የክለቦች የውድድር ዘመን ቅድመ ዳሰሳ | ሲዳማ ቡና

ቀጣዩ የቅድመ ውድድር ዳሰሳ እና የቀጣይ ጊዜያት ምልከታችን ትኩረት ሲዳማ ቡና ሆኗል።

በ2013ቱ የቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ያልታሰበ ጉዞ ካደረጉ ክለቦች ውስጥ አንዱ ሲዳማ ቡና ነበር። ከዚያ ቀደም በነበሩ ተከታታይ ጊዜያት በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ሲቆይ ይታይ የነበረው ቡድኑ ዓመቱን 31 ነጥቦች ይዞ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ሲያጠናቅቅ እስከውድድሩ ማብቂያ ጨዋታዎች ድረስ የመውረድ ስጋት እንደተጋረጠበት ቆይቷል። ሲዳማ ቡና በዓመቱ ውስጥ የአሰልጣኝ ቅያሬ ካደረጉ ክለቦች ውስጥም አንዱ ነበር። ለዓመታት አብረውት የቆዩትን አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉን 11ኛው ሳምንት ላይ አሰናብቶ ቀሪውን ጊዜ በአሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ እየተመራ ነበር ያጠናቀቀው። ይህ ለውጥ በውድድሩ አጋማሽ ከተደረጉ ዝውውሮች ጋር ተደምሮ ቡድኑ ዓመቱ ሲጀምር ከነበረው አንፃር በብዙ ለውጦች ውስጥ አልፎ ውድድሩን አጠናቋል። በዘንድሮው የሊጉ ፍልሚያ ላይ ወደ ውድድር ሲመጣም አምና ማብቂያው ላይ ያያቸውን ተስፋዎች ከአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ጋር ለማስቀጠል አስቦ በክረምቱ ራሱን በማጠናከር ሲዘጋጅ ከርሟል።

ሲዳማ ቡናዎች ከጅማ አባ ጅፋር እና መቐለ ሰባ እንደርታ ጋር የሊጉን ክብር ማሳካት ከቻሉት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ጋር ለቀጣይ ሁለት ዓመታት አብረው ለመዝለቅ መስማማታቸው የክረምቱ እንቅስቃሴያቸው ዋነኛው ውሳኔ ነው ማለት ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪ የክለቡ የቀድሞው ተጫዋች የነበረው እና ከ20 ዓመት በታች ቡድኑን በማሰልጠን ላይ ይገኝ የነበረው ወንድምአገኝ ተሾመን እንዲሁም ለይኩን ተደሰን (ዶ/ር) በረዳት አሰልጣኝነት ሾሟል። በግብ ጠባቂ አሰልጣኝነት ስንታየሁ ግድየለሁ በህክምና ባለሙያነት ደግሞ ብሩክ ደበበ እና ዮሴፍ ዮሐንስ የቡድኑ አባል ሆነው ይቀጥላሉ።

ሲዳማ ቡና በክረምቱ ያደረጋቸው ዝውውሮች እና ነባር ስብስቡ ከለቀቁት አንፃር ሲታይ ከአምናው የተለየ ቡድንን ይዞ መቀጠልን ያማከለ ይመስላል። ከቡድኑ ጋር ከተለያዩት ውስጥ አምስት የሚሆኑት ባሳለፍነው የውድድር ዓመት ከግማሽ በኋላ የመጡ መሆናቸው ሲታሰብ ዘንድሮ አዲስ ሲዳማ እንደምናይ ፍንጭ የሚሰጥ ነው። ከሁሉም በላይ ቡድኑ ኦኪኪ አፎላቢ እና ማማዱ ሲዲቤን ማጣቱ ፊት ላይ አግኝቶት የነበረው አስፈሪነት እንዳያሳጣው ቢያሰጋም አሰልጣኝ ገብረመድህን ይህ ሁኔታ እምብዛም ያሰጋቸው አይመስልም። አሰልጣኙ ለሦስተኛ ጊዜ በተጫዋችነት ካገኙት ናይጄሪያዊው አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢ ብዙ ጠንካራ ጎኖች የነበሩት መሆኑ እርሱን በቀጥታ ለመተካት የተጋነነ ውጪ የሚጠይቅ መሆኑን በወቅቱ በነበረን ቆይታ ሲያነሱ የሲዲቤ ጉዳይ ከዚህ የተለየ መሆኑን ግን አልሸሸጉም። ” በሲዲቤ ደረጃ ያለ ተጫዋች ለማግኘት ከጫፍ ደርሰናል። እርሱን ያልቀጠለበትም ምክንያት ታታሪ ባለመሆኑ ለሥልጠና ምቹ ባለመሆኑ ነው። ሀምሳ ሀምሳ በመሆኑ የሥራ አቅሙ (work rate) ከፍ ያለ ተጫዋች ለማግኘት ነው እየጣርን ያለነው።” ብለው የነበረ ሲሆን እንዳሉትም ኬንያዊው ፍራንሲስ ካሀታ እና ዩጋንዳዊው ዴሪክ ኒስምባቢን በዝውውር መስኮቱ መዝጊያ ቀናት ላይ ወደ ክለቡ መጥተዋል።

እንደ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ገለፃ ዘንድሮ በሊጉ ተፈላጊ ተጫዋቾች ባሉባቸው ክለቦች ውል ላይ ያሉ ስለሆነ ኮንትራት ከጨረሱት መካከልም አንዳንዶቹ በቡድኑ እይታ ውስጥ ቢገቡም በጣም የተጋነነ ክፍያ በመጠየቃቸው ቡድናቸው ሙሉ ለሙሉ አጥጋቢ የዝውውር ጊዜን ባያሳልፍም ካገኛቸው ተጨዋቾች የቀደመ የተጫዋችነት ደረጃ እና አሁን በቅድመ ውድድር ዘመን እያሳዩት ካሉት ብቃት አኳያ ግን ጥሩ ግልጋሎት እንደሚሰጡ ይጠብቃሉ። “በዝውውር ያመጣናቸው ተጫዋቾች በጣም ጥሩ ፣ የቡድኑን አጨዋወት ተከትለው መጫወት የሚችሉ ተጫዋቾች ናቸው። የተወሰኑት በጤና በኩል ወጣ ገባ እያሉብን ነው። የምንፈልገውን ሥራ በጊዜ ጀምረው በጊዜ የመጨረስ ሁኔታ አልታየባቸውም እንደዚህ ዓይነት ችግሮች አሉብን። ከዚህ ውጪ ግን የመጡት ተጫዋቾች በምፈልገው አጨዋወት ይሄዳሉ ብለን የገመትናቸው ስለሆኑ ጥሩ መግባባት ይፈጥራሉ ብዬ አስባለሁ። በአካል ብቃት በጣም ከፍ ያሉ ላይሆኑ ይችላሉ፤ በዕውቀት ግን በጣም ጥሩ ናቸው። በተለይ መሀል ላይ ያሉት እና በመስመር የሚጫወቱት ተጫዋቾቻችን ከከፍተኛ ሊግ የመጡትም በጣም ጥሩ ለውጥ እያመጡ ስለሆነ ጥሩ ነገር እንሰራለን ብለን እናስባለን። ”

ሲዳማ በግብ ጠባቂ ቦታ ላይ በቀድሞው ክለቦቻቸው ኢትዮጵያ ቡና እና ወላይታ ድቻ በርከት ያሉ ጨዋታዎችን የከወኑት ተክለማሪያም ሻንቆ እና መክብብ ደገፉን በመሳይ አያኖ፥ ለይኩን ነጋሽ እና በአጋማሹ ክለቡን ተቀላቅሎ ጥሩ ግልጋሎት የሰጠው ፋቢየን ፈርኖሌ ክፍተት ላይ አሟልቷል። ተከላካይ መሰመር ላይ ፈቱዲን ጀማል እና ሰንደይ ሙቱኩ የለቀቁ ሲሆን ተስፋዬ በቀለ፣ ምንተስኖት ከበደ፣ ጋናዊው ያከቡ መሀመድ እንዲሁም ሰለሞን ሀብቴ የቦታው ተጨማሪ ፈራሚዎች ሆነዋል። ሙሉዓለም መስፍን፣ ፍሬው ሰለሞን እና ቴዎድሮስ ታፈሰን ያገኘው አማካይ ክፍሉም ሲታይ ከለቀቁት የመሀል ተጫዋቾች አንፃር በልምድ እና በጥራት ጨምሮ የመምጣት ዕድል አለው። የከፍተኛ ሊጎቹ አንዋር ዱላ እና ብሩክ ሙሉጌታን ያገኘው የፊት መስመርም ከሁለቱ የውጪ ዜግነት ካላቸው ተጫዋቾች እና ከነባሮች ጋር ተደምሮ ተዋቅሯል።

ዝውውሮቹ ቡድን ከመገንባት አንፃር መልካም ቢባሉም እንደ አዲስ የማሰባጠሩ ኃላፊነት ግን ቀላል አይሆንም። ከዚህ በተለየ ግን የአብዛኞቹ አሰልጣኞች የየዓመቱ ፈተና የሆነው ይህ ጉዳይ በሲዳማ የዘንድሮው የመጨረሻ ቡድን ግንባታ ላይ የሚኖረው ተፅዕኖን የሚያቀል ጉዳይ ስለመኖሩ የሁለት ጊዜ ቻምፒዮኑ ዕምነት አላቸው። “ፈተናው ቡድኑን እንደቡድን መስራት ነው። አዲስ ቡድን በሚፈለገው የአጨዋወት መንገድ እንዲሄድ ማድረጉ ነው ። ነገር ግን አዳዲስ ቢሆኑም የማውቃቸው ተጫዋቾች ናቸው። እኔ የምከተለውን አጨዋወት እና የምፈልገውን ነገር የሚያውቁ ተጫዋቾች ናቸው አብዛኞቹ። ጥቂት የማላውቃቸው አሉ፤ ከከፍተኛ ሊግ እንደመጡት ያሉ። እነርሱ በውድድር ላይ አይቼ ያመጣኋቸው ናቸው። እነሱም በጥሩ ሁኔታ እየሄዱ ነው ያሉት።ጥሩ ነገር እንሰራለን የሚል ዕምነትም አለኝ።”

ይህን መሳይ ከነበረው የዝውውር ሒደት በተጨማሪ ስድስት ወጣት ተጫዋቾች በሲዳማ ቤት ማደግ ችለዋል። ግብ ጠባቂው ሀብታሙ መርመራ፣ ተከላካዩ መኳንንት ካሣ፣ አማካዩ አልማው አሸናፊ እንዲሁም የመስመር አጥቂዎቹ ማርኮ ተሾመ፣ ድገፈኝ ዓለሙ እና አቤኔዘር አሸናፊ በዚህ ውስጥ ይካተታሉ።

ሲዳማ ቡና ውል ያረዘመላቸውን፣ አዲስ የፈረሙትን እንዲሁም ኮንትራታቸው ያልተጠናቀቀ ተጫዋቾቹን ይዞ ከነሐሴ 10 ጀምሮ ዝግጅቱን ጀምሯል። በየመሐሉ የሚፈርሙ ሌሎች ተጫዋቾችንም እየጨመረ በሀዋሳ ከተማ ሲሰራ ሰንብቷል። በአካል ብቃት ላይ አመዝኖ የጀመረው የዝግጅት ሂደት የቡድኑ ስብስብ በብዛት አዲስ እንደመሆኑ በሚጫወትበት መንገድ ላይ ያጠነጠነ ሆኖ ቀጥሏል። በዝግጅት ጨዋታዎች ደረጃ ሲዳማ ሰበታ ከተማን መግጠም የቻለ ሲሆን በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ጨዋታ ላይ አራት ተጨማሪ ጨዋታዎችን ማድረግም ችሏል።

ከአሰልጣኙ የተፎካካሪነት እና የቻምፒዮንነት ልምድ እንዲሁም ክለቡ ካለፈው የውድድር ዓመት በፊት አሳይቶት ከነበረው ምልክት አንፃር ዘንድሮ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ሊኖር እንደሚችል ይገመታል። አሰልጣኝ ገብረመድህን ግን በዚህ ነጥብ ሙሉ ለሙሉ የሚስማሙ አይመስሉም። ” በዚህ ሁኔታ ውጤቱን መተንበይ ከባድ ነው። በቀጣይ የመዘጋጃ ጨዋታዎች ቡድናችንን እየሠራን አንድ ጠንካራ ቡድን ለመስራት ጥረት እናደርጋለን። ከዚያ በኋላ የመጀመሪያው አራት እና አምስት ጨዋታ ካየን በኋላ ነው ምን ደረጃ ላይ ይቀመጣል ብለን ልንወስን የምንችለው፤ ከወዲሁ ብዙ ነገር ማለት አንቻልም።” በማለትም የቡድናቸውን የውጤት መዳረሻ ለመገመት ጊዜው ገና እንደሆነ ያነሳሉ።

በ2014ቱ ውድድር ከዓምናው አንፃር በእጅጉ ተሻሽሎ መቅረብ ያለበት ዋናው የቡድኑ ክፍል የኋላው ነው። ዓምና በሊጉ በርካታ ግብ በማስተናገድ (31) ከድሬዳዋ ከተማ ጋር በጋራ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ሲዳማ ቡና ይህን ድክመት ለማረም ስብስቡ ላይ ማሻሻያ አድርጋጓል። ግቦች በቀላሉ እንዳይቆጠሩ ለማድረግ አጠቃላይ የቡድኑ መዋቅር አስተዋፅዖ ቢኖረውም የተጫዋቾች የግል ብቃት በራሱ ስህተቶችን ከመቅነስ እና መናበብን ከመፍጠር አንፃር ወሳኝ ነው። የመጡት ተጫዋቾች ከአሰልጣኙ ጋር ከዚህ ቀደም አብረው የመሥራት ልምዱ የነበራቸው እንደተስፋዬ በቀለ እና ምንተስኖት ከበደን ያካተተ መሆኑ ሲታሰብም ቦታው ለሚፈልገው ቅንጅት መልካም አጋጣሚን ይፈጥራል። በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ላይ ጋናዊው ያኩቡ መሀመድ ያሳየው አቋምም ቦታውን ይበልጥ ለማጠናከር ሁነኛ አማራጭ ያደርገዋል። በሌላ በኩል ግን በግሉ ተስፋ ሰጪ ዓመት አሳይቶ የነበረው ጊት ጋትኩት ዘንድሮ በቦታው በሚኖረው ፉክክር ውስጥ ዕድገቱን የማስቀጠል ፈተና እንደሚጠብቀው መናገር ይቻላል።

የተጫዋች አሰልጣኝ የከዚህ ቀደም የአብሮነት ልምድ በሲዳማ የአማካይ ክፍል ላይም መደገሙ እንደተከላካይ ክፍሉ ሁሉ የውህደት ሥራውን ሊያቀለው ይችላል። እዚህ ላይ እንደ ብርሀኑ አሻሞ እና ዳዊት ተፈራ ያሉ ቁልፍ ተጫዋቾች የሚኖርባቸው ቦታን የማስጠበቅ ፍልሚያ ስብስቡን ይበልጥ ሊያጎለብተው ይችላል። ይህ ሀሳብ ባለፉት ዓመታት ያሳየውን ብቃት አምና መድገም ያልቻለው ሀብታሙ ገዛኸኝ እና ብልጭ በሚልበት አጋጣሚ ጉዳት ሲፈትነው ለቆየው ይገዙ ቦጋለ እንዲሁም ለተመስገን በጅሮንድ የሚሰራ ነው። ሁለት የውጪ ዜጎችን ያካተተው የቦታው ፉክክር ዓመቱን ለእነዚህ ተጫዋቾች ወሳኝ ያደርገዋል።

ሲዳማ ቡና በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቀዳሚ ፍልሚያውን ጥቅምት 9 ላይ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በማድረግ ዓመቱን ይጀምራል።

የሲዳማ ቡና የ2014 ስብስብ ዝርዝር

ግብ ጠባቂዎች

1 ፍቅሩ ወዴሳ
30 ተክለማሪያም ሻንቆ
99 መክብብ ደገፉ
44 ሀብታሙ መርመራ (U-23)
80 አዱኛ ፀጋዬ

ተከላካዮች

2 መኳንንት ካሣ (U-23)
3 አማኑኤል እንዳለ
4 ተስፋዬ በቀለ
5 ያከቡ መሐመድ
6 መሐሪ መና
12 ግሩም አሰፋ
19 ግርማ በቀለ
21 ሰለሞን ሀብቴ
22 ምንተስኖት ከበደ
24 ጊት ጋትኩት

አማካዮች

7 ፍሬው ሰለሞን
15 ቴዎድሮስ ታፈሰ
16 ብርሀኑ አሻሞ
20 ሙሉዓለም መስፍን
26 አልማው አሸናፊ (U-23)
56 ማርኮ ተሾመ (U-23)
10 ዳዊት ተፈራ

አጥቂዎች

8 ተመስገን በጅሮንድ
9 ሀብታሙ ገዛኸኝ
11 ይገዙ ቦጋለ
14 ብሩክ ሙሉጌታ
17 አንዋር ዱላ
23 ዴሬክ ንሲምባቢ
25 ፍራንሲስ ካሀታ
27 አቤኔዘር አስፋው (U-23)
77 ደግፈኝ ዓለሙ (U-23)