የፊታችን እሁድ በሚጀመረው የ2014 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ በጨዋታ መሐል የሚቀየሩ ተጫዋቾችን በተመለከተ አዲስ ደንብ መውጣቱ ታውቋል።
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የበላይነት የሚደረገው የሀገራችን ትልቁ የሊግ እርከን የዘንድሮውን ዓመት ውድድሩን ከጥቅምት 7 አንስቶ ማድረግ ይጀምራል። ውድድሩ ባለንበት ሳምንት መጨረሻ በሀዋሳ ከተማ ከመጀመሩ በፊት ደግሞ ዛሬ ጠዋት በክለቦች መካከል የደንብ ውይይት ተደርጓል። ለብዙሃን መገናኛዎች ዝግ የነበረው እና መግባባት የተሞላበት እንደሆነ በተነገረው በዚህ ውይይት ላይ በርካታ ጉዳዮች መነሳታቸውን ሲታወቅ አዲስ እና ጥሩ ይዘት ያለው ደንብም በሊግ ካምፓኒው ቀርቦ በክለቦች ይሁንታን ማገረኘቱ ተረጋግጧል።
በውይይቱ ዘለግ ያለ ደቂቃ የወሰደው አዲሱ ደንብ በጨዋታዎች ተጋጣሚ ክለቦች አምስት ተጫዋቾችን እንዲቀይሩ የሚፈቅድ ሲሆን ተጫዋቾቹን ግን በሦስት አጋጣሚዎች ብቻ እንደሚቀየሩ ያትታል። ከዚህ በተጨማሪ ከአምስቱ ተጫዋቾች ሦስቱ በአረንጓዴ ቴሴራ የተመዘገቡትን ዋና ተጫዋቾች ሲያካትት ሁለቱ ደግሞ በቢጫ መታወቂያ እና ልዩ መታወቂያ የተመዘገቡትን ተጫዋቾች ብቻ እንደሚፈቅድ ሶከር ኢትዮጵያ ተረድታለች። አንዳንድ ክለቦች በዚህኛው ሀሳብ ባይስማሙም የተሻለው እና አብዛኛውን የገዛው ሀሳብ ሆኖ ተገኝቶ እንደፀደቀ አውቀናል።