የዩጋንዳ እግርኳስ ማኅበር ቀጣዩን የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ሻምፒዮናን እንደሚያስተናግድ የተረጋገጠ ሲሆን ኢትዮጵያም በውድድሩ ትካፈላለች ተብሏል።
ከመካከለኛው እና ምስራቅ አፍሪካ የተወጣጡ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሄራዊ ቡድኖችን የሚያሳትፈው የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ሻምፒዮና ዩጋንዳ እንደሚደረግ ከዚህ በፊት ተገልፆ የነበረ ሲሆን የዩጋንዳ እግር ኳስ ማኅበር ጽ/ቤት ባካሄደው የመጨረሻው የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ውድድሩን እንደሚያስተናግድ ማረጋገጫ ሰጥቷል። ከዚህ ቀደም ነሐሴ አጋማሽ ላይ ይደረጋል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ወዳልተገለፀ ቀን ተራዝሟል። አሁንም ውድድሩ እንደሚካሄድ ከመገለፁ ውጪ ቀኑ አልተጠቀሰም።
ይህ ውድድር ለመጨረሻ ጊዜ የተስተናገደው በ2019 ሲሆን በወቅቱም ዩጋንዳ አሰናድታ ታንዛኒያ ኬንያን በፍጻሜ አሸንፋ ዋንጫ ከፍ ማድረጓ አይዘነጋም።
በዚህ ውድድር ላይ በአሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የሚመራው እና ኮስታሪካ ለምታስተናግደው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በማጣርያ ውድድሩ ሦስተኛ ዙር ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የሚሳተፍ ሲሆን ከቀናት በኋላም ለተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ወደ ዝግጅት እንደሚገባ ለማወቅ ተችሏል።