ወልቂጤ ከተማን የተመለከተው የቅድመ ውድድር ዘመን ዳሰሳችንን እንዲህ አሰናድተነዋል።
በተሰረዘው የ2012 ውድድር ዓመት ወደ ኢትዮጵያ አንደኛ የሊግ እርከን ውድድር የመጣው ወልቂጤ ከተማ አምና አጀማመሩ እና አጨራረሱ የተራራቀ የሆነበትን ጊዜ አሳልፏል። በመጀመሪያዎቹ 11 ሳምንታት በውጤትም ሆነ በእንቅስቃሴ ቢያንስ በሰንጠረዡ አጋማሽ በላይ የማጠናቀቅ አቅም እንዳለው ማሳየት ቢችልም ቀጣዮቹ ሳምንታት ግን በተቃራኒው የቀጠሉ ነበሩ። ቡድኑ የነበረውን ጠንካራ የመከላከል አቅም እያጣ ተደጋጋሚ ሽንፈቶች እየበረከቱበት መጥቶም ከአሰልጣኝ ደግአደረገ ይግዛው ጋር እስከመለያየት ደርሷል። በመቀጠል በምክትል አሰልጣኙ አብዱልሀኒ ተሰማ ቀጥሎም በአሰልጣኝ ሲሳይ አብርሀ እየተመራ ሊሻሻል ያልቻለበትን ዓመት በወራጅ ቀጠና ውስጥ አጠናቋል። ነገር ግን የትግራይ ክልል ክለቦች ዘንድሮ ወደ ውድድር መመለስ አለመቻላቸውን ተከትሎ የእነርሱን ቦታ ለመተካት ሲባል በተዘጋጀው ውድድር ሌላ ዕድል ያገኘው ወልቂጤ ከተማ አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸውን ቀጥሯል። በውድድሩም በአምስት ጨዋታዎች 11 ነጥቦችን በመሰብሰብ በሁለተኝነት አጠናቆ በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውስጥ መቀጠሉን ለማረጋገጥ በቅቷል።
2013 ላይ አራት አሰልጣኞችን የተጠቀመው ወልቂጤ ከተማ ከማሟያ ውድድሩ በኋላ ከአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ጋር ተጨማሪ አንድ ዓመት ለመቀጠል ወስኗል። በምክትልነትም አሰልጣኝ ኢዮብ ማለን በመቅጠር የአሰልጣኝ ቡድን አባላቱን ማሟላት የጀመረው ክለቡ ቆየት ብሎም አሰልጣኝ ደጉ ደሳለኝን በግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝነት ሾሟል። ከዚህ በተጨማሪ ታምሩ ናሳ የህክምና ባለሙያነት ሥዩም እንግዳወርቅ ደግሞ የቡድን መሪነት ሚና ኖሯቸው በወልቂጤ ከተማ የቴክኒክ ክፍል ውስጥ እንመለከታቸዋለን።
ወልቂጤ ከተማ በዝውውሩ ረገድ ዘግየት ብሎ ገበያውን ቢቀላቀልም ከሌሎች ጋር ሲነፃፀር በብዛት መካከለኛ የሚባል በጥራት ግን ጥሩ የሆነ የዝውውር ጊዜን አሳልፏል። ቡድኑ ዮናስ በርታ እና ዮናታን ፍሰሐን ውል ያራዘመ ቢሆንም አብዝቶ ሲጠቀምባቸው የነበሩ እንደጀማል ጣሰው፣ ቶማስ ስምረቱ፣ ሄኖክ አየለ እና አሜ መሐመድን የመሳሰሉ ተጫዋቾቹ ዘንድሮ አብረውት እንደማይቀጥሉ ታውቋል። በመሆኑም በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ በወጥነት የሚሳተፉ እና ካለፈው ዓመት አንፃር ሊያጠናክሩት የሚችሉ ተጫዋቾች ያስፈልጉት ነበር። በዚህም አይቮሪኮስታዊው ግብ ጠባቂ ሲልቪያን ግቦሆ እና ሰዒድ ሀብታሙን በግብ ጠባቂነት ወደ ስብስቡ አምጥቷል። ተከላካይ መስመር ላይ ዋሀብ አዳምስ እና አበባው ቡታቆ አማካይ ክፍል ላይ ደግሞ ፋሲል አበባየሁ፣ አብርሀም ታምራት እና ፍፁም ግርማ አዳዲሶቹ የወልቂጤ ከተማ ተጫዋቾች ሆነዋል። ከዝውውሩ በርከት ያሉ ተጫዋቼችን ፊት መስመር ላይ ያስፈረመው ወልቂጤ ከተማ አላዛር ዘውዱ፣ ጫላ ተሺታ፣ መሐመድ ናስር እና ጌታነህ ከበደን በእጁ ማስገባት ችሏል።
“በጅማም እነ አቡበከር፣ ቤካም፣ አማኑኤል፣ ኢብራሂምን ከየት እንዳወጣኋቸው እናንተ ታውቃላችሁ። ዘንድሮ ደግሞ አትጠራጠሩ የሚገርም ነገር ታያላችሁ ብዬ አስባለሁ። በቢጫ ቴሴራ አምስት ከወልቂጤ ሦስት ደግሞ በአረንጓዴ ቴሴራ አዳዲስ ፊቶችን ታያላችሁ።” የሚሉት አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው በዘንድሮው ቡድናቸው ውስጥ ግብ ጠባቂው ቢንያም አብዮት ፣ ተከላካዩ ቴዎድሮስ ብርሀኑ አማካዮቹ ምንተስኖት ዮሴፍ፣ አድናን ፈይሰል፣ ሚልዮን ኤርገዜ እና ቴፐኒ ፈቃደን አካተው ውድድሩን እንደሚጀምሩ ይጠበቃል።
አሰልጣኝ ጳውሎስ ባደረጓቸው ዝውውሮች እና አሁን ላይ ባለው የቡድናቸው ስብስብ ልበ ሙሉ ናቸው። አምና ነጥረው መውጣት የቻሉት ረመዳን የሱፍ እና አብዱልከሪም ወርቁ አሁንም በስብስቡ ውስጥ መገኘታቸው ቡድኑን በነበረው ጠንካራ ጎን ላይ ተመስርቶ ለማጠናከር የተመቸ እንደሆነ ያስባሉ። ከዚህ ባሻገር ወልቂጤ በደካማነት ይጠቀስ የነበረው የፊት መስመር ክፍሉ በተለይም ደግሞ የአህመድ ሁሴንን ብቃት ማሻሻል ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ያነሳሉ። “ከተከላካይ ፣ እስከ አማካይ እስከ አጥቂ ቡድኑ ሙሉ ነው። እነ አሕመድን የመሰለ አጥቂ ይዘህ፤ ባለፈው ዓመት በሊጉ ብዙ ኳስ ይስታል ይባላል። እኔ የማልስማማው ጉዳይ አለ። መጀመሪያ ለመሳት ጎል ላይ መድረስ አለብህ። እሱ ጎል ጋር ስለሚደርስ ነው የሚስተው፤ ደርሶ እንዳይስት ማድረግ ደግሞ የኛ ሥራ ነው። በተግባር ዘንድሮ ከአሕመድ፣ ከእስራኤል፣ ከአቡበከር ሳኒ ከእነ ጫላ ከእነ ያሬድ ከእነ አላዛር ፊት ላይ ካሉ ተጫዋቾች በተለይ ብዙ ነገር እጠብቃለሁ። ፈጣኖች እና ወደ ጎል ቶሎ የሚደርሱ ተጫዋቾች ስላሉን ያንን እንጠቀማለን ብዬ አስባለሁ። በዚህም ፈጣን የማጥቃት ጨዋታ ነው የምንጫወተው።”
አሰልጣኙ ይህንን ፅሁፍ ባዘጋጀንበት ወቅት ስሙን ሳይጠቅሱ “በሀገሪቱ አለ የተባለ አንድ አጥቂ በቅርቡ ይቀላቀለናል” በማለት አንስተውት የነበረው ጌታነህ ከበደ ወደ ወልቂጤ መምጣትም በስብስባቸው ላይ ያላቸውን ዕምነት ይበልጥ ከፍ እንደሚያደርገው መገመት አያዳግትም።
ወልቂጤ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ዘግየት ብሌ ጷግሜ አንድ ቀን በሀዋሳ ከተማ ነበር ማድረግ የጀመረው። በእርግጥ ከሰኔ አጋማሽ እስከ ሐምሌ መጀመሪያ በዘለቀው የማሟያ ውድድር ላይ መቆየቱ ቡድኑ ዝግጅቱን ቆይቶ መጀመሩ አሰልጣኙ በቶሎ ወደሚፈልጉት የዝግጁነት ደረጃ ለማምጣት እንዳይቸግራቸው ያገዘ መስላል። “በአካል ብቃት ደረጃ ቡድኑ ብዙ አልተጎዳም። ራሳቸውን አዘጋጅተው የመጡ ተጫዋቾች በመሆናቸው በቶሎ ወደ ኳሱ ነው የገባነው ። Endurance, speed, flexibility and strength በሙሉ ከኳስ ጋር ነው የሰራነው። በመቀጠል የውህደት ሥራዎች ላይ አተኩረናል። በቀጣይ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ማድረግ እንጀምራለን። ” የሚለው ሀሳባቸውም ይህንን ያጠናክራል።
አሰልጣኝ ጳውሎስ ይህንን አስተያየት ከሰጡን በኋላ ወልቂጤዎች በተመሳሳይ ውድድሮች ላይ ካልተካፈሉት አርባ ምንጭ ከተማ እና ወላይታ ድቻ ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን አድርገዋል። በእርግጥ ክለቡ በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫም ሆነ በአዲስ አበባ ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ አለመካፈሉ ከሌሎች ክለቦች አንፃር በአጭር ቀናት ተደጋጋሚ በሆኑ የፉክክር ጨዋታዎች ስብስቡን የመፈተሽ ዕድል እንዳያገኝ አድርጎታል። አሰልጣኙ ግን ቡድኑ ዝግጅቱን ቆየት ብሎ መጀመሩ መሰል ውድድሮች ተጫዋቾችን ለጉዳት ሊዳርጉ መቻላቸው ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ሊያመዝን እንደሚችሉ አንስተውልን ነበር።
“ብዙ ማውራት የሚያስፈልገው ነገር አይደለም ። ግን በወልቂጤ ክለብ ታሪክ ያልተገኘ ውጤት አመጣለሁ ብዬ ገምታለሁ።” የሚሉት አሰልጣኝ ጳውሎስ በመለያ ውድድሩ ላይ እንደተመለከትነው ለኳስ ቀጥጥር ቦታ የሚሰጥ እና ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ለመድረስ የሚሞክር ቡድን እንደሚሰሩ ሲጠበቅ የስብስባቸው የጥንካሬ ምንጭ በተጨዋቾች መሐል ያለው ግንኙነት እንደሆነ ዕምነቱ አላቸው። “በጣም ኳስ ይዞ በቶሎ ተጋጣሚ ሜዳ ገብቶ ተቃራኒ ቡድንን የሚያስጨንቅ ቡድን መሥራት ላይ ነው ያተኮርነው። አንደኛ ተጫዋቾቹን ከሆቴል አጠቃቀም ጀምሮ በሥነ ምግባርም የምናዛቸውን ነገር ሁሉ እያደረጉ ነው። እና 25ቱም ተጫዋቾች ለእኔ አንድ ናቸው። አንዱን ተክቶ አንዱ የመጫወት ብቃት አለው። ምንም ኩርፊያ የለም ፣ ምንም መጣላት የለም። አንድ ናቸው 25ቱም። ሊጉ ላይ ስንቆይ ያንን ነገር አስተምሬያቸዋለው ከዛ ነው የቀጠልነው። አዳዲሶቹንም ይሄንን ነው ያስተማርናቸው። በጣም ትልቅ መተሳሰብ እና ወዳጅነት አላቸው። ይህ እንግዲህ የቡድን አስተዳደር ውጤት ነው። የአሰልጣኝ ሥራ ነው። እንግዲህ ይህንን ከረዳቴ እና ከግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ ጋር በመተጋገዝ በመነጋገር ውጤታማ እንሆናለን ብዬ እገምታለሁ።”
ወልቂጤ በአብዛኞቹ የሊጉ ክለቦች ዘንድ የሌለ የአምናውን ቡድን ጠንካራ ጎን የማስቀጠል ዕድል ይኖረዋል። ለዚህም እምነት ተጥሎባቸው በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ በብዛት ይካተቱ የነበሩት ዳግም ንጉሤ፣ ረመዳን የሱፍ፣ ሀብታሙ ሸዋለም፣ አብዱልከሪም ወርቁ እና በኃይሉ ተሻገር አብረው መኖራቸው ይረዳል። የቡድኑ የተሻለ ጎን የነበረው የአማካይ መስመሩ ብዙ አለመነካካቱ ለአሰልጣኙ የማሻሻል ስራ መነሻ የሚሆን ነው። በአዲስ መልክ የተካተቱት ተጫዋቾችም ቦታው ላይ ያለውን አማራጭ ያሰፋለታል። በዚሁ አማካይ መስመር ላይ ባሳለፍነው የውድድር ዓመት ድንቅ ጊዜ ያሳለፈው አብዱልከሪም ወርቁ ሌሎች ክለቦችን የሚያማልል ቢሆንም ኮንትራት ያለው መሆኑ ለወልቂጤ በረከት ነው። ተጫዋቹም በግል ብቃቱ ይበልጥ ተሻሽሎ ዘንድሮም ተፅዕኔ ፈጣሪንቱን እንደሚያስቀጥል ይጠበቃል። ያም ቢሆን አሰልጣኝ ጳውሎስ በአመዛኙ ማለፊያውን በአማካዩ በኩል የሚያደርገውን የቡድኑን የማጥቃት ሂደት ተገማችነት መቀነስ ይጠበቅባቸዋል።
ወልቂጤ ሁነኛ ፈራሚ ያገኘበት ወሳኝ ቦታ የግብ ጠባቂ ቦታ ነው። አምና በግለሰባዊ ስህተቶች ግቦችን ማስተናገዱ ላስመዘገበው ደካማ ውጤት አንዱ መነሻ የሆነው ወልቂጤ አሁንም የአይቮሪኮስት ብሔራዊ ቡድን ተመራጭ የሆነው ግብ ጠባቂ ሲልቪያን ግቦሆን በእጅ ማስገባቱ የችግሩ መፍትሄ እንደሚሆን ይታሰባል። ከግብ ፊት የነበረው የተከላካ መስመሩ አለመናበብም እንዲሁ ዋጋ ሲያስከፍለው ቆይቷል። እርግጥ ነው ይህ ችግር በመለያ ውድድሩ ላይ ግብ ሳያስተናግድ በመውጣት ጭምር ተሻሽሎ ታይቷል። ሆኖም ሊጉ የረጅም ጊዜ ውድድር ከመሆኑ አንፃር ዮናስ በርታ እና ውሀብ አዳምስን አዲስ ጥምረት በአግባቡ መግራት ይጠበቅበታል። የአበባው ቡታቆ ወደ ስብስቡ መምጣትም በግራ በኩል ረመዳን የሱፍን በልምድ ያግዛል።
እንደሌላው የቡድኑ ክፍል ሁሉ ብዙ ተጫዋቾች ጌታነህ ከበደ ይበልጥ ተጠናክሯል። በሦስት የፊት ተሰላፊዎች ከመጠቀሙ አንፃር አማራጫቹ መስፋታቸው በመልካም ጎኑ የሚታይ ሲሆን የቦታው ተሳላፊዎችን የግል አጨራረስ ብቃት አሳድጎ መምጣት እጅግ አስፈላጊ ይሆናል። መሰል ጉዳዮች ተስተካክለው ከመጡ በስብሱ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች ቢያንስ ቡድኑ ስጋት ውስጥ ሳይገባ እንዳይዘልቅ ለማድረግ ጥሩ እርምጃዎች ሆነው ይታያሉ።
ወልቂጤ ከተማ የዘንድሮውን የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጉዞውን ጥቅምት 8 ላይ አዳማ ከተማን በመግጠም ይጀምራል።
የወልቂጤ ከተማ የ2014 ስብስብ
ግብ ጠባቂ
1 ሲልቪያን ግቦሆ
30 ቢንያም አብዮት (U-23)
99 ሰዒድ ሀብታሙ
ተከላካዮች
3 ረመዳን የሱፍ
4 ተስፋዬ ነጋሽ
5 ዮናስ በርታ
12 አበባው ቡታቆ
17 ዮናታን ፍስሐ
19 ዳግም ንጉሤ
23 ቴዎድሮስ ብርሀኑ (U-23)
24 ዋሀብ አዳምስ
26 ፍፁም ግርማ
አማካዮች
8 በኃይሉ ተሻገር
13 ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ
14 አብዱልከሪም ወርቁ
15 ቴፐኒ ፈቃደ (U-23)
20 ያሬድ ታደሰ
21 ሀብታሙ ሸዋለም
22 አብርሀም ታምራት
27 ሚልዮን ኤርገዜ (U-23)
28 ፋሲል አበባየሁ
29 ምንተስኖት ዮሴፍ (U-23)
67 አድናን ፈይሰል (U-23)
አጥቂዎች
7 ጫላ ተሺታ
9 ጌታነህ ከበደ
10 አህመድ ሁሴን
11 እስራኤል እሸቱ
16 አላዛር ዘውዱ
18 አቡበከር ሳኒ
25 መሐመድ ናስር