የአህጉሪቱ ትልቁ ዋንጫ የሆነው የአፍሪካ ዋንጫ በቶታል ኢነርጂስ አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ለእይታ ቀርቧል።
በ1957 መደረግ የጀመረው የአፍሪካ ዋንጫ ከወራት በኋላ 33ኛውን ውድድር በካሜሩን አስተናጋጅነት እንደሚያደርግ ይታወቃል። በውድድሩ የሚሳተፉ 24 ሀገራትም ከወራቶች በፊት ተለይተው መታወቃቸው አይዘነጋም። በዚህ ውድድር ላይ ተሳታፊ የሆነችው ኢትዮጵያም ውዱ ዋንጫ ለእይታ ከሚዞርባቸው 18 ሀገሮራች መካከል አንዷ መሆኗን ከቀናት በፊት ድረ-ገፃች ዘግባ ነበር። ይህንን ተከትሎም ዋንጫው በዛሬው ዕለት ሀገራችን በመግባት በይፋ ለእይታ ቀርቧል።
ላለፉት 70 ዓመታት በሀገራችን ሲሰራ የቆየው ቶታል ኢነርጂስ ከአፍሪካ የእግርኳስ የበላይ አካል ካፍ ጋርም የስራ ግንኙነት ከፈጠረ ሰነባብቷል። ይኸው ተቋም የቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ ከመጀመሩ ከሦስት ወራት በፊት ዋንጫውን ወደ ሀገራችን በማምጣት ዛሬ ከሰዓት በተቋሙ ዋና መስሪያ ቤት ጥሪ ለተደረገላቸው እንግዶች እና የብዙሃን መገናኛ አባላት ለእይታ አብቅቷል።
የቶታል ኢነርጂስ የኢትዮጵያ ማርኬቲንግ ማናጀር አን ሶፊያ፣ የተቋሙ የብራንድ አምባሳደር ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ እና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ም/ዋና ፀሐፊ አቶ ሰለሞን ገብረሥላሴ ከ8:30 ጀምሮ በተከናወነው ዝግጅት ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተዋል። ዛሬን ጨምሮ ለአምስት ቀናት በሀገራችን የሚቆየው ዋንጫ ወደ ሀገራችን መምጣቱን በተመለከተ ሦስቱ የክብር እንግዶች ንግግር አድርገዋል። በተለይ የተቋሙ የብራንድ አምባሳደር ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ዋንጫው ወደ ሀገራችን በመግባቱ ደስታ እንደተሰማው ገልፆ በካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥሩ ውጤት እንደሚገጥመው ሀሳቡን አጋርቷል። ከንግግሮቹ በኋላ ደግሞ የዕለቱ የክብር እንግዶች በጋራ ለታሪክ ፎቶ ተነስተዋል።
ይህ ዋንጫ ከአራት ቀናት በኋላ ሀሙስ ሜክሲኮ እና ቦሌ በሚገኙት የቶታል ኢነርጂስ ሰርቪስ ስቴሽኖች ለእግርኳስ ደጋፊዎች እና ለህዝብ ለእይታ እንደሚቀርብም ተጠቁሟል። በዚያው ቀን ከአመሻሽ 10:30 ጀምሮ ደግሞ በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል በሚዘጋጅ ደማቅ ሥነ-ስርዓት የመንግስት ሀላፊዎች፣ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አባላት እንዲሁም ጥሪ የሚደረግላቸው እንግዶች በተገኙበት በድጋሜ ለእይታ እንደሚቀርብ ተመላክቷል። በመጨረሻም በስፍራው የተገኙ ሰዎች ከዋንጫው ጋር ፎቶዎችን እንዲነሱ በማድረግ ሥነ-ስርዓቱ ፍፃሜውን አግኝቷል።