ከ2 ዓመታት በኋላ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተመለሰው መከላከያ ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ ያሳደጉትን የቡድን አባላት ነገ እውቅና ይሰጣል።
በ2013 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ አንድ ተደልድሎ ውድድር ሲያደርግ የነበረው መከላከያ በ16 ጨዋታዎች በሰበሰባቸው 38 ነጥቦች የምድቡ አንደኛ ሆኖ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ማለፉ ይታወቃል። በአሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የሚመራው ክለቡም ለሊጉ ውድድር ዝግጅቱን እያከናወነ ሲሆን በነገው ዕለትም በክለቡ አመራሮች ሽልማት ሊበረከትለት እንደሆነ ታውቋል።
በአሁኑ ሰዓት ባህር ዳር የሚገኙት የቡድኑ አባላትም (የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ለማድረግ) ነገ ጠዋት ወደ መዲናችን በመጓዝ ማረፊያቸውን በራስ ሆቴል የሚያደርጉ ይሆናል። የክለቡ አመራሮች ባዘጋጁት ዝግጅት መሰረትም እዛው ስብስቡ ባረፈበት ራስ ሆቴል ምሽት ላይ ወደ ሀገሪቱ ከፍተኛ የሊግ እርከን ያሳደጉትን ተጫዋቾች እና የአሠልጣኝ ቡድን አባላት እውቅና በመስጠት ሽልማት እንደሚያበረክት ተጠቁሟል።