የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ በሰበታ ከተማ አሸናፊ ተጠናቋል

ለአስራ ስድስት ቀናት በአምስት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች መካከል ሲደረግ የነበረው የመጀመሪያው የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ በደማቅ ስነ ስርአት ሰበታ ከተማን አሸናፊ በማድረግ ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡

በሲዳማ ክልል እግር ኳስ ፌድሬሽን አዘጋጅነት በጎፈሬ የትጥቅ አምራች ተቋም ስፖንሰር አድራጊነት ለመጀመሪያ ጊዜ በአምስት የሊጉ ክለቦች መካከል በሀዋሳ ከተማ ለአስራ ስድስት ቀናት ሲደረግ የነበረው የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ በደመቀ የመዝጊያ ስነ ስርአት በዛሬው ዕለት ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡

ሀድያ ሆሳዕና 0-0 ሲዳማ ቡና

ዛሬ ውድድሩ ፍፃሜውን ሲያገኝ ቀደም ብሎ 7፡00 ላይ ከመጨረሻው ጨዋታ ቀደም ብሎ በሲዳማ ቡና እና ሀድያ ሆሳዕና መካከል ጨዋታ ተከናውኗል፡፡ ተመጣጣኝ እና ጠንከር ያለ የሜዳ ላይ ፉክክርን ባስተዋልንበት የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ግቦችን አንመልከትበት እንጂ በሜዳ ላይ የነበረው ማራኪ የጨዋታ ፍሰት ሳቢ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ 10ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬው ሰለሞን ከርቀት መቶ ግርማ በቀለ በግንባር በቅፅበት ገጭቶ መሳይ አያኖ በሚገርም ብቃት ያዳናት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራም ነበረች፡፡ 29ኛው ደቂቃ በሀድያ ሆሳዕና በኩል ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ በረጅሙ የላካት ኳስ በቶሎ ባዬ ገዛኸኝ ተቆጣጥሯት አክርሮ ወደ ግብ ሲመታ ፍቅሩ ወዴሳ ያዳናት ኳስ በዚህኛው አጋማሽ የተመለከትናቸው ጠንካራዎቹ ሙከራዎች ናቸው፡፡


ልክ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ጠንከር ያለ በቅብብሎሽ የታጀበን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን በደንብ ማስተዋል በቻልንበት ሁለተኛው አጋማሽ 50ኛው ደቂቃ ላይ የሀድያ ሆሳዕናው አማካይ አበባየው ዮሐንስ ከርቀት በሞከራት እና ፍቅሩ ወዴሳ ባዳናት አጋጣሚ ሀድያ ሆሳዕና ቀዳሚዎቹ የግብ አጋጣሚ ፈጣሪዎች መሆን ችለዋል፡፡ የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ ሲመጣ ሲዳማ ቡና የጨዋታውን የሀይል ሚዛን ወደራሳቸው መውሰድ ጀምረዋል፡፡ በተለይ 62ኛው ደቂቃ መሀሪ መና ከመስመር አሻምቶ ይገዙ ቦጋለ በግንባር ገጭቶ ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣችበት እና በተደጋጋሚ ይገዙ ቦጋለ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶች ቢያደርጉም ያለ ግብ ጨዋታው ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡

ከጨዋታው ፍፃሜ በኋላ የሀድያ ሆሳዕናው ግብ ጠባቂ መሳይ አያኖ የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ተሸልሟል።

ሰበታ ከተማ 0-1 ሀዋሳ ከተማ

በመቀጠል 9፡00 ላይ ቀደም ብሎ የውድድሩ ቻምፒዮን መሆኑን ባረጋገጠው ሰበታ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ መካከል የተካሄደ ነበር፡፡ ጨዋታው ከመጀመሩ ቀደም ብሎ በክብር እንግድነት በርከት ያሉ አካላት ተገኝተው አስጀምረውታል፡፡ አቶ ኢሳያስ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ሳሙኤል መኮንን የጎፈሬ ትጥቅ አምራች ተቋም ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጃጎ አገኘሁ የሲዳማ ክልል ባህል እና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ፍሬው አሬራ የሲዳማ ስፖርት ኮሚሽነር አቶ ብርሀኑ በቀለ የሰበታ ከተማ ከንቲባ እና የክለቡ የቦርድ ፕሬዝዳንት አቶ ፍሮሞሳ ለገሰ የኦሮሚያ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት እንዲሁም አቶ አንበሴ አበበ የሲዳማ እግር ኳስ ፌድሬሽን ም/ፕሬዝዳንት እና ሌሎች ጥሪ የቀረበላቸው በርካታ እንግዶች ተገኝተው አስጀምረውታል፡፡ የመጀመሪያው የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ የዋንጫ አሸናፊ መሆኑን ያረጋገጠው ሰበታ ከተማ በመጨረሻ ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ ሽንፈትን አስተናግዷል፡፡

ፈጣን በሚመስል ተቀራራቢ የጨወታ ሂደት ጅምሩን ያደረገው እና በሂደት የሀዋሳ ከተማ የተሻለ የግብ ሙከራን በጉልህ ማስተዋል የቻልንበት የመጀመሪያው አጋማሽ ሰበታ ከተማዎች በጂኒያስ ናንጄቤ አማካኝነት ባደረጋት ሙከራ እና ዳግም ተፈራ በቅልጥፍና በመለሰበት ሙከራ ቀዳሚዎች ዕድል ፈጣሪዎች ሆነዋል፡፡ 20ኛው ደቂቃ ላይ ላይ ዳንኤል ደርቤ በቀኝ በኩል በረጅሙ አሻምቶ ተባረክ ኢፋሞ በግንባር ገጭቶ የወጣበት እና 32ኛው ደቂቃ ላይ ዮሐንስ ሱጌቦ ከመስመር በተመሳሳይ ወደ ግብ አሻምቶ መድሀኔ ብርሀኔ በግንባር ገጭቶ ሀይለሚካኤል አደፍርስ ያወጣበት ኳስ ሀዋሳዎች በግብ ሙከራ ብልጫ መውሰዳቸውን ያመላክታል፡፡

ከእረፍት መልስ ጎል ማስቆጠርን በደንብ የፈለጉ የሚመስሉት ሀዋሳ ከተማዎች ብሩክ ኤልያስን ወደ ሜዳ ቀይረው ካስገቡ በኋላ በሌላኛው ብሩክ በየነ እና መድሀኔ ብርሀኔ እንዲሁን በመሀል ሜዳ ተጫዋቹ በቃሉ ገነነ ድንቅ ጥምረት ጎል በጊዜ በዚህኛው አጋማሽ አግኝተዋል፡፡ብሩክ በየነ የሰጠውን ድንቅ ኳስ 49ነኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ብሩክ በየነ አራት የሰበታ ተጫዋቾች አልፎ ድንቅ ጎል ከመረብ አሳርፎ ሀዋሳን መሪ አድርጓል፡፡ከጎሉ መቆጠር በኋላ ቡድኖቹ በሜዳ ላይ ጥሩ ቆይታን ቢፈጥሩም ተጨማሪ ጎል ሳንመለከት ጨዋታው ተጠናቋል፡፡


ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የዚህ ጨዋታ ምርጥ ተብሎ ፀጋሰው ድማሙ ከሀዋሳ ከተማ ተመርጧል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ደመቅ ያለ የሽልማት ስነ ስርአት ተከናውኗል፡፡ በውድድሩ አስተዋጽኦ ላደረጉ ተቋማት ፥ ግለሰቦች እና የሚዲያ አጋር ለሆነችው ሶከር ኢትዮጵያም የማስታወሻ ሽልማቶች ተበርክተዋል፡፡

በመቀጠል ለተሳታፊ ክለቦች በጎፈሬ ትጥቅ አምራች እና በሲዳማ እግር ኳስ ፌድሬሽን የተዘጋጀላቸውን ስጦታ የተበረከተ ሲሆን ኮከብ ተጫዋች – በኃይሉ ግርማ (ሰበታ ከተማ) ፣ ከፍተኛ ግብ አግቢ – ጂኒያንስ ናንጄቦ (ከሰበታ ከተማ 3 ጎል)፣ ኮከብ ግብ ጠባቂ – መሳይ አያኖ (ከሀድያ ሆሳዕና) ፣ ኮከብ አሰልጣኝ – ዘላለም ሽፈራው (ሰበታ ከተማ) ፣ የስፖርታዊ ጨዋነት ዋንጫ ተሸላሚ (ሀድያ ሆሳዕና) በመሆን የተዘጋጀላቸውን ሽልማት የወሰዱ ሲሆን የፍጻሜ ጨዋታውን ለመሩ ዳኞች እና ሌሎች በርካታ አካላት ሶስተኛ በመሆን ያጠናቀቀው ሲዳማ ቡና የነሀስ ሁለተኛ ሆኖ ለፈፀመው ሀዋሳ ከተማ የብር እና ለውድድሩ አሸናፊ ሰበታ ከተማ የዋንጫ እና የወርቅ ሜዳሊያ ሽልማት ከተበረከተ በኋላ ውድድሩ ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡

ያጋሩ