በቀጣይ ዓመት ለሚደረገው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የምድብ ፍልሚያዎችን እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በደቡብ አፍሪካ አቻው ተረቶ ከማጣሪያው ምድብ መውደቁ ተረጋግጧል።
አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከሦስት ቀናት በፊት ባህር ዳር ላይ በደቡብ አፍሪካ 3-1 ከተሸነፈው የመጀመሪያ አሰላለፍ ሦስት ለውጦችን አድርገው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በለውጦቹም ሱሌይማን ሀሚድ አስራት ቱንጆን፣ አማኑኤል ዮሐንስ ይሁን እንደሻውን እንዲሁም መስዑድ መሐመድ ሽመልስ በቀለን ተክተው ጨዋታውን ቀርበዋል።
በዋልያዎቹ የተረጋጋ የኳስ ማንሸራሸር ሂደት የጀመረው ጨዋታ ቀስ በቀስ የባፋና በፋናዎቹን ጫና የመፍጠር ባህሪ ማሳየት ጀምሯል። በአቡበከር ናስር በኩል ያጋደለ ጥቃት ለማድረስ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ኢትዮጵያውያኑ የማጥቃት ሂደታቸው ወደ ሙከራዎች መለወጥ ሳይጀምር ግብ አስተናግደዋል። 11ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ ቪክቶር ሌስዋሎ በግንባሩ ሲገጭ ኳስ ወጥቶ ለማዳን ጥረት ላይ የነበረው ፋሲል ገብረሚካኤልን አልፋ ወደ ግቡ አቅጣጫ ስታመራ ጌታነህ ከበደ ለማዳን ያደረገው ጥረት ሳይሳካ በራሱ ላይ አስቆጥሯል።
17ኛው ደቂቃ ላይ መስዑድ መሐመድ ከግራ መስመር የደረሰውን ኳስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት ቡድኑን አቻ ለማድረግ በመጣር የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ሙከራ ሰንዝሯል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ቡድኑ እጅግ በጥሩ የአንድ ሁለት ቅብብል ሳጥን ውስጥ ገብቶ ያለቀለት አጋጣሚ አግኝቶ ነበር። በዚህም አቡበከር ናስር ከተከላካዮች ጋር ታግሎ ለጌታነህ ያቀበለውን ኳስ አምበሉ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
አሁንም በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ የተሻሉት ዋልያዎቹ በ25ኛው ደቂቃም ሌላ አስቆጪ ዕድል አምክነዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም አቡበከር ናስር ከግራ መስመር እየገፋ የሄደውን ኳስ ለመሐል አጥቂው በድጋሜ ቢያቀብለውም ጌታነህ ሰውነቱን አዙሮ ወደ ግብ የመታው ኳስ የግቡን ቋሚ ታኮ ወደ ውጪ ወጥቷል።
ቀጥተኛ አጨዋወት በሜዳ ላይ ሲከተሉ የነበሩት ደቡብ አፍሪካዎች በ29ኛው ደቂቃ መሪነታቸውን ከፍ ለማድረግ ጥረዋል። በዚህም በፈጣን የመልሶ ማጣቃት በዕለቱ የዋልያው ክፍተት የነበረውን የግራ መስመር ቦታ በማጥቃት የተገኘውን ኳስ ወደ ሳጥን በመላክ አደገኛ ጥቃት ሰንዝረዋል። ነገርግን ቪክቶር ሌስዋሎ ከቀኝ መስመር ኳስ እንደደረሰው በአንድ ንክኪ ወደ ግብ ቢመታውም ዒላማውን ስቶ ወደ ላይ ወጥቶበታል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አምስት ደቂቃዎች ሲቀሩት ደግሞ ጨዋታው ሁለተኛ ግብ ሊያስተናግድ ነበር። ገና በጊዜ ግብ ያስተናገዱት ኢትዮጵያዎች ሱራፌል ዳኛቸው ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመታው ኳስ አቻ ሊሆኑ ቢዳዱም የባፋና ባፋናው አምበል እና የግብ ዘብ ሮንዊን ዊልያምስ አምክኖታል። አጋማሹም ጌታነህ ከበደ በራሱ መረብ ላይ ናስቆጠረው ኳስ ደቡብ አፍሪካን መሪ አድርጎ ተጠናቋል።
በመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች መሪ የሆኑት ደቡብ አፍሪካዎች በዚህኛውም ግማሽ በቶሎ መሪነታቸውን ለማስፋት ተንቀሳቅሰዋል። በቅድሚያም በ52ኛው ደቂቃ ንጃቡሎ ንግኮቦ ከርቀት አክርሮ ሲመታ ኢቪደንስ ማክጎባ ደግሞ በ56ኛው ደቂቃ ግብ ጠባቂ አልፎ ሌላ ሙከራ አድርጓል። በተለይ ቴቦሆ ሞክዌና ለማክጎባ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ማክጎባ ግብ ጠባቂው ፋሲልን አልፎ የመታውን ኳስ ሱሌይማን ከመስመር ላይ ከግብነት አግዷታል።
ከሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ አስራ አምስት ደቂቃዎች በኋላ ሱራፌልን በሽመለስ እንዲሁም ሱሌይማንን በአስራት የተኩት አሠልጣኝ ውበቱ በአንፃራዊነት ወደ ፊት ለመሄድ ቡድናቸው ጥሯል። ይህ ቢሆንም ግን እንደ መጀመሪያው አጋማሽ የጠሩ የግብ ዕድሎችን እስከ 66ኛው ደቂቃ ድረስ አልፈጠሩም ነበር። በዚህ ደቂቃም ጌታነህ ከበደ ከርቀት አክርሮ ኳስ መትቶ ዒላማውን ስቶ ወጥቶበታል። በ80ኛው ደቂቃ የጌታነህ ከበደ ተቀይሮ መውጣትን ተከትሎ የመሐል አጥቂ የሆነው አቡበከር ግብ ጠባቂው ዊልያምስ በረጅሙ ሊመታ ያሰበውን ኳስ ተደርቦ መረብ ላይ ለማሳረፍ ጥሮ ነበር። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ አስራት ከቀኝ መስመር ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ አቤል ያለው አግኝቶት በግማሽ የመቀስ ምት ሞክሮት ወጥቶበታል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች በቀሪዎቹ ደቂቃዎች እንደ ተለመደው ኳሱን ይዘው ቢጫወቱም ኳስ እና መረብን ማገናኘት ሳይችሉ ሦስት ነጥብ አስረክበው ከሜዳ ወጥተዋል።
ውጤቱን ተከትሎ የሁጎ ብሩሱ ደቡብ አፍሪካ ነጥቡን 10 በማድረስ የምድቡ መሪ ሆኗል። በባፋና ባፋና የተረታው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደግሞ ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ቢኖሩም እስካሁን በአራት ጨዋታዎች 3 ነጥቦችን ብቻ በመሰብሰቡ ወደ ኳታሩ የዓለም ዋንጫ የማለፉን ተስፋ አጨልሞ ከሜዳው ወጥቷል።