ሀዋሳ ከተማ በክረምቱ የዝውውር መስኮት አስፈርሞት የነበረውን ካሜሩናዊ አጥቂ ማሰናበቱ ታውቋል፡፡
የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን አገባዶ የፊታችን ዕሁድ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመክፈቻ ጨዋታ ጅማ አባጅፋርን በመግጠም ውድድሩን የሚጀምረው የአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉው ክለብ ሀዋሳ ከተማ በርካታ አዳዲስ እና ነባር ተጫዋቾችን ይዞ የዝግጅት ምዕራፉን በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ሲገመግም ሰንብቶ ሁለተኛ ደረጃ በመያዝ ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ ክለቡ ከአርባ ሁለት ቀናት በፊት የካሜሩን ዜግነት ያለው አጥቂው ኤይሚ ጄይካ ጋሲሶውን በአንድ ዓመት ውል አስፈርሞ የነበረ ቢሆንም ተጫዋቹ በልምምድ ወቅት እንዲሁም በወዳጅነት ጨዋታዎች ላይ ያሳየው አቋም እና እንቅስቃሴ አሰልጣኞችን ባለማሳመኑ መሰናበቱን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡
በደቡብ አፍሪካው ክለብ ኤሚ ሌስ አስተርስ ፣ በደቡብ ኮሪያው ክለብ ኢችኦን ሲትዝን ፣ በቬትናሞቹ ኤስ ኤች ቢ ዳ ናንግ እና ታሀአንች ሆአ በተባሉ ክለቦች እንደተጫወተ የህይወት ታሪኩ የሚያትተው ይህ ተጫዋች በአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በሜዳ ላይ ባለመወደዱ ለመለያየት ችሏል፡፡ ሀዋሳ ከተማ የተጫዋቹን ቦታ ከታች ባደጉ አጥቂዎች ለመተካት ማሰቡን ሰምተናል፡፡