ኳስ መትቶ ነበር። የጨዋታው መገባደጃ ላይ አቻ ለመሆን የጣሩት ጦሮቹ በ86ኛው ደቂቃ ሰመረ ከግራ የሳጥኑ ክፍል በመታው ኳስ የመጨረሻ ዕድላቸውን ሞክረዋል።
የፍፃሜ ጨዋታው ኮከብ ሆኖ የተመረጠው አለልኝ አዘነ ደግሞ የኮከብነቱን ሽልማት ተረክቧል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ባህር ዳር ከተማ የውድድሩ አሸናፊ በመሆኑ ዋንጫ እና የወርቅ ሜዳሊያውን ሲረከብ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ሆነው ያጠናቀቁት መከላከያ እና ቅዱስ ጊዮርጊሶች የብር እና የነሀስ ሜዳሊያ ተበርክቶላቸዋል። የውድድሩ የፀባይ ዋንጫ ተሸላሚ ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆኖ በመመረጥ ልዩውን ዋንጫ ተረክቧል።