የመጪውን የቤት ኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች ዳሰሳ በዐፄዎቹ የምንጀምር ይሆናል።
ፋሲል ከነማ በሚሌኒየሙ ካደረገው የሊግ ተሳትፎ ውጪ በ2009 የውድድር ዓመት ከከፍተኛ ሊጉ አድጎ ፕሪምየር ሊጉን ከተቀላቀለ ወዲህ በአምስተኛው የውድድር ዘመኑ በቤትኪንግ ስም የተሰየመውን ሊግ ዋንጫ ማንሳት ችሏል። አሸናፊ በነበረበት ባለፈው የውድድር ዓመት ከሊጉ ጅማሬ እስከ ፍፃሜው ውጥ አቋም ያሳየው ቡድኑ 54 ነጥቦችን ይዞ ሲያጠናቅቅ ከተከታዩ ኢትዮጵያ ቡና ጋር የነበረው ልዩነት 13 ነበር። ሊጉን ከተቀላቀለበት ጊዜ አንስቶ በውጤትም ሆነ በቡድን ግንባታ ራሱን እያሻሻለ የመጣው ፋሲል ዘንድሮም በዋንጫ ፉክክር ውስጥ እንደሚኖር የሚጠበቅ ሲሆን ከቻምፒዮንነት ማግስት የሚኖረውን ፈተና በምን ዓይነት ሁኔታ ይወጣዋል የሚለው ጉዳይ ደግሞ ተጠባቂ ሆኗል።
ክለቡን በተሰረዘው እና ባሳለፍነው የውድድር ዓመት በአሰልጣኝነት የመሩት አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ለተጨማሪ አንድ ዓመት ውላቸውን የማራዘማቸው ውሳኔ የፋሲል የቅድመ ውድድር ጊዜው የመጀመሪያ እርምጃ ነበር። ከእርሳቸው ጋርም ምክትሎቻቸው አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ እና አሰልጣኝ ሙሉቀን አቡሀይ አብረው ይቀጥላሉ። በተጨማሪም በግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝነት አዳም ባዘዘው፣ በህክምና ባለሙያነት ሽመልስ ደሳለኝ እንዲሁም በቡድን መሪነት ሀብታሙ ዘዋለ በ2014ቱ የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የፋሲል ከነማ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ሆነው እናያቸዋለን። የክለቡ ውጤታማ ዓመት ማሳለፍ በአሰልጣኝ ቡድን አባላቱ ላይ ምንም ለውጥ ሳያደርግ ወደ አዲሱ የውድድር ጊዜ እንዲመጣ ምክንያት እንደሆነውም ዕሙን ነው።
እንደ አምናው ሁሉ ዘንድሮም ፋሲል ከነማ በዝውውር ገበያው ላይ በጥቂቱ የተሳተፈ ክለብ ሆኗል። በእርግጥ ቡድኑ ከነባር ተጫዋቾቹ መካከል በዋናነት ሙጂብ ቃሲም፣ እንየው ካሣሁን እና መጣባቸው ሙሉን ብቻ ማጣቱ ሲታይ በርካታ ዝውውሮችን እንደማይፈፅም በቀላሉ መገመት ይቻላል። ያም ቢሆን እየተገነባበት የመጣበት ሒደት ከሌሎች ክለቦች ተነጥሎ በትክክለኛው ቀጣይነት ያለው ቡድን የማነፅ ጉዞ ላይ እንዳለ ያመለክታል። በዚህም መሰረት ፋሲል ከነማ ሦስት ዝውውሮችን ብቻ ሲያደርግ ሁለቱ ከቡድኑ ጋር የተለያዩትን ተጨዋቾች በቀጥታ የመተካት አንዱ ደግሞ ተጨማሪ ጥንካሬን የመፍጠር እንድምታ ይታይባቸዋል። በክረምቱ ለረጅም ጊዜ አነጋጋሪ ሆኖ የቆየው እና በመጨረሻም በመለያየት የተቋጨው የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሙጂብ ቃሲም ጉዳይ ሰፊ ክፍተት ሊፈጥር ይችል የነበረ ቢሆንም ፋሲል ናይጄሪያዊው አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢን ቀደም ብሎ በእጁ ማስገባቱ መፍትሄ ሆኖለታል። የቀኝ መስመር ተከላካይ ቦታ ላይ አብዱልከሪም መሐመድ መፈረሙ የእንየውን ክፍተት እንደሚሸፍን ሲጠበቅ አስቻለው ታመነ ወደ ጎንደሩ ክለብ መምጣቱ ደግሞ የመሐል ተከላካይ ምርጫውን ከማስፋቱም በላይ የዋልያዎቹ ተመራጭ የመሐል ተከላካይ ክፍል የሆነውን የያሬድ እና የአስቻለውን ጥምረት በክለብ ደረጃ ለመፍጠር አስችሎታል።
አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ከቡድኑ ጋር ሁለተኛውን የውድድር ዓመታቸውን የሚያሳልፉ በመሆኑ ያለፉት ጊዜያት የግንባታ ሒደት ውስጥ አሻራቸው መኖሩ ተደምሮበት የክለቡ ክፍተትን ብቻ የመሙላት የዝውውር አካሄድ ለእርሳቸውም አሳማኝ ሆኖላቸዋል። “በሙጂብ ነበር ፊት ላይ ስናጠቃ የነበረው። ኦኪኪን ስናመጣ ሀሳባችን የጨዋታ አደራደራችን ወደ 4-4-2 ሊቀየር እንደሚችል ነበር። አሁን ግን ሙጂብ ሌላ ዕድል አግኝቷል። ስለዚህ የለመድነው ፎርሜሽንም ነው ፤ ኦኪኪ መኖሩም ይረዳናል። ከኋላ የአስቻለው መምጣትም የራሱ ጠንካራ ጎን አለው። አብዱልከሪምም በልምድ ይረዳናል።” በማለት ዝውውሮቹ እንደተስማማቸው ይናገራሉ።
ያም ቢሆን ፊት መስመር ላይ ሙጂብን በቀጥታ ከመተካት ባለፈ ተጨማሪ የአጥቂ መስመር ተጫዋች አለማዘዋወሩ ውድድሮች በተጋጋሉ ጊዜ ጉዳት ቢያጋጥም ክፍተቱን ለመሙላት አማራጮቹ ጠባብ እንዳይሆኑበት ያሰጋል። አሰልጣኙ ግን ባለፈው ዓመት እንዳደረጉት ሁሉ በመከላከያ እና አዲስ አበባ ከተማ ያሰለጠኑት እና በፋሲል ውጤታማ ዓመት በወሳኝ ጨዋታዎች ላይ ተቀይሮ በመግባት ልዩነት የፈጠረው አጥቂያቸው ፍቃዱ ዓለሙ ላይ ዕምነታቸውን ጥለዋል። “ፍቃዱ አልፎ አልፎ ጉዳት እየገጠመው በመሆኑ እንጂ አሁን ላይ ወደ ጥሩ አቋም እየመጣ በመሆኑ እና ጥሩ አጥቂያችን ነው ብለን ስለምናምን ክፍተታችን ይህንን ያህል ይሆናል ብዬ አላስብም።”
ፋሲል ከፊት መስመሩ በተለየ የመሐል ተከላካይ ምርጫዎቹ ሰፊ ሆነውለታል። ዓምና በወጥበት የተጠቀመበት የያሬድ ባየህ እና ከድር ኩሊባሊ ጥምረት አሁንም በቡድኑ ውስጥ ይገኛል። ከዚህ ባለፈ በመጨረሻ ጨዋታዎች ላይ ጥሩ ብቃት ያሳየው እና ዘንድሮ ውሉ ተራዝሞለት ከክለቡ ጋር የዘለቀው ዳንኤል ዘመዴም የቦታው ተመራጭ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ቡድኑ ከፍ ያለ ጥራት ያለው ሌላኛውን የመሐል ተከላካይ አስቻለው ታመነን በእጁ አስገብቷል። በመሆኑም ተጫዋቾቹን አማርጦ ከመጠቀም በዘለለ የአደራደር ለውጥ በማድረግ በሦስት የመሐል ተከላካዮች ለመጫወት የሚያስችለው አጋጣሚ እንደተፈጠረለት መናገር ይቻላል። ዐምና በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ላይ መሰል ሙከራዎችን ሲያደርግ መታየቱ እንዳለ ሆኖ የአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ አሁናዊ አስተያየትም ይህንኑ ሀሳብ የሚያጎለብት ነው። “በሚጠቅመን ፎርሜሽን እንገለገላለን። አንዳንዴ በአራት ተከላካይ አንዳንዴ ደግሞ በሦስት ተከላካይ ተሰላፊዎች ልንጠቀም እንችላለን። እንደምንፈልገው የአደራደር ዓይነት ተጫዋቾችን የምንጠቀም ይሆናል። ሦስት ጥራት ያላቸው ተከላካዮች መያዛችን ግን ይጠቅመናል። ምክንያቱም ውድድሩ 30 ጨዋታ ነው። ጉዳትም ሌሎች ነገሮችም ሊኖሩ ይችላሉ። ዐምና በእውነት ዕድለኛ ሆነን በሁለቱ ተከላካዮች ጨርሰናል። ከዛ አንፃር ሦስቱ መኖራቸው ጥቅሙ የጎላ ነው።”
በጥቅሉ የፋሲል ከነማ መስመር የያዘ የዝውውር አካሄድ በበጎ እና በአስተማሪነቱ የሚነሳ ሲሆን አንድ ስጋት ማስከተሉ ግን አይቀርም። የቡድኑ ስብስብ ባለፉት ዓመታት በነበሩት አብዛኞቹ ተጫዋቾች ዘንድሮም ሲቀጥል በተጋጣሚዎቹ ዘንድ ተገማችነትን ሊፈጥርበት ይችላል። ተጋጣሚዎቹ የመጫወቻ መንገዱን፣ ጠንካራ እና ደካማ ጎኑን በአግባቡ ለመረዳት እና የሚያዋጧቸውን ስልቶች ለመንደፍ የሚረዷቸውን በቂ ግብአቶች ከከዚህ ቀደሙ የፋሲል ጨዋታዎች መውሰድ ይችላሉ። ይህንን መቀልበስ የሚቻለውም የተጫዋቾችን የግል ብቃት ከሌሎቹ ዓመታት አሻሽሎ በመቅረብ እንዲሁም አዳዲሶቹን ተጫዋቾች ጥቅም ላይ የሚያውሉ አዳዲስ ስልቶችን በመንደፍ ተገማችነቱን በመቀነስ ነው። አሰልጣኝ ሥዩምም ከዚህ ስጋት ይልቅ የቡድኑ ወጥ የግንባታ ሒደት የበለጠ ትርጉም እንዳለው ዕምነታቸውን የያስቀማሉ። “ሁልጊዜም ቡድን በየዓመቱ ስትገነባ ካለፈው ዓመት አንፃር ይጨምርልኛል የምትለውን እያሰብክ ነው የምትሄደው። ስለዚህ ከቁጥር ማነስ እና መብዛት ይልቅ ጥራቱ ጥንካሬውን የሚጨምር ነው።”
የፋሲል ከነማ የቅድመ ውድድር ዝግጅት ነሀሴ 3 ቀን በባህር ዳር ከተማ የተጀመረ ነበር። ከሌሎቹ ክለቦች በተለየ ዝግጅቱ ሊጉን ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ከሱዳኑ አል ሂላል ጋር የነበረበትን የደርሶ መልስ ጨዋታ ከግምት ውስጥ ያስገባ ነበር። ምንም እንኳን በሁለቱም ጨዋታዎች አቻ የተለያየው ቡድኑ በድምር ውጤት ከውድድሩ በጊዜ ቢሰናበትም በኮስታራ የውድድር ጨዋታ ራሱን መፈተሽ መቻሉ ግን ለአጠቃላዩ የውድድር ዓመት ዝግጅቱ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑ አይቀርም። አሰልጣኙም በዚህ ሀሳብ ይስማማሉ። “ጨዋታው ጥሩ ጠቀሜታ አለው። ምክንያቱም ሂላል በአፍሪካ ከሚገኙ ስመ ገናና ቡድኖች ውስጥ አንዱ ነው። ከቡድኑ ጋር በሜዳችንም ከሜዳችንም ውጪ የነበረን እንቅስቃሴ ጥሩ ስለነበር ለሊጉ ውድድር ጥሩ ጎን አለው ይረዳናልም ብዬ አስባለሁ። ” ሲሉ ጠቀሜታውን ያስረዳሉ።
ከዚህ ውጪ የፋሲል ከነማ የዝግጅት ጊዜ ፈተና ተደርጎ የሚታየው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የዝግጅት ጊዜ እና ጨዋታዎች ነበሩ። ስድስት ተጫዋቾችን ለዋልያዎቹ ያስመረጠው ፋሲል የዝግጅት ጊዜውን ያለእነዚህ ወሳኝ ተጫዋቾቹ ለመከወን ተገዷል። በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ ተጫዋቾቹን አለማካተቱ ከላይ እንደተጠቀሰው በፉክክር ጨዋታዎች በዋና ተሰላፊዎቹ ከእስካሁኑ የተለዩ ስልቶችን ተግብሮ ውጤታቸው ለማየት ክፍተት የሚፈጥርበት ነው። በሌላ ጎኑ ስንመለከተው ደግሞ ቡድኑ አብሮ የቆየ በመሆኑ እና በአዲስ መልክ የተቀላቀሉት ተጫዋቾች በቁጥር በርካታ አለመሆናቸው ብዙ እንቅፋት እንዳይፈጥርበት የሚረዳው ነው። የሌሎች ተጫዋቾችን ብቃት ገምግሞ ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ ገብተው ሊፈጥሩ የሚችሉትን ጥቅም ለመረዳትም በር ሊከፍትለት ይችላል።
ሁሌም ቢሆን ከቻምፒዮንነት በኋላ የሚመጣ የውድድር ዓመት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። አሸናፊነት በአንድ የውድድር ዓመት የመጣ አጋጣሚ እንዳልሆነ ለማሳየት ክለቦች በትክክልም የበላይነታቸውን ለማጉላት ደጋግመው ዋንጫዎችን ማንሳት ይኖርባቸዋል። ከዓላማ ከፍታ አንፃር ካየነውም ከሊግ ክብር ባለፈ በአህጉራዊ ውድድር ላይ በወጤት ተሻሽሎ ለመታየት ትኬት መቁረጫው መንገድ ዳግም ቻምፒዮን ሆኖ መገኘት መሆኑ እርግጥ ነው። ከዚህ አንፃር ፋሲል ከነማ ዘንድሮ ከዓምናው ገዘፍ ያለ ፈተና ይጠብቀዋል። የሊጉ የሁልጊዜም የዋንጫ ፉክክር እንዳለ ሆኖ የዐምና ቻምፒዮኖቹ በእያንዳንዱ ጨዋታ በተፎካካሪዎቻቸው ዘንድ የተለየ ትኩረት እየተደረገባቸው መሄዱ የማይቀር ነው። ዋና አሰልጣኙም ይህን ጉዳይ ከግምት ውስጥ ያስገቡት ይመስላል። “ፋሲል በሊጉ ከሚጠቀሱ ጠንካራ ቡድኖች መካከል አንዱ ስለሆነ የምንዘጋጀውም በዛ ልክ ነው። ዕቅዳችንም አላማችንም በድጋሚ ቻምፒዮን መሆን ነው። በዚህ ውስጥ እያንዳንዱ ጨዋታ ላይ ትልቅ ፈተና ይጠብቀናል። ያንን ለመወጣት እኛም በቂ ዝግጅት አድርገን እንቀርባለን ብዬ ነው የማስበው።”
የተጠባቂነት ፈተና ውጪያዊ ከሆነው የተጋጣሚዎች ፉክክር ብቻ ሳይሆን ከውስጥም የሚመጣ ነው። የክለብ አመራሮች እና ደጋፊዎች የቡድናቸው ዕድገት በመጣበት መንገድ እንዲቀጥል ይጠብቃሉ። ፋሲሳ ባለፈው ዓመት ካሳያቸው የቻምፒዮንነት ማማ ላይ ሳይወርድ ተጨማሪ ስኬቶችን ሲያጣጥም መመልከት መፈለጋቸው አይቀርም። ይህ ደግሞ ከውጪያዊው ፈተና በላይ ጉልበት ያለው መሆኑ ግልፅ ነው። አሰልጣኝ ስዩም ከበደ የዚህን ጫና ሁኔታ ዓምና የተመለከቱበትን ቀዳሚ ሳምንታት በማስታወስ ዘንድሮ ሊፈጠር እንደማይገባው አበክረው ይናገራሉ። “አንድ ቡድን ቻምፒዮን መሆኑ የሚታወቀው በስተመጨረሻ ነው። በመሐል ላይ ውጣ ውረዶች ሊኖሩ ስለሚችሉ ደጋፊዎቻችን ሁሌም በትዕግስት መጠበቅ አለባቸው። ባለፈው ዓመት ገና ሊጉ ተጀምሮ በሦስተኛው ጨዋታ ላይ የውጤት መዋዥቅ ሲገጥመን የነበረውን የደጋፊውን ጫና የምናስታውሰው ነው። ነገር ግን በስተመጨረሻ ቻምፒዮን ሆነናል። ድጋፍ ማለት እስከ እንጥፍጣፊው እስከ ሠላሳኛው ሳምንት ድረስ በትዕግስት ጠብቆ ቡድኑ ሲዳከም አጠናክሮ ጥሩ ሲሆን ደግሞ ይበልጥ ጥሩ እንዲሆን ማበረታታት ከደጋፊያችን ይጠበቃል።”
በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ዘንድሮ ከዐምናው የተሻለ ሆነው ሊታዩ የሚችሉ ተጫዋቾችን ስንመለከት በቅድሚያ ሱራፌል ዳኛቸውን እናገኛለን። የቀድሞው የአዳማ ከተማ አማካይ እንደ ተጫዋች ከላበት ደረጃ እና በመጀመሪያው ዓመት በፋሲል ካሳየው አቋም አንፃር በ2013 በተለይም እስከሊጉ አጋማሽ ድረስ በተጠበቀው ልክ አልተንቀሳቀሰም። ተጫዋቹ በክረምቱ በብሔራዊ ቡድን ካሳየው ንቃት አንፃር ሲታይ ግን ዘንድሮ በክለቡ ውስጥ ጎልቶ ሊወጣ እንደሚችል ይገመታል። ሌላኛው የቀድሞው ቡድን አጋሩ በረከት ደስታም በአዳማ ይታይበት የነበረው ተፅዕኖ ፈጣሪነት ተቀዛቅዞ ቢታይም በአፍሪካ ውድድር እና አዲስ አበባ ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ የቀደመ ትኩረት ሳቢነቱን የመመለስ ፍንጭ አሳይቷል። ይህን ጠንካራ ጎን ወደ ዋናው ውድድር ይዞ ከመጣ ዓምና በሊጉ በርካታ ኳሶችን (11) ለግብ ያመቻቸው ሽመክት ጉግሳን ኃላፊነት መካፈል በተፅዕኖ ፈጣሪነቱ ውስጥ ከበረከት የሚጠበቅ ጉዳይ ነው።
የኦኪኪ አፎላቢ ወደ ፋሲል መምጣት በራሱ የተጨዋቾች ኃላፊነት ላይ ለውጥ የሚያመጣ ነው። የመጨረሻ አጥቂነት ባህሪን ከተላበሰው ሙጂብ ይልቅ ኦኪኪ ወደ አማካይ ክፍል እና ወደ መስመር ቀርቦ ንክኪዎችን የመፍጠር ባህሪ ፊት ላይ የሚፈጥረውን ክፍተት ተጠቅሞ ግብ ማስቆጠር ላይ የተሻለ መሆንን ከአማካዮች በተለይም ከበረከት ደስታ እና ሽመክት ጉግሳ ዓይነት ተጨዋቾች እንድንጠብቅ ያደርጋል። በሌላ በኩል መሀል ክፍል ላይ ከሀብታሙ ተከስተ ጋር በመጣመር አልፎ አልፎም ብቸኛ ተከላካይ አማካይ ሆኖ የምናየው ይሁን እንዳሻው ሌላው ጎልብቶ እንደሚመጣ የሚጠበቅ ተጫዋች ነው። በዋልያዎቹ የማጣሪያ ጨዋታዎች ቀዳሚ ምርጫ ውስጥ ሲካተት የታየው ቁመተ አጭሩ አማካይ ካለውም ልምድ አንፃር ይህንን አቋም በሊጉ ሊያስቀጥል ይችላል። ከግብ ጠባቂው ፊት ያለውን ስብስብ ስንመለከትም ያሬድ ባየህ ፣ ከድር ኩሊባሊን ፣ ዳንኤል ዘመዴን እና አዲስ ደራሹ አስቻለው ታመነ በግል ብቃት ነጥሮ መውጣት መቻል የቡድኑ ቀደሚ ተመራጭ የሚያደርጋቸው መሆኑ ፉክክራቸው ይበልጥ ተሻሽለው እንዲመጡ በር ከፋች ይሆናል።
የፋሲል ከነማ የ2014 ሙሉ ስብስብ
ግብ ጠባቂዎች
1 ሚኬል ሳማኬ
30 ይድነቃቸው ኪዳኔ
31 ቴዎድሮስ ጌትነት
ተከላካዮች
2 አብዱልከሪም መሀመድ
3 ሄኖክ ይትባረክ
5 ከድር ኩሊባሊ
12 ሳሙኤል ዮሐንስ
13 ሰዒድ ሐሰን
15 አስቻለው ታመነ
16 ያሬድ ባየህ (አምበል)
21 አምሳሉ ጥላሁን
25 ዳንኤል ዘመዴ
32 ዳንኤል ፍፁም (U-23)
አማካዮች
6 ኪሩቤል ኃይሉ
7 በረከት ደስታ
8 ይሁን እንዳሻው
10 ሱራፌል ዳኛቸው
14 ሀብታሙ ተከስተ
17 በዛብህ መለዮ
18 ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ
19 ሽመክት ጉግሳ
24 አቤል እያዩ
27 ዓለምብርሀን ይግዛው
33 ደጀን ገበየሁ (U-23)
አጥቂዎች
4 ኦኪኪ አፎላቢ
9 ፍቃዱ ዓለሙ
28 ናትናኤል ማስረሻ
35 ፋሲል መራው (U-23)
ማስታወሻ
በምስሉ ላይ የሚታዩ ፎቶዎች በተነሱበት ወቅት ለብሔራዊ ቡድን የተመረጡ ተጫዋቾች ከቡድኑ ጋር ያልነበሩ በመሆኑ መካተት አለመቻላቸውን እንገልፃለን።