ጥቂት ቀናት የቀሩት የዘንድሮው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ ሀዋሳ ከተማን የተመለከት የውድድር ዓመት ዳሰሳችንን እነሆ።
በቤትኪንግ በተሰየመው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ዓመት በቀድሞው ተጫዋቹ ሙሉጌታ ምህረት በመመራት ወደ ውድድር የገባው ሀዋሳ ከተማ ስድስተኛ ደረጃን ይዞ ነበር ያጠናቀቀው። በተከታታይ ሽንፈቶች የጀመረው የቡድኑ ጉዞ በቶሎ በማገገም ቀስ በቀስም ወጣ ገባ በሚል አቋም ቀጥሎ 35 ነጥቦችን በመሰብሰብ የተደመደመ ሆኗል። የውድድር ዓመቱን እጅግ በከፋ ሁኔታ የመውረድ ስጋት ሳይጋረጥበት እንዲሁም የጠራ የዋንጫ ተፎካካሪነት ፍልሚያ ውስጥ ሳይገባ የተረጋጋ የሚባል ጊዜ ነበር ያሳለፈው። ከውጤት ባሻገር ግን የሐይቆቹ ቡድን ወጣት ተጫዋቾች ረጅም የጨዋታ ደቂቃዎችን ያገኙበትን እንዲሁም ለመጪው የውድድር ዘመን ተስፋ ሆነው የታዩበት ጊዜም ነበር። ከእነዚህም ውስጥ የወንድምአገኝ ኃይሉ፣ ብሩክ በየነ፣ ዳዊት ታደሰ እና መስፍን ታፈሰ ነጥሮ መውጣት የክለቡ ያለፈው ዓመት ስኬት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው።
ሀዋሳ ከተማ ለሚመጣው የውድድር ጊዜ ከአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ጋር አብሮ እንደማይቀጥል ከታወቀ በኋላ በወርኃ ሐምሌ መግቢያ ላይ አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉን በሁለት ዓመት ውል በዋና አሰልጣኝነት ሾሟል። በምክትልነት ከክለቡ ጋር ለሁለት ዓመታት የቆየው ብርሀኑ ወርቁ ውል የታደሰ ሲሆን ተጨማሪ ረዳት አሰልጣኝ በመሆን የረጅም ጊዜ የተጫዋችነት ልምድ ያለው እና በአሰልጣኝነት ያለፉትን አራት ዓመታት ያሳለፈው ገረሱ ሸመና ወደ ክለቡ መጥቷል። ከዚህ በተጨማሪ የቀድሞው የግብ ዘብ አዳሙ ኑመሮ ደግሞ የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ ሆኖ ወደ ሀዋሳ ሲመጣ የህክምና ባለሙያው ሂርጳ ፋኖ እና የቡድን መሪው ብርሀኑ ኤጳሞ ዘንድሮም ከቡድኑ ጋር የሚቀጥሉ አባላት ናቸው።
ሀዋሳ የዝውውር መስኮት ተሳትፎው ክፍተቶቹን ከመሙላት አንፃር የተቃኙ ይመስላሉ። ከክለቡ ጋር ለአምስት ዓመታት የቆየው ቶጓዊው ግብ ጠባቂ ሶሆሆ ሜንሳህን በጋናዊው ግብ ጠባቂ መሀመድ ሙንታሪ ተክቷል። ተከላካይ መስመሩ ላይ ምኞት ደበበ ፣ ደስታ ዮሐንስ እና ብርሀኑ በቀለን ቢያጣም አሁንም በሀዲያ ሆሳዕና የነበሩት ፀጋሰው ድማሙ እና መድሀኔ ብርሀኔን እንዲሁም ተስፉ ኤልያስን ማምጣት ችሏል። አማካይ ክፍል ላይ ከክለቡ ጋር የተለያዩት ጋብርኤል አህመድ ፣ አለልኝ አዘነ እና ኤፍሬም ዘካሪያስ ክፍተት ደግሞ ኤርሚያስ በላይ፣ አብዱልባስጥ ከማል እና በቃሉ ገነነ ወደ ኃይቆቹ ቤት አምርተዋል። ከዚህ ውጪ የመስመር አጥቂው ብሩክ ኤልያስ ከዓምናው ባልተጓደለው የፊት መስመር ላይ ታክሏል።
አዲሱ የቡድኑ አለቃ አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ የቡድኑ የዝውውር ጊዜ ተሳትፎ የሚያስቡትን ዓይነት መልክ የያዘላቸው ይመስላል። “በየክለቡ ውል የጨረሱ የምፈልጋቸው ተጫዋቾች ወደ ሌሎች ክለቦች አምርተዋል። የመጡት ተጫዋቾች በአንድ ጊዜ ብቁ እንዲሆኑ አይጠበቅም። ለእነሱ ቡድኑ አዲስ ነው፤ እኔም አዲስ ነኝ እና ወደ ዋናው ቡድን ውስጥ ለመዋሀድ ብዙ ሥራ ይጠበቅባቸዋል። አሁን ደግሞ ጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ያሉት። ዐምና የነበረው ቡድንም በወጣት የተገነባ እና ጠንካራ ነበር። አሁንም ወጣቶች ጨምረን ነው እየገነባን ያለነው። በተለይ ምኞት ደበበ የቡድኑ ቋሚ ተሰላፊ ነበር በእርሱ ቦታ ላይ የሀዲያ ሆሳዕናውን ፀጋሰው ድማሙን ተክተናል። ሌሎች ቦታዎችም ላይ እንዲሁ እየተካን ነው። ጊዜ ቢያስፈልገውም ከጊዜ ጋር ጥሩ ቡድን ይሆናል ብዬ ነው የማስበው። ”
ከእነዚህ መተካካቶች ውጪ ቡድኑ ውላቸው ያለቁ እነደ ላውረንስ ላርቴ እና ዮሀንስ ሴጌቦ የመሳሰሉ ተጫዋቾችን ማቆየት ሲችል በማይታማበት የከዚህ ቀደም ልምዱ ዘንድንሮም አምስት ተጫዋቾችን ከ20 ዓመት በታች ቡድን አሳድጓል። በእዚህም የዘንድሮዎቹ ተረኞች የተካላካይ መስመር ተጫዋቾቹ ሚኪያስ ታምራት፣ ታምራት ተስፋዬ እና ፍቃደሥላሴ ደሳለኝ እንዲሁም አማካዮቹ ብሩክ ዓለማየሁ እና አስችሎም ኤልያስ ሆነዋል። ከሰባ እስከ ሰማንያ በመቶው ታዳጊ ላይ መሰረት አድርገው እየሰሩ እንደሆነ የሚናገሩት አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉም የዐምናዎቹ እና ዘንድሮ ወደ ቡድኑ ያደጉ ተጫዋቾች በውድድሩ መልካም ነገር እንደሚያሳዩ ዕምነታቸውን ጥለዋል። “ሀዋሳ ከተማ ታዳጊዎችን በብዛት የያዘ ቡድን ነው። እኔም እሱ ላይ ነው ትኩረት አድርጌ እየሰራሁ ያለሁት። በተመሳሳይ ከዚህ ቀደም ካሰለጠንኩት ከሲዳማ ቡና ጋር ተመሳሳይ ነገ ነው ያለው። ከታዳጊዎች ውስጥ ማንም የተቀነሰ ተጫዋች የለም ሁሉንም እያየን ነው። ብዙዎቹ አሁን ላይ እየተስተካከሉ ነው ማለት ይቻላል። እነሱ ላይ መስራት ለሀዋሳም ሆነ ለሀገር ትልቅ ጥቅም ስላለው እነሱ ላይ መሰረት አድርገን እየሰራን ነው። ” ብለዋል።
የአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ስብስብ በነሀሴ ወር አጋማሽ መቀመጫው በመሆነችው የሀዋሳ ከተማ የቅድመ ውድድር ዘመን ዝግጅቱን መስራት ጀምሯል። ክለቡ በሀዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ፣ በግብርና እና ደቡብ ክልል ሜዳዎች ላይ እያቀያየረ ሲሰራም ከርሟል። ዝግጅቱን የተጨዋቾችን ጥንካሬ እና ፅናት በሚያሻሽሉ ሥራዎች የጀመረው ሀዋሳ ቀስ በቀስ እንደየተጫዋቾቹ ሁኔታ ወደ ሌሎች የዝግጅት ክፍሎች አምርቷል። በዚህ ወቅትም ከሀዋሳ የከፍተኛ ሊግ ስብስብ እና ከድሬዳዋ ከተማ ጋር የዝግጅት ጨዋታዎችን አድርገዋል። ከዚህ በተጨማሪ የሀዋሳ ተወላጅ ከሆኑና ከብሪስቶል አካዳሚ እንዲሁም ከጎልደን ቡት አካዳሚ ከመጡ ወጣት አሰልጣኞች ጋርም በመሆን ሥልጠናዎች እንዲሰጡ ተደርጓል። የዝግጅት ጊዜያቸውን በውድድር ካዳበሩ ክለቦች ውስጥ የነበረው ሀዋሳ በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ላይ ተሳትፎ በሁለተኝነት አጠናቋል።
ጥሩ መሰረት ይዟል ተብሎ የሚታሰበው ሀዋሳ ከተማ ዓምና በተለይም ከበድ ካሉ ቡድኖች ጋር በቀላሉ ክፍተት የማይሰጥ አቀረረብ ይዞ ተመልክተነዋል። ከዛ ውጪ በቶሎ ግብ ላይ ለመድረስ ተነሳሽነቱ ያለው ለዚህም በዋነኝነት ሁለቱን መስመሮች የሚጠቀም ቡድን ነበር። አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉም በሲዳማ ከገነቡት ጠንካራ ቡድን ባህሪ ጋር ይህ የሀዋሳ የዓምናው አካሄድ ተመሳሳይነት ያለው በመሆኑ በአጨዋወቱ ላይ ስር ነቀል ለውጥ የሚያደርጉ አይመስሉም። ” ሙሉጌታ ምህረት ወጣት አሰልጣኝ ነው፤ በተመሳሳይ እኔም እንደዛው። የሚያመሳስለን ነገር አለ። አሁንም ኳስ ከኋላ መስርቶ ግን በፈጣን እንቅስቃሴ ጎል ጋር የሚደርስ፣ ከጎሉ በቶሎ ተጫውቶ የሚወጣ፣ ተቃራኒ ሜዳ ላይ መብዛት የሚችል እና አደጋ የሚፈጥር ውጤታማ የሆነ ቡድን ነው እየገነባን ያለነው።” ሲሉ በሀዋሳ የሚሰሩትን ቡድን ባህሪ ያብራራሉ።
በተለምዶው ወጣቶችን ልምድ ካላቸው ጋር መቀላቀል ጠንካራ ስብስብን ሲፈጥር ይታያል። ሀዋሳ የዚህ ሀሳብ ተቋዳሽ ለመሆን ጥሩ መስመር ላይ ያለ ይመስላል። እርግጥ ነው አመዛኞቹ ተጫዋቾች ወጣት የሚባሉ ቢሆንም ባለፉት ሁለት እና ሦስት የውድድር ዘመናት አድገው መጠነኛ ልምድ ያገኙም ያሉበት በመሆኑ መሀል ላይ ከሚረጋው የወትሮው ውጤቱ የዘለለ ደረጃን ይዞ እንዲጨርስ መጠበቁ አይቀርም። ይህ ሀሳብ የስፖርት ቤተሰቡ ብቻ ሳይሆን የአሰልጣኝ ዘርዓይም ይመስላል። “አምና ብቅ ያሉ ተጫዋቾች ነበሩ አሁንም ጎልተው የሚታዩት እነርሱ ናቸው። በቡድኑ ላይም ትልቅ ተነሳሽነት እና ፍላጎት አለ። ያ ነገር በመኖሩ በፍጥነት ወደምንፈልገው ነገር እንደሚመጡ ነው የማስበው። ባለፉት ሦስት ዓመታት የነበረውን የቡድኑን አማካይ ደረጃ ስንመለከት ወደ ስድስተኝነት የቀረበ ነው። በመሆኑም እኛ ከአንድ እስከ አራት ያለውን ደረጃ ይዘን ለመጨረስ ነው እንደዕቅድ የያዝነው። ያ ማለት ቻምፒዮን አንሆንም ማለት አይደለም። የምንሰራው ለእሱ ነው። ግን ዋና ዓላምው አምና ከነበረው ሪከርዶችን ማሻሻል ነው። ለምሳሌ ፋሲል ዋንጫ ሲያነሳ በመጀመሪያው ዓመት ሦስተኛ ነበር፤ መቐለም እንዲሁ አራተኛ ነበር። ብዙ ጊዜ አራት እና አምስተኛ ደረጃ ላይ የቆዩ ቡድኖች ቻምፒዮን ለመሆን ቅርብ ናቸው። ቀጣይ ቡድናቸውን አስተካክለው ስለሚመጡ ማለት ነው። እኛም በቀጣይ ሁለት ዓመታት ጠንክረን ሰርተን ሀዋሳን ወደሚታወቅበት ውጤታማነት ለማምጣት ነው ዕቅዳችን።”
በሀዋሳ ከተማ የ2013 የውድድር ዓመት እንደ አማካዩ ወንድምአገኝ ኃይሉ ጎልቶ የወጣ ተጫዋች ማግኘት ይከብዳል። ወደ ዋናው ቡድን ባደገበት ዓመት የመሀል ክፍሉ ቀዳሚ ተመራጮች ውስጥ መቀላቀሉ በራሱ ትልቅ ስኬት ሲሆን በየጨዋታዎቹ ላይ እየጎለበተ የሄደው በራስ መተማመኑ እና ተፅዕኖ ፈጣሪነቱ ድንቅ ነበር። ዘንድሮ ደግሞ ተጫዋቹ አምና ካስመዘገው የአምስት የግቦች ቀጥተኛ ተሳትፎ ላቅ ያለ ትገባራ ይጠበቅበታል። ይህንን ለማድረግ ግን ከአዲስ ፈራሚዎቹ አማካዮች ጋር በቶሎ መዋሀድ እና የግል ብቃቱን አሻሽሎ ዕድገቱን ማስቀጠል ይጠበቅበታል።
የሀዋሳ የአጥቂ መስመር ተሰላፊዎች በወጥነት መቀጠል ጥሩ ጎን ይኖረዋል። አምና በአንድነት 20 ግቦችን ያስገኘው የመስፍን ታፈሰ፣ ብሩክ በየነ እና ኤፍሬም አሻሞ የፊት መስመር ዘንድሮ ይበልጥ ጎልብቶ እንደሚታይ ይገመታል። እዚህ ላይ በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ጥሩ አቋምን ያስመልከተን ብሩክ ኤልያስ መጨመር የኤፍሬምን ልምድ በትኩስ ጉልበት ከማገዝ አንፃር የጎላ ሚና ይኖረዋል። የ2010 ከፍተኛ ሊግ ኮከብ ተጫዋቹ ብሩክ ኤልያስ የእግርኳስ ህይወቱን ዕድገት ለማስቀጠል ይህንን ዕድል በአግባቡ ከተጠቀመ በዘንድሮው ውድድር የመጉላት ዕድል ይኖረዋል።
ሀዋሳ ከተማ በኋላ መስመሩ ያካተትቸው ሁለቱ የውጪ ዜጎች ሳይነሱ አያልፉም። የተረጋጋው ግብ ጠባቂ መሐመድ መንታሪ መኖር ሀዋሳን ከኋላ ጠጣር እንደሚያደርገው ለመገንዘብ ተጫዋቹ ዓምና በሆሳዕና ያሳለፈውን ጊዜ ማስታወስ በቂ ነው። ነባሩ መሐል ተከላካይ ላውረንስ ላርቴም አጠቃላይ የመከላከል ሒደቱን የመምራት ብቃቱ ዘንድሮም እንደሚቀጥል ይጠበቃል። አጣማሪው ፀጋሰው ድማሙን ስንመለከት ደግሞ የባለ ልምዱን ምኞት ደበበን ቦታ በመሸፈን ረገድ ባለው ክህሎት ጥሩ ምርጫ ሆኖ እናገኘዋለን። ዐምና በሆሳዕና የመጨረሻ ጨዋታዎች ላይ ብቻ ጎልቶ መውጣቱን አሁን ሙሉ የውድድር ጊዜው ላይ ብቃቱን በማስየት ማስመስከር ግን ከግዙፉ ተከላካይ ይጠበቃል። ደስታ ዮሐንስ፣ ብርሀኑ በቀለ እና ዘነበ ከድርን ባጣው የመስመር ተከላካይ ቦታ ላይ ዮሐንስ ሱጌቦ ዘንድሮ ቁጥር አንድ ምርጫ መሆኑን ማስመስከር የግድ ሲለው የመድሀኔ ብርሀኔ እና ተስፉ ኤልያስ መምጣትም ለአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ አማራጮችን እንደሚያበራክትላቸው ይጠበቃል።
የሁለት ጊዜ የሊጉ ቻምፒዮኑ ሀዋሳ ከተማ ይህን መሳይ ከሆነው ስብስቡ ጋር የ2014 የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግን ጥቅምት 7 እንደ 2010ሩ ሁሉ በውድድሩ መክፈቻው ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋርን በመግጠም ይጀምራል።
የሀዋሳ ከተማ ሙሉ ስብስብ
ግብ ጠባቂዎች
30 አላዛር ማርቆስ
31 ዳግም ተፈራ
51 ምንተስኖት ጊንቦ
77 መሐመድ ሙንታሪ
ተከላካዮች
4 ፀጋአብ ዮሐንስ
6 አዲስዓለም ተስፋዬ
7 ዳንኤል ደርቤ (አምበል)
13 ታምራት ተስፋዬ (U-23)
14 መድሃኔ ብርሃኔ
15 አቤኔዘር ዮሐንስ
16 ወንድማገኝ ማዕረግ
19 ዮሐንስ ሱጌቦ
26 ላውረንስ ላርቴ
28 ተስፉ ኤልያስ
ፍቃደስላሴ ደሳለኝ (U-23)
ሚኪያስ ታምራት (U-23)
አማካይ
8 በቃሉ ገነነ
13 አብዱልባሲጥ ከማል
18 ዳዊት ታደሠ
22 ኤርሚያስ በላይ
23 ብሩክ ዓለማየሁ (U-23)
25 ሔኖክ ደልቢ
27 አስችሎም ኤልያስ (U-23)
29 ወንድማገኝ ኃይሉ
አጥቂ
9 ሀብታሙ መኮንን
10 መስፍን ታፈሠ
11 ቸርነት አውሽ
12 ብሩክ ኤልያስ
17 ብሩክ በየነ
20 ተባረክ ሄፋሞ
21 ኤፍሬም አሻሞ
27 ምንተስኖት እንድሪያስ
ማስታወሻ
አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ለፅሁፉ ግብዓት የሚሆኑ ምስሎችን ባነሳንበት ወቅት በአሰልጣኞች ስልጠና ላይ በመካፈል የነበሩ በመሆኑ በቡድን ፎቶ ላይ አለመካተታቸውን እንገልፃለን።