የክለቦች ቅድመ ውድድር ዝግጅት | ድሬዳዋ ከተማ

የክለቦችን የክረምቱን የዝግጅት ጊዜ እና ቀጣዩን የውድድር ዓመት ገፅታ እየቃኘንበት በምንገኘው ጥንቅራችን በቀጣይ ድሬዳዋ ከተማን እንመለከታለን፡፡


የምስራቁ ክለብ ድሬዳዋ ከተማ 2008 የውድድር ዘመን ላይ ዳግም ወደ ሊጉ ከተመለሰ በኋላ አራተኛ የውድድር ዓመቱን ይጀምራል፡፡ ባለፉት ስድስት ዓመታት ክለቡ በሊጉ የነበረው ቆይታ ሲታይ ግን በተረጋጋ ውጤት የታጀበ አልነበረም፡፡ ባሳለፍነውም ዓመት የመጀመሪያውን ዙር በሦሰት ድሎች ብቻ ለማጠናቀቅ የተገደደው ድሬ የአሰልጣኝ ለውጥ እና የስብስብ ማሻሻያ በማድረግ በመጨረሻዎቹ ሳምንታት ላይ በሰበሰባቸው ነጥቦች ነበር የወራጅ ቀጠናውን በስድስት ነጥቦች በመራቅ በድምሩ 28 ነጥቦችን ይዞ 10ኛ ደረጃን ላይ ለማጠናቀቅ የበቃው፡፡ በተለይም ከመጨረሻዎቹ ሰባት ጨዋታዎች በስድስቱ ከሽንፈት መራቁ እና 12 ነጥቦች መሰብሰቡ ለቡድኑ ትልቅ እገዛ ነበረው፡፡ እነዚህ 12 ነጥቦች የክለቡን አጠቃላይ የውድድር ዓመቱን ድምር ነጥብ 42 በመቶው የሚሸፍኑ ሲሆን በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ ሌሎች ክለቦች ካስመዘገቡት ውጤት ጋር ካስተያየነው ደግሞ ከሲዳማ ቡና እና ሰበታ ከተማ በመቀጠል ከውድድሩ አሸናፊ ፋሲል ከነማ ጋር ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚያስቀምጠው ነው፡፡ በጥቅሉ ድሬዳዋ ከተማ ባለፉት ጊዜያት ደካማ የዓመቱ ጉዞውን አጨራረሱን በማሳመር እየሻረ ወደ ቀጣዩ ዓመት በመሻገር የሰለጠነ ይመስላል፡፡

 

በ2013 በሊጉ ከነበሩ እና ዘንድሮ የአሰልጣኝ ለውጥ ሳያደርጉ ለውድድር ከሚቀርቡ አምስት ክለቦች ውስጥ አንዱ ድሬዳዋ ከተማ ነው፡፡ የውድድሩ 13ኛ ሳምንት ላይ ወደ ኃላፊነት የመጡት አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ክለቡ በነበረው 10 ነጥቦች ላይ ተጨማሪ 18 ነጥቦችን ጨምሮ በሊጉ እንዲቆይ ማስቻላቸው ዕምነቱን እንዲጥልባቸው እና ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት አብረው እንዲቀጥሉ አድርጓል፡፡ ከዋና አሰልጣኙ በተጨማሪ አሰልጣኝ ቶፊቅ እንድሪስ እና አሰልጣኝ ኤፍሬም ጌታሁን በምክትል አሰልጣኝነት እንዲሁም አሰልጣኝ አምባዬ በፍቃዱ የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ ሆነው የሚቀጥሉ ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጌታቸው ወልዴ እና አሥራት ለገሠ የቡድኑ የህክምና ባለሙያዎች ሲሆኑ ቆፊቅ ሀሰን በቡድን መሪነት እንዲሁም ኢንስትራክተር ፉዓድ የሱፍ በቴክኒክ ዳሪክተርነት የክለቡ አባል ናቸው።

ድሬዳዋ ከተማ ከአሰልጣኝ አንፃር በነባሩ ይቀጥል እንጂ ሰብስቡ በአመዛኙ በአዳዲስ ተጫዋቾች የተደራጀ ሆኗል። ከቡድኑ መዋቅር ውስጥ ስር ነቀል ሊባል የሚችል ለውጥ የተደረገበትም የፊት መስመሩ ሆኗል። የሦስቱን የውጪ ዜጎች ጁኒያስ ናንጄቦ ፣ ኢታሙና ኬሙይኔ እና ሪችሞንድ ኦዶንጎን ምትኮች ፍለጋ ወደ ገበያ የወጣው ክለቡ ማሊያዊው ማማዱ ሲዲቤ፣ አብዱራህማን ሙባረክ እና ሄኖክ አየለን አስፈርሟል። ጋዲሳ መብራቴ፣ አብዱለጢፍ መሀመድ እና አቤል ከበደም በመስመር አጥቂነት ማገልገል የሚችሉ እና የድሬን የፊት ክፍል ለማጠናከር ወደ ክለቡ የመጡ ሌሎች ፈራሚዎች ናቸው። አማካይ ክፍሉን ስንመለከት አሰልጣኙ ቡድኑን በተረከቡበት የ2013ቱ ውድድር የተጠቀሙባቸው አብዛኞቹ ተጫዋቾች አሁንም ከክለቡ ጋር የቀጠሉ ሲሆን ብሩክ ቃልቦሬ እና መጣባቸው ሙሉ ቦታውን ለማጠናከር በብስቡ ውስጥ ተካተዋል።

“ያለፉትን ጊዜያት የክለቡን አፈፃፀም ስናየው በዓመት ከ 30-33 ጎል ይቆጠርበታል። እዛ ላይ ትኩረት አድርገን መስራት ይጠበቅብናል። እኛ በዓመት ከ15 ጎል በታች ብቻ መቆጠር ይኖርበታል ብለን ነው የምናስበው። በዚህም ጠንካራ የተከላካይ ክፍል መስራት እንዳለብን እናስባለን። ባለፉት ዓመታት የነበሩትን ችግሮች በሙሉም ባይቻል እንኳን በተወሰነ መልኩ ቀርፈን የተሻለ ቡድን መስራት እናስባለን።” የሚሉት አሰልጣኝ ዘማርያም እንደ በረከት ሳሙኤል ፣ ፍሬዘር ካሳ ፣ ያሬድ ዘውነህ እና ዘነበ ከበደ ጋር በተለያየው ቡድናቸው ውስጥ የኋላ ክፍሉን ዳግም ለማዋቀር እንየው ካሣሁን፣ መሳይ ጳውሎስ እና ጋናዊው የመሐል ተከላካይ አውዱ ናፊዩን ማምጣት ችለዋል። በግብ ጠባቂዎች ረገድ ደግሞ ደረጄ ዓለሙ በክረምቱ አነጋጋሪ ከነበሩ ዝውውሮች መካከል በአንዱ ወደ ወላይታ ድቻ ያመራው ወንድወሰን አሸናፊን ክፍተት ሊሸፍን ከብርቱካናማዎቹ ጎራ ተቀላቅሏል።

ይህንን የውድድር ዓመት በዋነኝነት ከዚህ ቀደም ደጋግሞ ያየውን የስጋት ጉዞ ገሸሽ አድርጎ እርጋታ የተሞላበት ዓመት ማሳለፍን ዋና ዓላማው አድርጎ በመስራት ላይ የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ ጎን ለጎን በስብስቡ ውስጥ ወጣቶችን በቡድኑ ለማካተት በማሰብ ለአካባቢው ወጣቶች በሰጠው የሙከራ ዕድል ሚካኤል ሳሙኤል ፣ አቤል አሰበ እና አብዱልፈታ ዓሊ የተባሉ ተጫዋቾችን የቡድኑ አካል አድርጓል።

ድሬዳዋ ከተማ የቅድመ ውድድር ጊዜ ዝግጅቱን ለመከወን ሀዋሳን ምርጫው አድርጓል፡፡ ነሐሴ 21 በጀመረው የዝግጅት ጊዜውም የጂምናዚየም ሥራዎችን በሀዋሳው ኃይሌ ሪዞርት እንዲሁም የሜዳ ላይ ሥራዎቹን በደቡብ ኮሌጅ ሜዳ ላይ ሲከውን ሰነባብቷል፡፡ በእነዚህ ወቅቶች አሰልጣኝ ዘማርያም አዲስ ቡድን በመገንባት ሒደት ላይ በመሆናቸው ከ6-8 ሳምንት የሚደርስ የዝግጅት ጊዜ እንዲኖራቸው ሀሳቡ የነበራቸው ቢሆንም ባለው ጊዜ በአራቱም የቡድን ግንባታ ሂደት ንዑስ ክፍሎች ቴክኒክ፣ ታክቲክ፣ አካል ብቃት እና ሥነ-ልቦና በኩል ሲዘጋጁ መቆየታቸውን ነግረውናል። ከዚህ በተጨማሪ የወዳጅነት ጨዋታዎች እና በክረምት የክለቦች ውድድር ላይ ተሳትፎ ማድረግ የቡድኑ አጠቃላይ የዝግጅት ዕቅድ ውስጥ የተካተቱ ነጥቦች ነበሩ። በዚህም ከሀዋሳ ከተማ ጋር 1-1 የተለያዩበትን ጨዋታ ማድረግ ሲችሉ በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ጨዋታዎችም አራት ግጥሚያዎችን መከወን ችለዋል።

በቁጥር በርከት ያሉ ዝውውሮችን የፈፀመው ድሬዳዋ ከዐምናው ጋር ሲተያይ ቡድኑን ይበልጥ ሊያጠናክር የሚችልበት ሌሎች ዝውውሮች ሊኖሩ ይችሉ እንደነበር የአሰልጣኝ ዘማርያም አስተያየት ይጠቁማል። “የምንፈልገውን ያህል ተጫዋቾች አግኝተናል ብለን አናስብም። ጊዜው የውድድር ስለሆነም እየፈለግናቸው ከገንዘብ ጋር ተያይዞ የሄዱ ተጫዋቾች አሉ። በአቅማችን መስራት ስላለብን ፤ ያንን ምንም ማድረግ አንችልም። ነገር ግን ከዛ አንፃር ዘንድሮ ከባለፉት ዓመታት የክለቡ ታሪክ ተነስተን ሁል ጊዜ ላለመውረድ የሚጫወት ቡድን በመሆኑ ዘንድሮ ያንን አንድ ደረጃ ከፍ ማድረግ ከቻልን በቀጣይ ዓመት ደግሞ ክፍተቶቹን እየደፈንን ቡድን በሒደት ስለሚገነባ በቀጣይ ሁለት ሦስት ዓመታት ውስጥ ተወዳዳሪ እና ሊጉ ላይ ከአንድ እስከ አምስት የሚወጣ ተረጋግቶ የሚቀመጥ ቡድን ለመሥራት እንደጅማሮው ጥሩ ስብስብ አለን ብዬ አስባለሁ።”

የብርቱናማዎቹ የዝውውር ምርጫዎች ሲመዘኑ በተለይም የፊት መስመሩ ስብስብ ላይ ያለው የተጨዋቾች የግል ጠንካራ ጎኖች ሲታዩ ቡድኑ ከዐምናው አጨዋወቱ የተለወጠ አቀራረብ እንደሚኖረው ፍንጭ የሚሰጥ ነው። “ቡድን በአንድ የውድድር ዘመን ተገንብቶ የሚያልቅ ነገር አይደለም። እኔ ቡድኑን ዘንድሮ እንደ አዲስ እንደያዝኩት ነው የማስበው። ዓምና ቡድኑን ለማትረፍ ግማሽ ላይ ነበር የያዝነው። ቡድኑ ይጫወትበት የነበረውን መንገድ ይዘን እሱን እያዳበሩ እንዲሄዱ ከማድረግ አንፃር ነበር የሰራነው። በዚህም ቡድኑ ረዘም ያሉ ኳሶችን ይጫወት ነበር። አሁን ግን ተጫዋቾች ስንመለምል ጀምሮ አጭር እና መካከለኛ ቅብብሎችን እየተጠቀመ የሚጫወት ቡድን ለመሥራት የሚሆኑ ተጫዋቾችን ለመያዝ ሞክረናል።” የሚሉት የዋና አሰልጣኙ ሀሳብም ከቡድኑ የሚጠበቀውን የአጨዋወት ዘይቤ ለውጥ የሚጠቁም ነው። አሰልጣኙ ቀጥለውም ለውጡ ምንን መሰረት ያደረገ እና ወደምን የሚያመዝን ስለመሆኑ ሲናገሩ “ዐምና የነበረውን አጨዋወት ዘንድሮ ያሉት ተጫዋቾች ይተገብሩታል ብዬ አላስብም። በተለይ ፊት ላይ እንደ እነ ናንጄቦ ዓይነት አጥቂዎች ስለነበሩ እና ፈጣንም ስለነበሩ ከፍ ያሉ ኳሶችን እንጠቀም ነበር። በዛ መንገድ ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ለማድረስ እንሞክር ነበር። አሁን ግን ኳስን ከኋላ መስርተን ለመጫወት ነው እየሰራን የምንገኘው። ከተጨዋቾች በመነሳት ነውና ዕቅድ የሚዘጋጀው በዛ መንገድ እንቀጥላለን።” ይላሉ።

የሚያስተናግደውን አማካይ የጎል መጠን በግማሽ የመቀነስ ውጥን ያለው እና ወደ ግብ የሚደርስበትን አካሄድ በኳስ ቁጥጥር ላይ ከተመሰረተ ብልጫ ለማግኘት ያቀደው ድሬዳዋ ከተማ ሌላው ቀይሮ ለመምጣት ግድ የሚለው አዕምሯዊ ጥንካሬን ነው። የክለቡ የወራጅ ቀጠና ደንበኝነት አዲስ በሚገናባቸው ስብስቦች ውስጥም እየተዘዋወረ በመምጣቱ ከዚህ አዙሪት ወጥቶ በትክክልም የተፎካካሪ ቡድን ሥነ-ልቦና መገንባት የአመራሩም ሆነ የአሰልጣኝ ቡድን አባላቱ ቀዳሚ የስኬት መለኪያ ቢሆን አያስገርምም። “አብዛኞቹ ተጫዋቾች ይህንን ያለፉት ዓመታት ታሪክ በርቀት ነው የሚያውቁት አዲስም ስለሆኑ። አሁን ወደ ድሬዳዋ ሲመጡ ግን በትልቁ ትኩረት አድርገን እንሠራለን ያልነው እዚህ ጉዳይ ላይ ነው። ሥነ-ልቦናው ላይም እየሠራን ነው።” የሚሉት አሰልጣኝ ዘማርያም በነበሩባቸው ክለቦች የተለያየ አይነት የፉክክር ደረጃ ውስጥ የነበሩ አዳዲስ ፈራሚዎቻቸውን ከነባሮቹ ጋር ሲያዋህዱ የአሸነፊነት መንፈስ በውስጣቸው የመዝራት የቤት ሥራቸውን እንደጀመሩ ጠቁመዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ስለሚጠበቅባቸው ነገር እና ስለ ደጋፊዎች ባህሪ ሲያስረዱ ይህንን ፈገግ የሚያስብል ሀሳብ አንስተዋል። “የድሬዳዋ ተመልካች ብዙ ወጣቶችን ለሀገሪቱ እግርኳስ ያበረከተ ነው። እንደአጋጣሚ ሆኖ ወደኋላ ቀርቶ ሊሆን ይችላል እንጂ የከተማው እግርኳስ ከዚህ በፊት ያለው ታሪክ የተለየ ነው። ደጋፊዎቹ ግን በዕውቀት የሚደግፉ ናቸው። ስታሸንፍ ‘በአጋጣሚ አሸነፍክ እንጂ…’ ብለው እንደቡድን ያሳየኸውን አቋም ይነግሩሀል። አሁን ደጋፊ ወደ ሜዳ የሚመለስበት ጊዜም ስለሆነ እነሱን የሚመጥን ቡድን ካላቀረብክ በካልቾ ብለው ነው የሚያባሩህ (ሣቅ)። ስለዚህ እነሱን የሚመጥን ቡድን እንሰራለን ብለን እናስባለን።”

ድሬዳዋ ከተማ በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ጨዋታዎች የመጨረሻ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። እርግጥ ነው የቅድመ ውድድር ዘመን ላይ የሚደረጉ የፉክክር ውድድሮች ከመዘጋጃነት ባለፈ የዓመቱን ውጤት ሊጠቁሙ አይችሉም። ያም ሆኖ ቡድኑ ለማሻሻል ካሰባቸው ነጥቦች ዋነኛው አሁንም ክፍተትን ያሳየ መሆኑ ትኩራትን ይሻል። ይህም በመከላከሉ ረገድ ያለበት ድክመት በውድድሩ ሰባት ጎሎችን በማስተናገዱ ዳግም የመታየቱ ሁኔታ ነው። ድሬ በውድድሩ እጅግ ወሳኝ በሆነው የመሐል ተከላካይ ቦታ ላይ ተለዋዋጭ ጥምረቶችን በመጠቀም ያሳየን ሲሆን ከተጫዋቾቹ መሀከልም የወጣቱ ሚኪያስ ካሣሁን ልምድ ማነስ የጋናዊው አውዱ ናፊዩ ለሊጉ አዲስ መሆን እና የመሳይ ጳውሎስ የዝግጅት ጊዜ ጉዳት የአሰልጣኙን የጥምረት ምርጫ ከባድ ያደርገዋል። ለዚህም ይመሳል ተከላካይ አማካዩ ዳንኤል ደምሴን በቦታው የማሳለፍ አማራጭ ተተግብሮ የተመለከትነው። ከዳንኤል በተጨማሪ ከአንድ በላይ የሜዳ ላይ ኃላፊነቶችን ሊወጡ የሚችሉ ሌሎች ተጫዋቾች በስብስቡ ውስጥ መኖራቸው መሰል ክፍተቶችን ለመድፈን ለአሰልጣኝ ዘማሪያም ተጨማሪ እገዛ እንደሚሆናቸው ይጠበቃል።

ድሬዳዋ ካለፈው ዓመት አጨራረሱ ወደ ዘንድሮ ማሻገር ከሚገባው ጠንካራ ውህደቶች መካከል የዳንኤል ደምሴ እና ዳንኤል ኃይሉ ጥምረት ዋናው ነው። ከተከላካይ መስመሩ ፊት የተረጋጋ የኳስ ፍሰትን ከማስጀመር እና ከኋላ ያለውን ድክመት ከመሸፈን አንፃር ጥምረቱ በጀመረበት ሁኔታ እንዲቀጥል የግድ ይላል። ይህም የቡድኑ የኳስ ፍሰት ወደ ግብ ሙከራዎች እንዲቀየሩ ወሳኙን ሚና የሚወጣው ሱራፌል ጌታቸውን ሥራ ለማደላደል ድርሻ ይኖረዋል። ሱራፌል ዓምናም የአማካይ ክፍሉን በመምራት የፈጠራ ምንጭ ሲሆን መስተዋሉ ዘንድሮም በድጋሚ በቦታው ጎልቶ የሚወጣ የቡድኑ ሌላኛው ትኩረት ሳቢ ተጫዋች ያደርገዋል።

ከዚህ ውጪ አምና ስምንት ግቦችን ያስቆጠረው ሙኸዲን ሙሳ ዕድገቱን ጨምሮ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋችነቱ ጎልቶ እንደሚወጣ ይጠበቃል። በእርግጥ በአሰልጣኝ ዘማርያም ስር ከመጨረሻ አጥቂነት ይልቅ ለተደራቢ አጥቂነት የቀረበ ሚና ሲሰጠው መታየቱ ከተጋጣሚ ግብ ሊያርቀው ቢችልም በግል ያለው ፍጥነት እና ክፍተቶችን ፈልጎ ወደፊት በጥልቀት የመግባት ብቃቱ በሊጉ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ዝርዝር ውስጥ እንዳይጠፋ ሊያደርገው ይችላል። ፊት ላይ ጥሩ ፈራሚ ሆኖ የሚጠቀሰው ማማዱ ሲዲቤም ካለው የግል ክህሎት አንፃር የስብስቡን ጥራት በመጨመር ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል። የተጫዋቹ ብቃት እንዳለ ሆኖ በኢትዮጵያ ያለፉት አራት ዓመታት ቆይታው የታየበት የወጥነት ችግር ዳግም እንዳይንፀባረቅ ግን ያሰጋል። ድሬዳዋ ለወትሮውም ወጥ ግብ አግቢ ሳይኖረው መቆየቱ ሲታይም በማሊያዊው አጥቂ ላይ ከተመረኮዘ ይህ የተጫዋቹ ደካማ ጎን በአስፈላጊ ሰዓቶች ላይ ተፈላጊውን ግልጋሎት እንዳያሳጣው ያሰጋዋል።

ሌላው ትኩረት የሚስበው ተጫዋች የመሀል ተከላካዩ ሚኪያስ ካሣሁን ነው። ወጣቱ የልምድ እጥረት እንደ ደካማ ጎን ይነሳበት እንጂ በክህሎት ጥሩ ደረጃ ላይ የሚቀመጥ ነው። በተለይም ቡድኑ ሊከተለው ካሰበው የኳስ ቁጥጥር ላይ ያመዘነ አቀራረብ አንፃር በድፍረት እንቅስቃሴን በቅብብል የማስጀመር ብቃቱ በቦታው ያለውን ፉክክር አሸንፎ በአሰላለፍ ውስጥ አብዝቶ መካተት ከቻለ ለብርቱካናማዎቹ ጥሩ ተስፋ እንደሚሆን የሚጠቁም ነው።

በጥቅሉ በዘጠኝ የፕሪሚየር ሊጉ ተሳትፎ ከወገብ በላይ ያለፈ ውጤት ማስመዝገብ ያልቻለው ድሬዳዋ ይህን በመሰለ ዝግጅት የዘንድሮውን የውድድር ዓመት የሚጀምር ይሆናል። የሊጉ የመጀመሪያ ፍልሚያውንም በመክፈቻው ዕለት ጥቅምት 07 ከወላይታ ድቻ ጋር ያደርጋል።

የድሬዳዋ ከተማ የ2014 ቡድን ስብስብ

ግብ ጠባቂዎች

27 ምንተስኖት የግሌ

30 ፍሬው ጌታሁን

32 ደረጄ ዓለሙ

33 አብዩ ካሣዬ

ተከላካዮች

2 እንየው ካሳሁን

3 ያሲን ጀማል

4 ሄኖክ ኢሳይያሳ

6 ዐወት ገብረሚካኤል

12 ሚኪያስ ካሳሁን

13 መሳይ ጳውሎስ

15 አውዱ ናፊዩ

20 አብዱለጢፍ መሀመድ

አማካዮች

5 ዳንኤል ደምሴ

8 ሱራፌል ጌታቸው

10 ዳንኤል ኃይሉ

14 ሙሉቀን አይዳኝ

16 ብሩክ ቃልቦሬ

21 መጣባቸው ሙሉ                        

23 ወንድወሰን ደረጄ

44 አቤል አሰበ

45 ሚካኤል ሳሙኤል

47 አብዱልፈታ ዓሊ

አጥቂዎች

7 ቢኒያም ፆመልሳን

9 ጋዲሳ መብራቴ

11 ሳሙኤል ዘሪሁን

17 አቤል ከበደ

18 አብዱርሀማን ሙባረክ

19 ሙኸዲን ሙሳ

22 ሄኖክ አየለ

25 ማማዱ ሲዲቤ


ማስታወሻ

አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ለፅሁፉ ግብዓት የሚሆኑ ምስሎችን ባነሳንበት ወቅት በአሰልጣኞች ስልጠና ላይ በመካፈል የነበሩ በመሆኑ በቡድን ፎቶ ላይ አለመካተታቸውን እንገልፃለን።