ሎዛ አበራ ውሏን አድሳለች

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ወሳኝ አጥቂ የሆነችው ሎዛ አበራ ከክለቡ ጋር ያላትን ቆይታ ማራዘሟን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

የክለብ እግርኳስ ህይወቷን በሀዋሳ ከተማ የጀመረችው ሎዛ አበራ 2007 ላይ ወደ ደደቢት በመጓዝ ከበርካታ የእግርኳስ ቤተሰቦች ጋር መተዋወቋ አይዘነጋም። በተለይ በክለቡ በቆየችባቸው አራት ዓመታት የሊጉን ዋንጫ ለ3 ተከታታይ ጊዜያት በማግኘት፣ 4 ጊዜ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ እና 1 ጊዜ የሊጉ ኮከብ ተጫዋች በመሆን የእግርኳስ ህይወቷን በጥሩ መንገድ አስቀጠላለች። ከዛም ከሀገር በመውጣት በሲውድኑን ክለብ ንግስባካ ለግማሽ ዓመት ግልጋሎት ከሰጠች በኋላ ዳግም ወደ ሃገሯ በመመለስ አዳማ ከተማን በግማሽ ዓመት ውል ተቀላቅላ የሊጉን ዋንጫ በድጋሜ ከፍ አድርጋለች። በመቀጠል ደግሞ ወደ ማልታው ክለብ ቢርኪርካራ በማምራት የቡድን እና የግል ስኬቶችን አግኝታ ወደ ሀገሯ መመለሷ ይታወሳል።

ዓምና በአሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራውን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተቀላቅለ በሀገሯ መጫወት የቀጠለችው ተጫዋቿ የአንድ ዓመት ውሏ መጠናቀቁን ተከትሎ ቀጣይ ማረፊያዋ ሲጠበቅ ቢቆይም ተጫዋቿ ከባንክ ጋር ያላትን ውል ለተጨማሪ ዓመት ማራዘሟን ድረ-ገፃችን ተረድታለች።

ከዓመት በፊት በደማቅ ስነ-ስርዓት ከባንክ ጋር የተቀላቀለችው ተጫዋቿ ለክለቡ ዋንጫ አስገኛለው ባለችው መሠረት ቃሏን መጠበቋ አይዘነጋም። ከዚህ በተጨማሪም በ17 ጎሎች የ2013 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆና ያጠናቀቀች ሲሆን በሴካፋ የአፍሪካ ሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ የማጣሪያ ውድድር ላይም ድንቅ ብቃቷን ማሳየቷ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። አሁን ደግሞ ከክለቡ ጋር ለተጨማሪ ሁለት ዓመት ለመቆየት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ቢሮ በመገኘት መፈረሟ ታውቋል