የክለቦች የውድድር ዘመን ቅድመ ዳሰሳ | ሀዲያ ሆሳዕና

የሀዲያ ሆሳዕና የክረምቱ ዝግጅት ጊዜ እና በቀጣይ ይዞ የሚመጣውን አዲስ መልክ እንዲህ ተመልክተነዋል።


በ2008 ወደ ፕሪምየር ሊጉ መጥቶ በዛው የተሰናበተው ሀዲያ ሆሳዕና በተሰረዘው የ2012 የውድድር ዓመት ተመሳሳይ ዕጣ እንዳይደርስበት በሚያሰጋ ቁመና ሆኖ ላይ ነበር ውድድሩ በኮቪድ 19 ወረርሺኝ ምክንያት የተቋረጠው። ቡድኑን በአዲስ መልክ አዋቅሮ ወደ ውድድር በገባበት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ግን በአራት ተከታታይ ድሎች የጀመረ ጥሩ ዓመት ሊያሳልፍ በቅቷል። በ38 ነጥቦች አራተኛ ደረጃን ይዞ ለመጨረስ የቻለው ሀዲያ ሆሳዕና ዓመቱን በተረጋጋ የሜዳ ውጪ ሁኔታ ውስጥ ባያሳልፍም የሜዳ ላይ ውጤቱ እና ደረጃው ግን በጥቂቱ የተነቃነቀበት ጊዜ ባይጠፋም ጨርሶ ዝቅ ያለበት የውድድሩ ክፍል አልነበረም። በዚሁ ውድድር በክለቡ እና በተጨዋቾች መካከል የነበረው የደመወዝ አለመግባባት በተለያየ መልኩ ሲገለፅ ቆይቶ ውድድሩ ሊቋጭ አራት ሳምንታት ሲቀረው ፈንድቶ ታይቷል። በወቅቱ አስር ተጫዋቾችን ብቻ ይዞ ያለአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ሀዋሳ ከተማን የገጠመው የሆሳዕናው ቡድን በቀጣይ ሳምንታትም ዋና አሰልጣኙን እና በርካታ ቁልፍ ተጫዋቾቹን ሳይጠቀም ቀሪዎቹን ጨዋታዎች ለመጨረስ የተገደደበትን ጊዜ አሳልፏል።

ይህ የተጨዋቾቹ እና የክለቡ ውዝግብ ውድድሩ ከተጠናቀቀ በኋላም መቋጫ ሳያገኝ ወደ ፌዴሬሽኑ አምርቶ ተጫዋቾቹን ባለድል ያደረገ እና ሀዲያ ሆሳዕናን ወደ ዕግድ እንዲሄድ ያስገደደ ውሳኔን አስከትሏል። ከአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ጋርም የነበረው እሰጥ አገባ በተመሳሳይ ሁኔታ በፌዴሬሽኑ ፍርድ ሲያገኝ አሰልጣኙን አሸናፊ ያደረገ ሆኗል። ሂደቱ በዚሁ ቀጥሎ ለክለቡ የፋይናንስ ኃላፊ እስር እንዲሁም ለስራ አስኪያጁ ሥራ መልቀቅ መንስኤ እስከመሆን ደርሶ ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሀዲያ ሆሳዕና ሀሳቡን ወደቀጣዩ የውድድር ዓመት አዙሮ ወርሀ ሐምሌ እንደገባ በሀዋሳ ጥሩ ቡድን ሰርቶ ያሳየውን ወጣቱ አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረትን በዋና አሰልጣኝነት ሾሟል። በሂደት በተዋቀረው የቡድኑ የአሰልጣኞች ቡድን ውስጥም አሰልጣኝ ያሬድ ፈመቹ እና አሰልጣኝ መቅድም ገብረህይወዊት በአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት አቅራቢነት የክልቡ ረዳት አሰልጣኞች ሆነዋል። ከዚህ በተጨማሪ በሀዋሳ ከተማ ከአሰልጣኙ ጋር አብሮ የመሥራት አጋጣሚው የነበራቸው አሰልጣኝ ቅዱስ ዘሪሁን የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ በመሆን ወደ ክለቡ መጥቷል።

በክለቡ ውስጥ ከሆኑት ነገሮች አንፃር ሀዲያ ሆሳዕና በዝውውር መስኮቱ ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ አዲስ ቡድን የመገንባት ሥራ ይጠብቀው እንደነበር መገመት ቀላል ነው። ባሳለፍነው የውድድር ዓመት ከነበሩት ዋና ተጫዋቾች ውስጥ አምበሉ ሄኖክ አርፌጮ፣ ዑመድ ዑኩሪ፣ ተስፋዬ አለባቸው እና ሚካኤል ጆርጅን ውል ከማራዘሙ በዘለለ ክለቡ ከፍተኛ ዝውውር ከፈፀሙ የሊጉ ክለቦች ውስጥ አንዱ ሆኗል። ግብ ጠባቂ ቦታ ላይ በሀዋሳ ከተማ አራት ዓመታትን ያሳለፈው ቶጓዊው ሶሆሆ ሜንሳህ እና መሳይ አያኖ ወደ ሆሳዕና ሲመጡ መሀል ተከላካይ ቦታ ላይ ኤልያስ አታሮ፣ ፍሬዘር ካሳ እና መላኩ ወልዴ እንዲሁም በመስመር ተከላካይነት ብርሃኑ በቀለ እና ኢያሱ ታምሩ ሌሎች አዳዲስ ፈራሚዎች ሆነዋል። መሀል ክፍሉ ደግሞ ሳምሶን ጥላሁን፣ አበባየሁ ዮሐንስ፣ ኤፍሬም ዘካሪያስ እና ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃንን ሲያገኝ በፊት እና በመስመር አጥቂነት ባዬ ገዛኸኝ፣ ሀብታሙ ታደሠ፣ ፀጋዬ ብርሃኑ እና አስቻለው ግርማ ሌሎቹ የሀዲያ ሀሳዕና የቡድን አባላት ሆነዋል።

አዲሱ የሆሳዕና ስብስብ ሲታይ በልምድ ስብጥር እንዲሁም በተጫዋቾቹ ያለፈ ዓመት የተነጠል ብቃት መልካም የሚባል ዓይነት ነው። ነገር ግን ቁጥራቸው ብዙ መሆኑ እና ከሁሉም በላይ እንደቡድን ተጫዋቾቹን የማሰባጠሩ ጉዳይ ለአሰልጣኝ ቡድኑ ከባድ የቤት ሥራን የሚተው ይመስላል። ዋና አሰልጣኙ ይህ ጉዳይ በእርግጥም ወሳኝ መሆኑ የጠፋቸው አይመስልም። ” በእርግጥ እኔ ቡድኑን ስቀላቀል ከነባር ተጫዋቾች አራቱን ነው ያገኘሁት። አዲስ ቡድን ነው፤ የሰበሰብናቸውም ተጫዋቾች ፕሪምየር ሊጉ ላይ የነበሩ ናቸው እና እንደ አዲስ ቡድንነቱ ጊዜ ይፈልጋል። ያሉት ተጫዋቾች ደግሞ ልምድ ያላቸውም በፕሪምየር ሊጉ ላይም የታዩ ስለሆኑ ለቅንጅት ትንሽ ጊዜ ቢወስድም ግን ያን ያህል ከባድ ባይሆንም ብዙ ተጫዋች ማስፈረሙ በአንድ በኩል ጉዳት አለው። አማራጭም ስለሌለ እና ቡድኑ ባዶም ስለነበር በቂ ተጫዋቾችን አስፈርመናል።”

ሀዲያ ሆሳዕና አዲስ ቡድን ሲገነባ የወጣቶችንም አስፈላጊነት አልረሳም። ሁሉንም ክፍተቶቹን በዝውውሮች ብቻ በመሙላት በፋይናንሱ ረገድ ሌላ ፈተናን መጨመር እና የቡድን ግንባታውን ይበልጥ ከማክበድ ይልቅ 11 ወጣት ተጫዋቾችን ወደ ዋና ቡድኑ መቀላቀልን ምርጫው አድርጓል። ለዚህ ጉዳይ ስኬትም አምና ስድስተኛ ደረጃን ይዞ ባጠናቀቀው ቡድን ውስጥ በርከት ያሉ ወጣቶችን አብዝተው የተጠቀሙት የአሀኑ የሀዲያ ሆሳዕና ዋና አሰልጣኝ አቋም አጋዥ የሆነለት ይመስላል። “ወጣቶች ላይ መሥራት ከምንም ነገር በላይ የሚያስደስተኝ ነው። ሰፊ ዕቅድ ሲኖርህም ወጣቶች ላይ መስራትን ታስበዋለህ። አጋጣሚ ሆኖ ሀዲያ ሆሳዕና ላይም የነበሩ ወጣቶችን ስንይዝ የተሻሉ ተጫዋቾችም ናቸው። በዕቅዴ ስቀላቅላቸውም ብዙ ነገሮችን ዋጋ ከፍዬ ነው እና ዛሬ ወይም ሀዋሳ ከተማ ላይ የጀመርኩት ብቻ ሳይሆን ወደ ፊትም በወጣቶች ላይ የመስራት አላማም ስላለኝ ሀዲያ ሆሳዕና ውስጥም ያንን ደግሞ ማሳየት ነው የምፈልገው። ያሉት ተጫዋቾችም በብቃት ስለሚመጡ የተሻሉ ናቸው ብዬ ነው የማስበው እና አሁንም ወደፊትም ወጣቶች ላይ ትኩረት አድርጌ ነው የምሰራው። ”

በዚህም መሰረት ዓምና በተሳተፈበት ውድድር ጥሩ እንቅስቃሴ ካደረገው የ20 ዓመት በታች ቡድኑ ውስጥ ዋናው ቡድን በውዝግቡ ተጫዋቾችን ሲያጣ ምትክ የሆኑት ታዳጊዎች ዘንድሮ የዋናው ስብስብ አካል ሆነዋል። ከእነዚህ ውስጥ በወቅቱ ሁለት ግቦችን ያስቆጠረው እና ትኩረትን የሳበው ደስታ ዋሚሾ እንዲሁም በተመሳሳይ በሜዳ ላይ መልካም እንቅስቃሴ ያደረገው እንዳለ ዓባይነህ ይገኙበታል። ከእነርሱ በተጨማሪም ግብ ጠባቂው ያሬድ በቀለ፣ ተከላካዮቹ እሸቱ ግርማ፣ ቃለአብ ውብሸት፣ ካሌብ በየነ፣ ምንተስኖት አክሊሉ እና ማሞ ኃይሌ አማካዮቹ ክብርአብ ያሬድ፣ ተመስገን ብርሀኑ እና ቅዱስ ዮሃንስ በሀዲያ ሆሳዕና ቤት የእግር ኳስ ህይወታቸውን ለመፈንጠቅ ዕድሉን ያገኙ ሌሎቹ ወጣቶች ሆነዋል። ከእነዚህ መካከልም ኃይሌ እና ቅዱስ እንደ አዲስ ወደ ቡድኑ ሲያድጉ አምና ከነበሩት ውስጥ አምስቱ በአረንጓዴ ቴሴራ ቀሪዎቹ ስድስቱ ደግሞ በቢጫ ቴሴራ ቡድኑን ማገልገል ይቀጥላሉ።

 

ሀዲያ ሆሳዕና የዝግጅት ጊዜውን ነሐሴ 21 ሆሳዕና ላይ ነበር የጀመረው። በሒደትም ቀሪ የዝግጅት ጊዜውን ለማሳለፍ እና ጨዋታዎችን ለማድረግ በማሰብ ወደ ሀዋሳ ከተማ በማቅናት በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ ዝግጅቱን መከወን ቀጥሏል። የቡድኑን የዝግጅት ትኩረት በምንመለከት ጊዜ እምብዛም ያልተለመደ መልካም ነገር ሰምተናል። ይኸውም የውድድር ጊዜ ሲጀመር ትልቅ እንቅፋት የሚሆነው የተጫዋቾች የአካል ብቃት ተዛንፎ የመገኘቱ እና እሱን ለማስተካከል የሚፈጀው ረጅም ጊዜ በሀዲያ ሆሳዕና ውስጥ ያለመታየቱ ጉዳይ ነው። ይህን ነጥብ አስመልክተው ተጫዋቾች ከከዚህ ቀደሙ በተለየ ያለፈው የውድድር ዓመት ከተጠናቀቀ በኋላ በግላቸው ጥሩ ዝግጅት አድርገው መምጣታቸው ጫና እንዳቀለላቸው የገለፁት አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት በክረምቱ የዝግጅት ጊዜያቸው ቡድኑን በማቀናጀት እና ከኳስ ጋር በሚሰሩ ልምምዶች ላይ እንዳተኮሩ ነግረውናል።

በአዲሱ የውድድር ዓመት በሀዲያ ሆሳዕና ዘንድ ተስተካክሎ መቅረብ የሚገባው ዋነኛ ነገር ቢኖር ከሜዳ ውጪ ያለው አስተዳደራዊ ጉዳይ ነው። የአምናው ችግር ዳግም እንዳይከሰት ከወዲሁ የክለቡን የፋይናንስ አቅም የሚመጥኑ ዝውውሮች እና የጥቅማ ጥቅም ክፍያዎችን መወሰን ተገቢ ይሆናል። በዚህ ረገድ በአስተዳደሩ በኩል ከዚህ ቀደም ይነሱ የነበሩ ነገሮች አሁን ላይ አለመኖራቸውን ያነሱት አሰልጣኝ ሙሉጌታ አዲሱ ስብስብ እና የአሰልጣኝ ቡድን አባላቱ ይህንን ጉዳይ አጢነው መምጣታቸውን እስካሁንም ድረስ ያለው ነገር የተስተካከለ መሆኑን ነግረውናል።

በውጤት ደረጃ በሦስት ክለቦች ብቻ ተበልጦ ያጠናቀቀው ሀዲያ ሆሳዕና ዘንድሮም በፉክክሩ ውስጥ መቆየትን ማለሙ የሚቀር አይመስልም። አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረትም ከአዲሱ ክለባቸው ጋር ተመሳሳይ ህልምን ይዘዋል። “በእርግጥ አዲስ ቡድን ነው፤ ጊዜም ያስፈልጋል። እኔም ሊጉ ላይ ሁለተኛ ዓመቴ ቢሆንም ብዙ ችግሮች አይገጥሙኝም። ፉክክሩ ትንሽ ከበድ ቢልም ጥሩ ተፎካካሪ እሆናለሁ ብዬ አስባለሁ። ጠንካራ ቡድን እንደሚሆንም ጠብቁ።”

ከአጨዋወት አንፃር ስንመለከተው ደግሞ ቡድኑ ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል ደረጃ በስብስቡ ላይ ለውጥ ማድረጉ እና አዲስ አሰልጣኝ መሾሙ ሜዳ ላይ የተለየ ገፅታ ሊያላብሰው እንደሚችል ይታመናል። ዐምና በሊጉ ከፋሲል ከነማ ቀጥሎ ጥቂት ጎል ያስተናገደ ክለብ ሆኖ ሲያጠናቀቅ የነበረው ጠንካራ ጎኑ አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምኅረት በሀዋሳ ከተማ አንዳንድ ጨዋታ ላይ ካሳዩት ጥሩ የመከላከል አደረጃጀት አንፃር ስንመለከተው የመቀጠል አዝማሚያ ሊኖረው ይችላል። በተለይም በመሐል ተከላካይ ቦታ ላይ ከዚህ ቀደም በጅማ አብረው የተጫወቱት መላኩ ወልዴ እና ኤልያስ አታሮ ዓይነት ጥሩ ልምድ ያካበቱ ተጫዋቾችን የብቃት ዕድገት እያሳየ ካለው ፍሬዘር ካሳ ጋር የማጣመር አማራጩ በጠንካራ ጎን የሚታይ ነው። ክለቡ በተሳተፈበት የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ጨዋታዎች ላይም በመከላከሉ ረገድ መልካም ጅምር ላይ እንዳለ ፍንጭ በሚሰጥ መልኩ በአራት ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ብቻ ነበር መረቡ የተደፈረው። ከግለሰብ ብቃቶች ባለፈ የተሰላፊዎቹ ሜዳ የያካለል እና ክፍተቶችን የመድፍን ብቃት ከአማካይ መስመሩ ሽፋን የመስጠት አስተዋፅዖ ጋር ተደምሮ በቀላሉ ግብ እንዳያስተናግድ አግዞታል።

በማጥቃቱ ረገድ ሀዲያ ሆሳዕና ከቀደመው ጊዜ ከፍ ያለ በድፍረት ወደፊት የሚሄድ እና ለዚህም በዋነኝነት ሁለቱን መስመሮች ጥቅም ላይ የሚያውል ቡድን ሊወጣው ይችላል። በዚህም በወላይታ ድቻ ከመስመር በመነሳት ግቦችን ሲያስቆጥር የምናስታውሰው ፀጋዬ ብርሀኑ እንደተጫዋች ዕድገቱን የሚያስቀጥልበትን ዓመት ሊላሳልፍ ይችላል። በሌላኛው መስመር ታታሪው ሀብታሙ ታደሰ ለበድኑ የማጥቃት ሂደት ተጨማሪ ጉልበት የመሆን አቅም አለው። ሆሳዕና ሁለቱን መስመሮች አብዝቶ እንደሚጠቀም ለማሰብ ሌላኛው ፈራሚ አስቻለው ግርማን ማካተቱ ተጨማሪ ማስረጃ ይሆናል። ያም ቢሆን በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ላይ የቡድኑ የማጥቃት ልህቀት ገና ብዙ እንደሚቀረው ታይቷል።

አምና የነበረው ቡድን በርካታ ግቦችን አያስቆጥር እንጂ የግብ ምንጮቹ ሲታዩ የራሱ ጠንካራ ጎኖች ነበሩት። የተለያየ የጨዋታ ድርሻ ካላቸው ተጫዋቾች ግቦችን ማግኘቱ እንዲሁም ከጨዋታ ባለፈ ከቆሙ ኳሶች ኳስ እና መረብን ያገናኝ የነበረ መሆኑ በዚህ ረገድ ተጠቅሽ ነው። ከዚህ አንፃር ጥሩ የውድድር ዓመት ሊያሳልፍ ከሚችለው የኤፍሬም ዘካሪያስ እና ሳምሶን ጥላሁን ጥምረት የጨዋታ ፍሰቱን ከመምራት በላይ ይጠበቃል። ፊት መስመር ላይ ባለፈው ዓመት መገባደጃ ላይ የቡድኑ ተስፋ ሆኖ የፈነጠቀው ደስታ ዋሚሾ ዘንድሮ ዓይኖች ሁሉ ወደ እርሱ እንዲያተኩሩ የሚያደርግ ጊዜ ነበረው። በመሆኑም ከዓምናዎቹ ሦስት ግቦች በላይ ማስቆጠር ከወጣቱ ይጠበቃል። ከደስታ ውጪ ያሉት የቡድኑ የፊት መስመር ተሰላፊዎች ዑመድ ዑከሪ ፣ ሚካኤል ጆርጅ እና ባዬ ገዛኸኝ ደግሞ የሆሳዕና ሁነኛ የግብ ምንጭ የሚያደርጋቸው እና የወጥነት ጥያቄ የማያስነሳባቸው ዓመት ከፊታቸው ይጠበቃቸዋል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከወጣቱ አሰልጣኝ እና በዚህ መልኩ ከተገነባው ከአዲሱ ስብስቡ ጋር ወደ ውድድር ሲገባ ጥቅምት 10 ላይ የውድድሩ ቻምፒዮን ፋሲል ከነማን የሚገጥም ይሆናል።

የሀዲያ ሆሳዕና የ2010 ስብስብ


ግብ ጠባቂዎች

ሶሆሆ ሜንሳህ
መሳይ አያኖ
ያሬድ በቀለ

ተከላካዮች

ፍሬዘር ካሣ
ኤልያስ አታሮ
መላኩ ወልዴ
ሄኖክ አርፊጮ
ብርሃኑ በቀለ
ኢያሱ ታምሩ
እሸቱ ግርማ
ቃለአብ ውብሸት
ካሌብ በየነ

አማካዮች

ክብረአብ ያሬድ
እንዳለ ዓባይነህ
ኤፍሬም ዘካሪያስ
ሳምሶን ጥላሁን
ተስፋዬ አለባቸው
ቅዱስ ዮሐንስ
ምንተስኖት አካሉ
ፍቅረኢየሱስ ተወልደብርሃን
አበባየሁ ዮሐንስ

አጥቂዎች

ደስታ ዋሚሾ
ሚካኤል ጆርጅ
ሀብታሙ ታደሠ
ፀጋዬ ብርሃኑ
አስቻለው ግርማ
ባዬ ገዛኸኝ
ተመስገን ብርሃኑ
ዑመድ ኡኩሪ


ማስታወሻ

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምኅረት ለፅሁፉ ግብዓት የሚሆኑ ምስሎችን ባነሳንበት ወቅት በአሰልጣኞች ስልጠና ላይ በመካፈል የነበሩ በመሆኑ በቡድን ፎቶ ላይ አለመካተታቸውን እንገልፃለን።