ሉሲዎቹ ሦስተኛ የአቋም መፈተሻ ጨዋታቸውን አሸንፈዋል

በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከዩጋንዳ ጋር ጨዋታ ያለበት የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አመሻሽ ላይ ከኢትዮጵያ ከ16 ዓመት በታች ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ጋር ተጫውተው ድል ተቀዳጅተዋል።

በአሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ጥቅምት 10 እና 16 ከዩጋንዳ አቻቸው ጋር የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ይጠብቀዋል። ለዚህ ጨዋታ በካፍ የልዕቀት ማዕከል ማረፊያውን በማድረግ ሲዘጋጅ የነበረው ቡድኑም ከዚህ በፊት ከኢትዮጵያ ከ16 ዓመት በታች ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ጋር እና ከኢትዮጵያ ቡና ወንዶች የተስፋ ቡድን ጋር ተጫውቶ ያሸነፈ ሲሆን ዛሬ ደግሞ ባረፈበት ማዕከል ሦስተኛ የአቋም መፈተሻ ጨዋታውን ከኢትዮጵያ 16 ዓመት በታች ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ጋር በድጋሜ አድርጓል።

የቡድኑ አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ታሪኳ በርገና፣ እፀገነት ብዙነህ፣ ዓለምነሽ ገረመው፣ ሀሳቤ ሙሶ፣ መስከረም ካንኮ፣ ህይወት ደንጊሶ፣ እመቤት አዲሱ፣ አረጋሽ ካልሳ፣ ሴናፍ ዋቁማ፣ ሎዛ አበራ እና መዲና ዐወልን በመጀመሪያ አሰላለፍ በማስገባት ጨዋታውን ቀርበዋል። በጨዋታው ወደ ግብ በመድረሱ ረገድ የተሻሉ የነበሩት ሉሲዎቹ በ15ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ የሰላ ጥቃት ሰንዝረዋል። በዚህም ሴናፍ ዋቁማ ከግብ ጠባቂ ጋር የተገናኘቸረበትን ተከላካይ ሰንጣቂ የዐየር ላይ ኳስ አግኝታ ወደ ግብ ብትመታውም ሳይሳካለት ቀርቷል። ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ እቺው አጥቂ ዳግም ወደ ግብ በመሄድ የመታችው ኳስ መረብ ላይ አርፏል። በቀሪ ደቂቃዎች ቡድኑ በሎዛ እና ሴናፍ አማካኝነት ሌሎች አጋጣሚዎችን ቢፈጥርም ተጨማሪ ግብ ሳያገኝ አጋማሹን ፈፅሟል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ለውጠው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በተለይ አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ሁሉንም ተጫዋቾች በማሳረፍ ንግስት መዓዛ፣ ናርዶስ ዘውዴ፣ ትዝታ ኃይለሚካኤል፣ ቅድስት ዘለቀ፣ ብዙአየሁ ታደሰ፣ ኤደን ሽፈራው፣ ብርቱካን ገብረክርስቶስ፣ ሰናይት ቦጋለ፣ ሥራ ይርዳው፣ ረድኤት አስረሳከኝ እና መሳይ ተመስገንን ወደ ሜዳ አስገብተዋል።

አጋማሹ በተጀመረ በ10ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ የኳስ ቅብብል ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል ያመሩት የአሠልጣኝ ብርሃኑ ተጫዋቾች መሪነታቸውን ወደ ሁለት አሳድገዋል። በዚህም መሳይ ተመስገን ከሰናይት ቦጋለ ጋር አንድ ሁለት በመጫወት የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ያገኘችውን ኳስ በጥሩ አጨራረስ መረብ ላይ አሳርፋዋለች።

በተቃራኒው በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ሻል ብለው የታዩት የኢትዮጵያ ወንዶች ከ16 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች በ63ኛው ደቂቃ በቁጥር በዝተው ሉሲዎቹ የግብ ክልል ደርሰው ግብ የሚያገኙበትን የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። በዚህም የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ዮናታን ሀይማኖት ወደ ግብነት ቀይሮት የግቡን ልዩነት አጥበው ነበር። ይህ ቢሆንም ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ በጭማሪው ደቂቃ ከመዓዘን ምት የተሻማን ኳስ በቅድስት ዘለቀ በግንባሯ ግብ አድርጋዋለች። ጨዋታውም በሉሲዎቹ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ያጋሩ