መከላከያ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያሳደጉትን የቡድን አባላት ሸልሟል

በአሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ እየተመራ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተመለሰው መከላከያ ዛሬ አመሻሽ የቡድን አባላቱን እውቅና ሰጥቷል።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ 1 የበላይ ሆኖ የሀገሪቱን ከፍተኛ የሊግ እርከን ዳግም የተቀላቀለው መከላከያ ዘግይቶም ቢሆን ወደ ሊጉ ያሳደጉትን አባላት ሽልማት ሰጥቷል። ከምሽቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ በራስ ሆቴል በተካሄደው ዝግጅት ላይ የስፖርት ክለቡ የቦርድ አባል እና የመከላከያ ኢንዶክትሬሽን ዋና መምሪያ ተወካይ የሆኑት ብርጋዴል ጀነራል አስፋው ማመጫ፣ ጀነራል ኩማ ሚደቅሳ እና ኮሎኔል ማንያለዋል ታደለ በክብር እንግድነት ተገኝተዋል።

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ባለው ጦርነት ለተሰው የሰራዊቱ አባላት የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማድረግ የተጀመረው የምሽቱ መርሐ-ግብር የክለቡ ዳይሮክቶሬት ዳይሬክተር ደረጄ መንግስቱ የመክፈቻ ንግግር አድርገው በይፋ ተጀምሯል። አመራሩም የመጣውን ዋንጫ በጦርነቱ ለተሰው የሰራዊቱ አባላት ታሳቢ ለማድረግ እቅድ ተይዞ ዓመቱን ሙሉ ሲሰራ እንደነበር ጠቅሰው በታሰበው ልክ ዋንጫው እንደመጣ አውስተዋል። በተቋሙም ስም ተጫዋቾቹ፣ አሠልጣኞቹን እና አመራሮቹን አመስግነዋል። በመቀጠል ደግሞ በምድቡ በ38 ነጥቦች ወደ ሊጉ እንዲያድግ ያደረጉት የቡድኑ አባላት ያገኙትን ዋንጫ በአምበላቸው አሌክስ ተሰማ እና የቡድን መሪው አለሙ አማካኝነት ለአመራሮቹ አበርክተዋል። ከዛ ደግሞ የክለቡ የደጋፊ ማህበር ለሰራዊቱ አመራሮች ስጦታ ሰጥተዋል።

አስከትሎ ደግሞ በሦስት ደረጃዎች ከ200 ሺ ብር ጀምሮ እስከ 50 ሺ ብር ድረስ ሽልማት መሰጠት ተይዟል። በዚህም ከአሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ጀምሮ እስከ ተጫዋቾች ድረስ እንደየ ደረጃቸው ሽልማታቸውን ተረክበዋል። ሽልማቱን የሰጡት የስፖርት ክለቡ የቦርድ አባል ብርጋዴል ጀነራል አስፋው ክለቡ ወደ ሊጉ ማደጉን አድንቀው ሰራዊቱ ሙሉ በውጤቱ እንደተደሰተ አመላክተዋል። አስከትለውም እንደ ሀገር አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀውን ሀይል ማጥፋት እንዲሁም በኳሱ በፕሪምየር ሊጉ የተሻለ ውጤት እንዲመጣ እቅድ አለን ካሉ በኋላ ወራሪውን ሀይል ለመደምሰስ በሚደረገው ርብርብ ክለቡ ድል ማምጣት አለበት በማለት ጠንከር ያለ ሀሳብ አስተላልፈዋል። በመጨረሻም መከላከያ የተላበሰውን የአሸናፊነት መንፈስ ተላበሱ ብለው መልዕክት አስተላልፈው ሀሳባቸውን አገባደዋል። መርሐ-ግብሩም የእራት ግብዧ ከተደረገ በኋላ ፍፃሜውን አግኝቷል።