የክለቦች የቅድመ ውድድር ዘመን ዳሰሳችንን በመቀጠል የጣና ሞገዶቹን የተመለከተው ፅሁፍ ላይ ደርሰናል።
2011 ላይ ሊጉን የተቀላቀሉት ባህር ዳር ከተማዎች የመጀመሪያ ዓመታቸውን በሰንጠረዡ ወገብ ላይ ነበር የጨረሱት። ጥሩ መፎካከር የጀመሩበት የ2012 ውድድር እስኪቋረጥ ድረስም በላይኛው ፍልሚያ ውስጥ ከነበሩ ክለቦች መካከል ይገኙ ነበር። በድጋሚ ከአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ጋር ጀምረው የጨረሱት የዓምናው የውድድር ዘመን ደግሞ እንደ መጀመሪያው ሁሉ መሀል ላይ ማጠናቀቅ ችለዋል። በአመዛኙ ወጣ ገባ የነበረው የባህር ዳር የአምናው ጉዞ በ 33 ነጥቦች በሰባተኛ ደረጃ ላይ የተደመደመ ነበር። ዘንድሮ ደግሞ ክለቡ አዲስ አሰልጣኝ በመቅጠር እና በስብስቡ ላይ ማሻሸያዎች በማድረግ የሊጉን መጀመር በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።
ባህር ዳር ከተማ ከአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ጋር አብሮ እንደማይቀጥል ከታወቀ በኋላ የአሰልጣኝ ቡድን አባላቱን በአዲስ መልክ አደራጅቷል። በቅድሚያም አምና በሰበታ የነበሩትን አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱን በዋና አሰልጣኝነት ሾሟል። በምክትልነት ደግሞ ከነባሩ አሰልጣኝ አብርሀም መላኩ በተጨማሪ ቡድኑን በአምበልነት እየመራ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ያሳደገው ደረጄ መንግሥቱ ተሹሟል። ክለቡ በተጫዋችነት ቀሪ የአንድ ዓመት ውል የነበረው ደረጄን ወደ ምክትልነት ከማምጣቱ በተጨማሪ የግብ ጠባቂዎች አሠልጣኝ አሻግሬ አድማሱን በአዲሱ የአሠልጣኝ ቡድን ውስጥ አስቀጥሏል። በጣና ሞገዶቹ ቤት በተለየ ሁኔታ የሥነ ምግብ ባለሙያም ተመድቧል። ይህንን ኃላፊነት የሚወጡት ከዚህ ቀደም ለ2013 የአፍሪካ ዋንጫ ያለፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ የሠሩት ዶ/ር ተስፋዬ ብርሀኔ ሲሆኑ ኢሳይያስ ማሞ የህክምና በላሙያ፣ ሄኖክ ሀብቴ የቡድን መሪ፣ መብራቱ ሀብቱ ደግሞ የቴክኒክ ዳይሪክተርነት ሚናን ይወጣሉ።
ባህር ዳር ከተማ በዝውውር መስኮቱ ጥራት ያላቸው ዝውውርችን ከፈፀሙ ክለቦች መካከል ይገኝበታል። ከሒደቱ ዋና ትኩረቶች መካከል ቅድሚያውን የሚወስደው ደግሞ የግብ ጠባቂ ክፍሉ ነበር። ከሦስቱ የግብ ዘቦቹ ሀሪስተን ሄሱ፣ ጽዮን መርዕድ እና ሥነጊዮርጊስ እሸቱ ጋር በመለያየቱ አዲስ ስብጥር መፍጠር ይጠበቅበት ነበር። በመሆኑም አብበከር ኑሪ፣ ፋሲል ገብረሚካኤል እና ይገርማል መኳንንትን ወደ ስብስቡ አካቷል። በተለይም አቡበከር እና ፋሲል በ2013ቱ ውድድር በጅማ አባ ጅፋር እና ሰበታ ከተማ የነበራቸው ውጤታማ ቆይታ የጣና ሞገዶቹ በሁለቱ ብረቶች መሀል የሚያቆሙትን ተጫዋች የመወሰን ምርጫቸው ከፍ ያለ መሆኑን ይነግረናል።
ሌላኛው መልኩን ለውጦ የሚመጣው የቡድኑ ክፍል የፊት መስመሩ ነው። አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በመሐል እና በመስመር አጥቂነት እንደአስፈላጊነቱ ይጠቀሙባቸው የነበሩት ወሰኑ ዓሊ፣ ባዬ ገዛኸኝ እና ምንይሉ ወንድሙ አሁን በስብስቡ ውስጥ አይገኙም። በእነርሱ ምትክ ባህር ዳር የደረሱት አጥቂዎች ኦሴ ማውሊ፣ ዓሊ ሱሌይማን እና ተመስገን ደረሰ ሆነዋል። እዚህ ጋርም የቡድኑ የዓምና ደካማ ጎን የአጥቂ መስመሩ ከመሆኑ አንፃር በቦታው ላይ ትኩረት መደረጉን ጥሩ እርምጃ ሆኖ እናገኘዋለን። እንደ ግብ ጠባቂዎቹ ሁሉ ከጅማ እና ሰበታ የመጡት ተመስገን እና ማዎሊ የሳለፍነው ዓመት ብቃት ይደገማል ተብሎ ከታሰበ አሰልጣኝ አብርሀም በርከት ያሉ ግቦችን ከተጫዋቾቹ ይጠብቃሉ። ኤርትራዊው ዓሊ ሱለይማን ደግሞ በክረምቱ በነበረው የሴካፋ ውድድር ላይ ያሳየውን ብቃት በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ መክፈቻ ላይ መድገሙ ለጣና ሞገዶቹ ትልቅ ተስፋን ይዞ የሚመጣ ነው።
በዋነኝነት ሳምሶን ጥላሁንን ያጣው የባህር ዳር ከተማ አማካይ ክፍል አለልኝ አዘነ፣ መሳይ አገኘሁ (በተጨማሪ ተከላካይ)፣ ፉዐድ ፈረጃ፣ አብዱልከሪም ንኪማ እና ኃይማኖት ወርቁን አግኝቷል። ፉዓድ፣ መሳይ እና አለልኝ በሰበታ ከተማ፣ ወላይታ ድቻ እና ሀዋሳ ከተማ ቀዳሚ አሰላለፍ ውስጥ ደጋግመው የተካተቱ ተጫዋቾች መሆናቸው አይዘነጋም። በዚህ ላይ ብሩኩናፏሳዊው ኒኪማ እና ኃይማኖት አሁንም በስብስቡ ውስጥ ከሚገኙ እንደ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ፣ አፈወርቅ ኃይሉ፣ ፍፁም ዓለሙ ያሉ ተጫዋቾች ጋር ሲደመሩ መሐል ክፍሉ በበርካታ አማራጮች የተሞላ ሆኖ እናገኘዋለን።
ይህ የአማራጮች መስፋት በተለይም የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ለመጎናፀፍ እንዲሁም ከፊት ጨራሽ አጥቂዎችን እንደ አስፈላጊነቱ ለመጠቀም የራሱን ዕድል ይዞ ይመጣል። አሰልጣኝ አብርሀም እነዚህን የስብስቡን ጠንካራ ክፍሎች ከሊጉ ርዝመት እና ሊገነቡት ከሚያስቡት ቡድን ባህሪ ጋር ያገናኙታል። “ሊጉ ለእኔ ማራቶን ነው። ሁለት ሦስት ጨዋታ አድርገህ የምታቆመው ሳይሆን ለረጅም ጊዜ የሚካሄድ ነው። ስለዚህ በየቦታው ጥራት ያላቸው በርከት ያሉ ተጫዋቾችን መያዝ የቡድን ስብስብ አስተዳደር ጥሩ እስከሆነ ድረስ የተፈለገውን ዓይነት ቅርፅ መሀል ላይም ሆነ ፊት ላይ ጥቅም ላይ ቢውል ትልቁ ነገር ተጫዋቾቹን በአግባቡ በአስፈላጊው ጊዜ መጠቀሙ ላይ ነው። ስለዚህ እነዚህ ተጫዋቾች ካላቸው ጥራት አንፃር መሀል እና ፊት ላይ መብዛታቸው ቡድኑን ያግዘዋል። ዞሮ ዞሮ ግን እንደጨዋታው ክብደት እና ቅለት የተለያየ ቅርፅ ያለው ቡድን ይዞ መቅረብ አይደለም የምፈልገው። አንድ ወጥ የሆነ ጥሩ ቅርፅ ያለው ቡድን ይዘን ለመቅረብ ነው የምንፈልገው። ሁሉም ግን ቡድኑ ባለው የአጨዋወት ሀሳብ ከፍተኛ ተሳታፊ እንዲሆኑ እናደርጋለን።” ሲሉም ሀሳባቸውን ያስቀምጣሉ።
ሁለቱን የመስመር ተከላካዮች ሚኪያስ ግርማ እና ሳሙኤል ተስፋዬን ያጣው እንዲሁም በሰለሞን ወዴሳ እና መናፍ ዐወል ጥምረት ላይ የተገደበው የባህር ዳር የኋላ መስመር የዝውውሩ ዋና ትኩረት ሳይሆን መቅረቱ ግን አስገራሚ ነው። በመስመር ተከላካይነት እንደ ግርማ ዲሳሳ እና አዲስ ፈራሚው መሳይ አገኘሁ ዓይነት ሁለት ሚና የሚወጡ ተጫዋቾችን የመጠቀም አማራጭ ሲኖር ክለቡ በመሐል ተከላካይ ቦታ ላይ ፈቱዲን ጀማልን ብቻ ማስፈረሙ አማራጮቹን ውስን ያደርግበታል። አሰልጣኙም በአጥቂ እና በአማካይ ክፍላቸው ላይ ያላቸው የምርጫ ቅንጦት እዚህ ቦታ ላይ እንደማይኖራቸው አውቀዋል። የሚኖረውን ክፍተት ለመሸፈንም የነባር ተጫዋቾችን ብቃት ተስፋ ያደርጋሉ። ” በዝውውሩ ሁሉ ነገር ጥሩ ነው። መጠነኛ የሆነ የተከላካይ ክፍል ላይ የነበረን ዝውውር መቶ በመቶ የተሳካ ነው ባንልም ሌሎቹ ላይ ያደረግናቸው ዝውውሮች እና በክለቡ ውስጥ የቀሩ ተጫዋቾች የምንፈልገውን ነገር ለማሳካት ያግዙናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። በተቻለ መጠን ያሉትን ተጨዋቾች በአግባቡ በመጠቀም ችግራችንን ለመቅረፍ እንሞክራለን። በቅድመ ዝግጅት ውድድር ላይም በፊት የነበሩ ጥቃቅን ስህተቶች እየታረሙ ነው። ይህንኑ ለማጎልበት እንሄዳለን። በሥራችን ሂደት ውስጥ ተከላካይ ክፍሉ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ ጥረት እናደርጋለን።” በማለትም የቦታውን የዝውውር ሂደት የገመገሙበትን ሀሳብ ይሰጣሉ።
“ሁሌም እንደምለው አቅሙ እና ችሎታው እስካላቸው ድረስ ዕድሜ ሊገድባቸው አይገባም። ስለዚህ ለሊጉ የሚመጥን ጠንካራ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ወጣቶች እስካሉ ድረስ ለእነሱ ዕድል በመስጠት የምንቀጥል ይሆናል።” የሚል አመለካከት እንዳላቸው በሚገልፁት ዋና አሰልጣኙ የሚመራው ባህር ዳር ከተማ ዘንድሮ ግብ ጠባቂው ናትናኤል በልእስቲ፣ ተከላካዮቹ ብሩክ ያለው እና ፍፁም ፍትሕአለው፣ አማካዩ ኃይለሚካኤል ከተማው እና አጥቂው ኪዳነማርያም ተስፋዬን በቢጫ ቴሴራ በስብስባቸው አካተዋል።
ባህር ዳር ከተማዎች የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን በመቀመጫ ከተማቸው ነበር ያደረጉት። ነሐሴ 22 እና 23 ህክምና ምርመራ በማድረግ ከነሀሴ 24 ጀምሮ ወደ ዝግጅት ገብተዋል። በሦስት በተከፈለው የዝግጅት መርሐ ግብራቸውም በአጠቃላይ የአካል ብቃት ደረጃን ማሻሻል ላይ በመቀጠል ደግሞ ከኳስ ጋር በሚደረጉ ልምምዶች ውስጥ አልፈዋል። በሦስተኝነት የተቀመጠው የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች ዕቅዳቸውንም ያሳኩት ወደ መዲናዋ በማቅናት ከመስከረም 15 ጀምሮ በተከናወነው የአዲስ አበባ ዋንጫ ውድድር ላይ በመካፈል ነበር። በውድድሩ አምስት ጨዋታዎችን በማድረግ ራሳቸውን ሲፈትሹ እስከፍፃሜው ተጉዘው በከተማቸው በተደረገው የመጨረሻ ጨዋታ መከላከያን አሸንፈው ዋንጫዋን አንስተዋል።
በዝግጅት ወቅት የሚደረጉ ውድድሮችን ማሸነፍ አቋምን ከመለካት ባለፈ በዋናው ውድድር ተጠባቂነትን ይዞ ይመጣል። አዲስ አሰልጣኝ ለሾመው እና በአመዛኙ ጥሩ ዝውውሮችን የፈፀመው ባህር ዳር ከተማ ከተማም በዚህ ሚዛን ውስጥ መግባቱ የሚቀር አይመስልም። ከዚህ በመነሳት ቡድኑን በቀጥታ ለሊጉ ቻምፒዮንነት መጠበቅ የሚለው ሀሳብ ግን ለአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ የሚዋጥ አልሆነም። “መጀመሪያም ከክለቡ ጋር ስንነጋገር ያስቀመጥነው አንድ ወጥ የሆነ አስተማማኝ እና ቅርፅ ያለው ቡድን መገንባት ነው የዚህ ዓመት አላማችን። ቡድን በአንድ ዓመት አይገነባም። በአንድ አመት ተገንብቶ ዋንጫ እንዲያመጣ አይጠበቅበትም። ካልሆነ ከአቅም በላይ መጠበቅ (over ambitious) መሆን ነው። ይህ ደግሞ ጉዳት አለው። ስለዚህ በዚህ ዓመት የእኛ ዓላማ ጠንካራ እና አስተማመኝ የሆነ የራሱን ቅርፅ የያዘ ቡድን መገንባት ነው። ይህንን ለማሳካት ጥረት እናደርጋለን። ይህ ሲባል ደግሞ ወደ ላይኛዎቹ ተፎካካሪ ቡድኖች አንጠጋም ማለት ሳይሆን የቡድን ግንባታ ዓላማችንን እያሳካን እንቀጥላለን ለማለት ነው።” ሲሉም ይሞግታሉ።
ከአሰልጣኙ የቀደሙ ቡድኖች ባህሪ በመነስት ባህር ዳር ዘንድሮ በሜዳ ላይ የሚኖረውን የእንቅስቃሴ ዓይነት መገመት አይከብድም። በኳስ ቁጥጥር የበላይነት ፍፁም ዕምነት ያላቸው እንስትራክተሩ በጣና ሞገዶቹ ቤት በተጋጣሚዎች እንቅስቃሴ ላይ ከሚወሰን ይልቅ ወጥ የሆነ መገለጫ ያለው ቡድን የመግንባት ሀሳቡ አላቸው። በዚህ ሁኔታ የሚሰሩት ቡድን “ኳስ ብዙ የማያባክን” ሲሉ የገለፁት አሰልጣኝ አብርሀም በሰንጠረዡ እናት በሚደረገው ፉክክር ውስጥ በመቆየት እስከ ሦስት ወይም እስከ አምስት ያለውን ቦታ ማግኘትን ያስባሉ።
ባህር ዳር ወደ ኳስ ቁጥጥር አድልቶ ከመምጣቱ ባሻገር ያሉ ለውጦችን ስንመለከት በፍፁም ዓለሙ ሚና እንጀምራለን። 2013 ላይ የቡድኑ ብቸኛ የፈጠራ ምንጭ ሆኖ የታየው ፍፁም በርካታ ጎሎችን በማስቆጠርም ነበር ውድድሩን ያገባደደው። ይህ ጉዳይ ቡድኑ ለተጋጣሚዎች በቀላሉ ተገማች እንዲሆን ሲያደርገው የተጨዋቹን እንቅስቃሴ መቆጣጠር የቻሉ ቡድኖች ጨዋታ ሲቀላቸው በተደጋጋሚ ተመልክተናል። ዘንድሮ አማካይ መስመሩ ተጨማሪ ጥሩ ደረጃ ያላቸውን ተጫዋቾች ማግኘቱ እንዲሁም ፊት መስመር ላይ በንፅፅር የተሻሉ ጎል አስቆጥሪ ተጫዋቾች መካተታቸው የታታሪውን አማካይ ኃላፊነት የሚያቀልለት ይሆናል። ይህንን ተከትሎም ይደረግበት የነበረው ትኩረት መከፋፈል የተሻሉ ክፍተቶችን ካስገኘለት የፍፁም ዓለሙ ድንቅ አማካይነት እስከምን እንደሚደርስ የሚያሳየን ዓመት ይሆናል።
ሌላው የባህር ዳር የመሻሻል ነጥብ ከተጋጣሚዎች አቀራረብ አንፃር ይታያል። የዓምናው ባህር ዳር ኳስ መቆጣጠርን ከሚያዘወትሩ ወይንም በቶሎ ወደ ግብ ለመድረስ ከሚሞክሩ ቡድኖች ጋር ሲገናኝ የተሻለ ጥንካሬ ይስተዋልበት ነበር። በተቃራኒው በራሳቸው ሜዳ ላይ መቆየትን ምርጫቸው የሚያደርጉ ቡድኖች ሲገጥሙት በተሳኩ ቅብብሎች ወደ ተጋጣሚ ሳጥን መግባት ሲከብደው ይታይ ነበር። ይህ ሁኔታ ዘንድሮ ከወገብ በላይ ባለው የስብስብ አማራጭ የተለያዩ ስልቶችን ተጠቅሞ ተጋጣሚን ሰብሮ የመግባት ዕድልን በማግኘቱ ሊለወጥ ይችላል። ዓምናም በግለሰባዊ እና በመናበብ ስህተቶች ግቦች እንዲቆጠርበት ምክንያት ሲሆን የነበረውን የኋላ መስመሩን ያለብዙ ዕድሳት ተፈላጊው የትኩአት ደረጃ ላይ ማድረስ ግን የአሰልጣኝ አብርከም መብራቱ ፈተና መሆኑ አይቀርም።
የአዲስ አበባ ዋንጫን በማንሳት ወደ ዋናው ውድድር የሚገባው ባህር ዳር ከተማ ቀዳሚ ፍልሚያውን ጥቅምት 9 ላይ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር ይከውናል።
የባህር ዳር ከተማ የ2014 ስብስብ ዝርዝር
ግብ ጠባቂዎች
1 ናትናኤል በልስቲ (U-23)
23 ይገርማል መኳንንት
44 ፋሲል ገብረሚካኤል
91 አቡበከር ኑሪ
ተከላካዮች
2 ፈቱዲን ጀማል
4 ኃይማኖት ወርቁ
5 ጌታቸው አንሙት
6 መናፍ ዐወል
7 ግርማ ዲሳሳ
13 አህመድ ረሺድ
15 ሰለሞን ወዴሳ
16 መሳይ አገኘሁ
19 አቤል ውዱ
30 ፍፁም ፍትሕአለው (U-23)
66 ብሩክ ያለው (U-23)
አማካዮች
10 ፉአድ ፈረጃ
11 አፈወርቅ ኃይሉ
12 በረከት ጥጋቡ
14 ፍፁም ዓለሙ
21 ፍቅረሚካኤል ዓለሙ
25 አለልኝ አዘነ
27 አብዱልከሪም ኒኪማ
29 ኃይለየሱስ ከተማው (U-23)
አጥቂዎች
8 ኪዳነማርያም ተስፋዬ (U-23)
9 ተመስገን ደረሰ
11 ዜናው ፈረደ
17 ዓሊ ሱሌይማን
18 ሣለአምላክ ተገኘ
22 ይበልጣል አየለ
77 ኦሴ ማውሊ