የክለቦች ቅድመ ውድድር ዝግጅት | አዲስ አበባ ከተማ

ከከፍተኛ ሊጉ የተመለሰውን የዋና ከተማዋን ክለብ ዝግጅት እና ቀጣይ መልክ እንዲህ ዳሰነዋል።


አዲስ አበባ ከተማ 2009 ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ፕሪምየር ሊጉ አድጎ በዛው ዓመት ወደ ከፍተኛ ሊግ ከተመለሰ በኋላ ዘንድሮ በድጋሚ በሀገሪቱ ቀዳሚ የሊግ እርከን እንመለከተዋለን። ዐምና በሦስት ምድቦች ተከፍሎ ሲከናወን በነበረው የከፍተኛ ሊጉ ውድድር ምድብ ለ ላይ ተደልድሎ የነበረው የሚዲናዋ ክለብ 51 ነጥቦችን በመሰብሰብ ሦስት ጨዋታዎች እየቀሩት ነበር የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን መቀላቀሉን ያረጋገጠው።

የ2009ኙን ታሪክ ላለመድገም እና በሊጉ ለመቆየት የሚጠብቀውን ፈተና ለመጋፈጥ በክረምቱ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ የከረመው አዲስ አበባ አጀማመሩ አነጋጋሪ ነበር። ሐምሌ ተገባዶ ነሐሴ እስኪገባ ድረስ ክለቡ በአሰልጣኝ ቡድን አባላቱም ሆነ በስብስቡ ላይ ምንም ዜናን ሳያሰማ መቆየቱ ከሌሎቹ ክለቦች የአካሄድ ፍጥነት አንፃር ትኩረትን የሚስብ ነበር። ከዝምታው ባሻገር የአሰልጣኙ እና የአንዳንድ ተጨዋቾች ውል እስከ ጥቅምት 30 ድረስ ብቻ የሚቆይ የመሆኑ ነገርም እንዲሁ አነጋጋሪ ነበር። አሁን ላይም ቢሆን ይህ ጉዳይ በተለይም ከአሰልጣኝ ቡድን አባላቱ አንፃር ሲታይ ግራ አጋቢ እንደሆነ የቀጠለ ነበር። ውድድሩ በሚጀምርበት ወር ላይ ኮንትራቱ በሚጠናቀቅ የአሰልጣኝ ቡድን ስብስብ ወደ ሊጉ መግባት ያለው እንድምታ ጥሩ አለመሆኑ የዋና አሰልጣኙም ሀሳብ ነው። ሁኔታው በቡድኑ ላይ ሥነ ልቦናዊ ጫና እንዳለው ይህንንም እስመልክቶ በተደጋጋሚ በቃል እና በፅሁፍ ጥያቄ ቢያቀርቡም ምላሽ አለማግኘታቸውን የሚገልፁት አሰልጣኝ እስማኤል አቡበከር ሀሳባቸውን ሲቀጥሉ “ማምጣት ያለባቸውን አሰልጣኝ ማምጣት ይችላሉ እኔም በዚህ አምናለሁ። ነገር ግን ሥራው እስኪበላሽ ድረስ መጠበቅ የለበት። ይህ ክለቡን የሚጎዳ ነው። ክለቡን አትመጥንም ከተባለ መጀመሪያ ነው ለመጪው ሰው መዘጋጀት ያለበት። ምክንያቱም ክለቡ 70-80 ሚሊየን ብር እያወጣ ውጤቱ ነው የሚበላሸው። ይህ ነገር እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ ያለበት አካል ጥንቃቄ ማድረግ አለበት። ብዙ የሰው ኃይል እና ገንዘብ የፈሰሰበት ተቋም ስለሆነ ነገሮች በአግባቡ መከወን አለባቸው።” ይላሉ።

አሁናዊ ሁናታው ይህ ሆኖ ሳለ በክረምቱ ወቅት ግን ለክለቡ መዘግየት ምክንያት ሆኖ የቀረበው የበጀት አለመፅደቅ ጉዳይ መፍትሄ አግኝቶ እንደ አዲስ ባዋቀረው ቦርድ ስር ሰፊ ምክክር ከተደረገ በኋላ ክለቡ ከአሰልጣኝ እስማኤል አቡበከር ጋር አብሮ እንደሚቀጥል ይፋ አድርጎ ነበር። ከእርሳቸው ጋርም በምክትል አሰልጣኝነት ደምሰው ፍቃዱ የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኙ መሠረት ወልደማርያም እንዲሁም የህክምና ባለሙያዎቹ በቀለ ዘነበ እና ነርስ ዳዊት ኢጃሮ ከቡድን መሪው ሲሳይ ተረፈ የአዲስ አባባ ከተማ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ሆነው እናገኛቸዋለን።

አዲስ አበባ ከዚህ ውጣ ውረድ በኋላ እጅግ ዘግይቶ ወደ ዝውውር ይግባ እንጂ ከተወዳዳሪ ክለቦች ሁሉ በርካታ ተጫዋቾችን በማስፈረም ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ከፍተኛውን ቁጥር አስመዝግቧል። ያም ሆኖ እንደአሰልጣኙ ሀሳብ ከሆነ የክለቡ እንቅስቃሴ መዘግየት በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ደረጃ እንደ ዕቅድ የያዟቸውን ተጫዋቾች እንደአዲስ ለማምጣትም ሆነ የነበሯቸውን ለማቆየት እንቅፋት መሆኑ ወደ ሦስተኛ አማራጮች ፊታቸውን በማዞር ነበር ማስፈረም የጀመሩት። ከዚህ ውስጥ አንድ የውጪ ዜጋ እና አንድ የፕሪምየር ሊግ ያለውን ጨምሮ ዘጠኝ ከከፍተኛ ሊግ ሲሆኑ ቀሪዎቹን ዐምና በሊጉ ሌሎች ክለቦች የተመለከትናቸው ተጫዋቾች ናቸው። ቡድኑን እንደ አዲስ ከተከላቀሉ ተጫዋቾች ውስጥ ግብ ጠባቂዎቹ ወንድወሰን ገረመው እና ዳንኤል ተሾመ ይገኙበታል። ሳሙኤል ተስፋዬ፣ ልመንህ ታደሰ፣ ያሬድ ሀሰን እና ቴዎድሮስ ሀሙ ደግሞ ለአዲስ አበባ ተከላካይ ክፍል አዳዲስ ስሞች ሆነዋል። አማካይ ክፍል ላይ ዋለልኝ ገብሬ፣ ኤልያስ አህመድ፣ ሙሉቀን አዲሱ፣ ጋብሬል አህመድ ፣ ፋይሰል ሙዘሚል እና ናይጄሪያዊው ቻርለስ ሪባኑ ተካተዋል። ሳዲቅ ተማም ፣ እንዳለ ከበደ ፣ ብሩክ ግርማ፣ ሪችሞንድ ኦዶንጎ እና በከፍተኛ ሊጉ 12 ግቦችን ያስቆጠረው ቢንያም ጌታቸውም የቡድኑ የፊት መስመር ፈራሚዎች ሆነዋል።

ይህን መሳይ የነበረው የክለቡ የግብይት ሒደት በአሰልጣኙ ሲመዘን አጥጋቢ የሚባል ዓይነት ነበር። “ነባር ተጨዋቾች አሉ። እነርሱ ላይ ልምድ ያላቸው፣ በሊጉ የተጫወቱ እና ወጣቶቹንም ይመሩልናል ያልናቸውን ተጫዋቾች ሰብስበናል። በየጨዋታ ክፍሉ ከዓምናው መቶ በመቶ ባይሆንም የተሻለ ለውጥ አለ ብዬ አስባለው።” ሲሉ አሰልጣኝ እስማኤል ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የክለቡ እንቅስቃሴ የነባሮቹን ተጫዋቾች ውል በማራዘም ጭምር የተከወነ ነበር። በዚህም መሰረት ግብ ጠባቂው ዋኬኒ አዱኛ፣ ተከላካዮቹ ነብዩ ዱላ፣ ሳሙኤል አስፈሪ፣ ዘሪሁን አንሼቦ፣ ሮቤል ግርማ እና አሰጋኸኝ ጴጥሮስ አማካዩ ብዙዓየሁ ሰይፉ እንዲሁም የመስመር አጥቂዎቹ ፍፁም ጥላሁን እና የሺዋስ በለው ዘንድሮም ከመዲናዋ ክለብ ጋር እንደሚቀጥሉ ታውቋል። በተጨማሪም ግብ ጠባቂው ኮክ ኩዌት ተከላካዮቹ ቦይ ጆን እና ኤልያስ ወዬሳ ፥ አማካዩ ሙከሪም ምዕራብ እና የመስመር አጥቂው ምንተስንኖት ዘካሪያስ ከ23 ዓመት በታች ቡድን የሚጫወቱ ሆነዋል።

አሰልጣኝ እስማኤል የቡድኑን ስብስብ ከሌሎች ክለቦች ጋር ሲያነፃፅሩ መለኪያቸው ያደረጉት የመጫወቻ ቦታ ንፃሬን ነው። “እኛ ሁሌ የምንመርጠው በቦታ ነው። ምርጫችን ተጫዋቾች በመጫወቻ ቦታቸው ላይ ያላቸውን ችሎታ እና አቅም ያገናዘበ በመሆኑ እንደውም ብዙ ጊዜ ይህ ነገር ለእኛ ይሳካልናል። ተጫዋቾቹ በከፍተኛ ሊጉ ሦስት እና አራት ዓመታትን የተጫወቱ እና ብዙ ልምድ ያላቸው ናቸው። ስለዚህ በመጫወቻ ቦታቸው ላይ የዳበሩ ናቸው። ለሊጉ አዲስ ቢሆኑም በቦታቸው ጥሩ አቅም ያላቸው ናቸው። ስለዚህ ኃላፊነታቸው ላይ ሲቀመጡ በቶሎ ይጣጣማሉ።”

ክለቦች በየዓመቱ ስብስባቸውን ከመቀየራቸው አንፃር በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ የተጫዋቾች በተለያዩ ቡድኖች ውስጥ ሲዘዋወሩ መታየት ሲነቀፍ ይሰማል። በሌላ በኩል ደግሞ የረጅም ጊዜ ልምድን ያካበቱ ተጫዋቾችን ይዞ መገኘት ቢያንስ በሊጉ ለመክረም ጠቃሚ መሆኑን የሚሞግቱም አይጠፉም። ከዚህ አንፃር አሰልጣኝ እስማኤል ቡድናቸው በዕድሜ ረገድ እንደማይታማ ይጠቁማሉ። “ያሉበት ዕድሜ ለእግርኳስ ጥሩ ዕድሜ ነው ብዬ ነው የማስበው። ሮጠው ያልጠገቡ ናቸው። ስለዚህ ዕድሉ ከተሰጣቸው እና ካነሳሷቸው የተሻሉ እንደሚሆኑ አስባለሁ። ከሀገርም አንፃር እንደልማት ሥራ ስናስበው አዳዲስ ፊቶች እንዲካተቱ ነው ያደረግነውም። ለምሳሌ የዴ ኤስ ቲቭ ምርጥ 11 በአመዛኙ ስማቸው በይፋ የማይታወቁ ተጫዋቾችን ነው ያወጣው፤ እንደ ረመዳን የሱፍ እና ቸርነት ጉግሳ ዓይነቶቹ። እኛም ጋር ወጣቶች እና ብዙ ጊዜ የማውቃቸው አቅማቸውንም ያሳያሉ ብዬ የማምነው ተጫዋቾች ናቸው። ከዛ አኳያ ጥሩ ይሆናሉ ብዬ አስባለሁ።”

የአዲስ አበባን ስብስብ በቅርብ ዓመታት ሊጉ ላይ በነበሩባቸው ክለቦች ከፈጠሩት ተፅዕኖ አንፃር ከሌሌች ክለቦች ፈራሚዎች ጋር ስናነፃፅረው ግን ደከም ብሎ እናገኘዋለን። ይህ ነጥብ ክለቡ ወደ ገበያ ሲወጣ ከመዘገይቱ ጋር የተገናኘ ነው ማለት ይቻላል። ያም ቢሆን ግን በሊጉ ውስጥ የሰፋ የተጨዋቾች ጥራት ልዩነት እንደሌለ አጥብቀው የሚያምኑት አሰልጣኙ “ጥራት” የሚለው አገላለፅ ላይ ያላቸው ዕምነት የተለየ መሆኑንም ያስረዳሉ። “እኛ ሀገር የተጫዋች ጥራት ደረጃ ላይ ደርሰናል ብዬ አላምንም። ከጥራት ይልቅ ብዛት ነው ያለው ለዛም ነው እንደሀገር ውጤታማ ያልሆነው። በራስ የመተማመን ጉዳይ ካልሆነ በቀር እንደውም እዚህ ያሉን ተጫዋቾች የተሻሉ ናቸው። ያ ደግሞ በጨዋታ ሂደት የሚመጣ ነው። አቅሙ እና ችሎታው አላቸው። ለምሳሌ ከሀምበርቾ ያመጣነው ቻርለስ በተከላካይ አማካይ ቦታ ላይ ጥሩ አቅም ያለው ተጭዋች ነው። ከብዙዎቹ ፕሪምየር ሊግ ላይ ካሉት የተሻለ ነው። ጥራት በሚባለው ደረጃ ላይ ግን የደረሰ ክለብ በሊጉ የለም። ለምሳሌ እኔ ትናንት ያሰለጠንኩት አቡበከር ናስር ነው ሊጉ ላይ መጥቶ 29 ግብ ያገባው። የትናንቱ ታዳጊ በዚህ ፍጥነት ይህንን ማድረጉ ለእኔ የሚያሳየኝ ሊጉ በጥራት በኩል ገና እንደሆነ ነው። ከውጪም ቢሆን ከፍ ያለ አቅም ያለው አሰልጣኝም ሆነ ተጫዋች ወደዚህ ሀገር አይመጣም። ጥራት ያለው ተጫዋች በክፍያ ደረጃም በጣም ብዙ ነው ወደዚህም መጥቶ ይጫወትም ወደተሻለ ሀገር ይሄዳል እንጂ። የእኛም ተጫዋቾች ጥራት አላቸው ተብሎ ከታሰበ ወደ ውጪ ወጥተው መጫወት አለባቸው። ነገር ግን ከጥራት ይልቅ ስም ነው ያላቸው።”

የአዲስ አበባ ከተማ የዝግጅት ጊዜ እንደ ዝውውር ሂደቱ ሁሉ ዘግይቶ መስከረም 4 ላይ የጀመረ ነበር። በወቅቱ መቀመጫውን በወወክማ በማድረግ ቢጀምርም ቦታው ለቡድኑ የተመቸ አልሆነም። “የአያያዝ ችግር ነበር፤ ፕሪምየር ሊግ ለሚጫወቱ ተጫዋቾች ቦታው አይመጥንም።” በሚል በአሰልጣኙ የተገለፀው ቦታ የአመጋገብ ፣ የመኝታ ፣ የውሀ እና የልብስ ማጠቢያ ክፍተት እንደነበረበት ተጠቁሟል። ሆኖም በጉዳዩ ላይ ግምገማ ከተደረገ በኋላ ስብስቡ መስከረም 12 ላይ በስፖርተኞች አያያዝ የተሻለ ልምድ ወዳለው ኢትዮጵያ ሆቴል አምርቷል። ሆቴሉ ለቡድኑ ተስማሚ የነበረ ቢሆንም ሌላው ችግር ደግሞ የልምምድ ቦታ ሆኗል። ቡድኑ ይዘጋጅ የነበረው በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የነበረ ሲሆን የአዲስ አበባ ዋንጫ በስታዲየሙ መጀመር በተለየም የአካል ብቃት ላይ በቀን ሁለቴ ልምምድ ለመሥራት ለነበረው ውጥን እንቅፋት ፈጥሮበታል። በመሆኑም ድግግሞሽ በሚፈልገው በአካል ብቃት ላይ ትኩረት ያደረገው ልምምዱን በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ለመቀጠል ተገዷል።

አዲስ አበባ ከተማ በሲቲ ካፕ ውድድር ላይ ተካፋይም ነበር። ከዝግጅት ጊዜው ማጠር አንፃር ቡድኑ ውድድሩ ላይ መካፈሉ አሰልጣኙን ያስደሰተ አልነበረም። ሆኖም ውድድሩ በአስተዳደሩ የተዘጋጀ በመሆኑ የከተማዋ ቡድን በሃያ ቀናት የቅድመ ውድድር ዝግጅት ሦስት ጨዋታዎችን እንዲያደርግ ሆኗል። ያም ቢሆን የዝግጅት ጊዜው አጭር ከመሆኑ አንፃር ውድድሩ ባይኖር ሌሎች የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን ማድረግ ሊያዳግት ይችል ስለነበር ክፍተቶቹን ለማየት ተሳትፎው ጥሩ ዕድል እንደሰጣቸው የአሰልጣኙም ዕምነት ነው። “በአስር ቀን ውስጥ ተጫዋቾችን መልምሎ የተወሰነ ልምምድ አድርጎ ወደ ውድድር መግባት በጣም ከባድ ነበር። ይሄ በራሱ ትልቅ ስኬት ነው ብዬ ነው የማስበው። ”

እንደምናስታውሰው ክለቡ ወደ ሊጉ ብቅ ባለበት የ2009 የውድድር ዓመት በአጨዋወት ደረጃ የኳስ ቁጥጥርን ቀዳሚ ከፍ ሲልም ብቸኛ ምርጫው ያደረገ ነበር። በሊጉ የመቆየት ዕድሉ በእንጥልጥል በነበራባቸው ጊዜያትም እንኳን በትዕግስት ኳስን ከራሱ ሜዳ ተቀባብሎ ለመውጣት የሚሞክር መልክ ነበረው። አዲስ አበባን ዘንድሮ በዚሁ መልክ መጠበቁ ግን የማይታሰብ ነው። የአሰልጣኙ አስተያየትም ሆነ በቅድመ ውድድር ጊዜ እንደተመለከትነው ቡድኑ በአመዛኙ በተጋጣሚ አጨዋወት ላይ የተመሰረተ አቀራረብ የሚኖረው ይመስላል። ኳስ ይዞ መጫወት በፍጥነት በቀጥተኛ መንገድ ጎል ላይ ከመድረስ ጋር የቀላቀለ ሒደትን የማስመልከት ዕድሉም የሰፋ ነው። እርግጥ ነው ይህ ሁኔታ 2009 ላይ በአጨዋወቱ ወጥነት በቀላሉ ተገማች ሆኖ የነበረበትን መንገድ ሊያስቀርለት ይችላል። የተሰማቸውን ፊት ለፊት በመናገር ለሚታወቁት እና በወቅቱ ለተወሰነ ጊዜ ከክለቡ ጋር ለነበሩት አሰልጣኝ እስማኤል ግን ሁኔታው ከአጨዋወት ተገጋችነት ጋር የተገናኘ አልነበረም። “2009 ላይ የነበረው ችግር በተወሰነ መልኩ አለ። ከዛ የሚለየው እነዚህ ተጨዋቾች ወጣቶች እና የነገ ሀገር ተረካቢዎች በመሆናቸው ነው። 2009 ላይ የነበሩት ተጫዋቾች አብዛኞቹ የሰለቻቸው እና በደላላ ገንዘብ ሰጥተው የገቡ ነበሩ። መጫወቱን ሳይሆን ገንዘቡን የሚፈልጉ ተጫውቾች ነበሩ። እኔ 2009 ሚያዚያ ላይ ቡድኑ ካበቃለት በኋላ ነበር የገባሁት። ይህንን ነው እንደችግርም ያየሁት።” ይላሉ።

አዲስ አበባን ከሌሎች ክለቦች የሊጉ ተሳታፊዎች የሚለየው ሌላኛው ጉዳይ የአሰልጣኙ የልምድ ሁኔታ ነው። ከተሳታፊ ክለቦች ውስጥ በውጪ አሰልጣኝ ከሚሰለጥነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ውጪ ለሊጉ አዲስ (በዋና አሰልጣኝነት) በሆኑ አሰልጣኝ ውድድሩን በመጀመር አዲስ አበባ ከተማ ብቸኛው ነው። ወጣት አሰልጣኞች ከስንት አንዴ ብቅ በሚሉበት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመዲናዋን ክለብ ይዘው የሚቀርቡት አሰልጣኝ እስማኤል ከዚህ ቀደም በሐረር ሲቲ ወጣት ቡድን ውስጥ የሰሩ ሲሆን በተቀሩት የሥልጠና ጊዜያቸው የአሁኑን ክለባቸውን በምክትልነት እና በዋና አሰልጣኝነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ነገር ግን በሊጉ አዲስ የሚሆኑ ብቸኛ የሀገር ውስጥ አሰልጣኝ መሆናቸው ምንም ተፅዕኖ አልፈጠረባቸውም። ይልቁኑም እስካሁን በሊጉ የነበረውን ልምድ ያላቸውን አሰልጣኞች የማስቀደም አካሄድ አምርረው ይተቻሉ። “በሊጉ ውስጥ ከ 20-30 ዓመት ተቆዩ አሰልጣኞች የዋንጫ ታሪክ የላቸውም። እኔ የማያቸው በባህር ውስጥ እንዳለ ድንጋይ ነው። ውሀ ውስጥ ስለቆየ ብቻ እንደ ዓሳ መዋኘት ይችላል ዓይነት ነው ሀሳቡ። ምክንያቱም ከልምዳቸው የሚወሰድ ትምህርት የለም። ከቅዱስ ጊዮርጊስ የውጪ አሰልጣኞች፣ ከአሰልጣኝ ገብረመድህን እና ከአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ በቀር በውጤት ረገድ የሚጠቀስ ነገር የለም። በልምድ የተሻለ መሆን በሥራ እና በውጤት መታየት አለበት። በሊጉ ዝም ብሎ መዞር ግን ዕድሜ ከመቁጠር ያለፈ ነገር የለውም። ልምድ ልምድ የሚሉትም ታዳጊውን አሰልጣኝ ለመምታት እና ለመኮርኮም መንገድ ለመፍጠር ነው።” ሲሉ ከልምድ ጋር የተያያዘ አተያያቸውን አጋርተዋል።

አዲስ አበባ ከተማ ተለዋዋጭ አቀራረብ ይዞ ይመጣል የሚለውን የአሰልጣኙን ሀሳብ ከስብስቡ አንፃር ስንመለከተው በሊጉ በሌሎች ክለቦች በኳስ ቁጥጥር አጨዋወት ትግበራ የሚታወቁት ጋብርኤል አህመድ ፣ ዋለልኝ ገብሬ እና ኤልያስ አህመድን መያዙ በዚህ አጨዋወት ለመታየት የሚረዳው ሆኖ እናገኘዋለን። የብዙአየሁ ሰይፉ በቡድኑ ውስጥ መቀጠልም በቅብብሎች ላይ ለተመሰረተ ዕቅድ ጥሩ ግብዓት ይሆናል። ከዚህ በተለየ ከፕሪምየር ሊጉ አንፃር ሲታይ ከአጨዋወት መንገድ ምርጫ ቅንጦት ይልቅ ውጤት ተኮር በሆነው የከፍተኛ ሊግ ውድድር ውስጥ ያለፉ ተጫዋቾች መበራከት ቡድኑን ለፈጣን እና ቀጥተኛ ጥቃት የሚሆን ባህሪ ያላብሰዋል። በዚህ ረገድ የሪችሞንድ ኦዶንጎ መካተትም በረጅም ኳሶች ወደ ግብ የመድረስ ሂደትን የሚያጠናክርለት ይሆናል።

በተናጠል የግል ብቃት በኩል በቅድሚያ አማካዩ ብዙአየሁ ሰይፉን እናገኛለን። ለሊጉ አዲስ የሆነው ተጫዋቹ ዓምና ግብ የሆኑ ኳሶችን በማመቻቸት እና ራሱም በማስቆጠር ያሳየውን ብቃት ዘንድሮ መድገም ከቻለ የዓይን ማረፊያ መሆኑ አይቀርም። ወደ ጅማ ሊያቀና ከጫፍ ደርሶ የተመለሰው ተከላካዩ እያሱ ለገሰም በዚሁ መንገድ የሚገለፅ ነው። ለተከታታይ ዓመታት በከፍተኛ ሊጉ ግቦችን እያስቆጠረ የመጣው ቢኒያም ጌታቸው ደግሞ ይህንን መንገድ በዋናው ሊግ ላይ በመድገም አንፀባርቆ የመታየት ዕድሉ ያለው አጥቂ ነው። ራሳቸውን በሚገባ ከማሳየት አኳያ በኢትዮጵያ ቡና በጥቂት ጨዋታዎች የተመለከትነው ፍፁም ጥላሁን እና የእምቅ ችሎታውን ያህል መድመቅ ያልቻለው ሳድቅ ተማም ዘንድሮ ራሳቸው አፎካክረው የሚምወጡበት አጋጣሚ ተከፍቶላቸል።

መዲናዋ ክለብ አጠቃላይ ስብስብ በሊጉ ልምድ ካላቸው ተጨዋቾች በተጨማሪ ከፍተኛ ሊግ ቀመስ የሆነ ስብስብ መያዙ በራሱ ከሚፈጥረው ስጋት ውጪ አዲስ ነገር የማሳየት ርሀብን አላብሶት ሊታይ ይችላል። ከቀናት በኋላ የሚጀምረው ውድድር ቡድኑን ከሁለቱ ሀሳቦች ወደ የትኛው አቅጣጫ ይዞት ይጓዛል የሚለውን ጉዳይ ማየት ስንጀምር በአንደኛው ሳምንት አዲስ አበባ ከተማ ጥቅምት 09 ከባህር ዳር ከተማ ጋር በመጫወት ጉዞውን ይጀምራል።


የአዲስ አበባ ከተማ የ2014 ስብስብ

ግብ ጠባቂዎች

1 ዋኬኔ አዱኛ

23 ወንድወሰን ገረመው

30 ዳንኤል ተሾመ

44 ኮክ ኮየት (U-23)

ተከላካዮች

2 ሳሙኤል አሰፈሪ

6 አሰጋኸኝ ጴጥሮስ

21 ሳሙኤል ተስፋዬ

22 እያሱ ለገሰ

17 ዘሪሀን አንሼቦ

15 ቴዎድሮስ ሀሞ

14 ልመንህ ታደሰ

19 ሮቤል ግርማ

16 ያሬድ ሀሰን

5 ነብዩ ዱላ (U-23)

33 በአይ ጆን (U-23)

36 ኤልያስ ወይሳ (U-23)

አማካዮች

20 ቻርለስ ሪባኑ

4 ጋብርኤል አህመድ

22 ሙሉቀን አዲሱ

24 ዋለልኝ ገብሬ

9 ኤልያስ አህመድ

27 ፋይሰል ሙዘሚል

8 ብዙአየሁ ሰይፉ

38 ሙከሪም ምዕራብ (U-23)

አጥቂዎች

13 ብሩክ ግርማ

10 ፍፁም ጥላሁን

7 እንዳለ ከበደ

12 ቢኒያም ጌታቸው

29 ሪችሞንድ ኦዶንጎ

3 ሳድቅ ተማም

11 የሸዋስ በለው (U-23)

36 ምንተስኖት ዘካሪያስ (U-23)


ማስታወሻ

አሰልጣኝ እስማኤል አቡበከር ለፅሁፉ ግብዓት የሚሆኑ ምስሎችን ባነሳንበት ወቅት በአሰልጣኞች ስልጠና ላይ በመካፈል የነበሩ በመሆኑ በቡድን ፎቶ ላይ አለመካተታቸውን እንገልፃለን።