የባህር ዳር ስታዲየም በካፍ ግምገማ ተደርጎበታል

ሀገራችን በብቸኝነት አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የእግርኳስ ጨዋታዎችን እየከወነችበት የምትገኘው የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ያለበት ደረጃ ከካፍ በመጡ ባለሙያ ተገምግሟል።

በአዲሱ የኢትዮጵያ ሚሌኒየም መገንባት የጀመረው የባህር ዳር ሁለገብ ስታዲየም ከሰባት ዓመታት በኋላ በከፊል የግንባታውን ሂደት አገባዶ የካፍ እና ፊፋ ጨዋታዎችን የማስተናገድ ፍቃድ እንዳገኘ ይታወቃል። ለመጀመሪያም ጊዜ በ2007 ደደቢት እና የሲሸልሱ ኮት ዲኦር ያደረጉትን የኮንፌዴሬሽን ካፕ ጨዋታም አስተናግዷል። በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ደግሞ በዛኑ ዓመት በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ኢትዮጵ እና ሌሶቶ ያደረጉትን ጨዋታ ስታዲየሙ አስተናግዶ ነበር።

ምንም እንኳን ስታዲየሙ ሙሉ ለሙሉ የግንባታውን ሂደት ባያጠናቅቅም ከተጠቀሰው ጊዜ ጀምሮ የክለብ እና ብሔራዊ ቡድኖችን ጨዋታዎች ሲያስተናግድ ከርሟል። በተለይ የአዲስ አበባ ስታዲየምን ጨምሮ በሀገራችን የሚገኙት ሌሎች ስታዲየሞች በካፍ መመዘኛ መስፈርት መሠረት ለውድድሮች ብቁ አይደሉም ተብለው እግድ ከተላለፈባቸው በኋላ በብቸኝነት ያሉበትን ጥቃቅን ክፍተቶች በማሻሻል ግልጋሎት ሲሰጥ የነበረው ስታዲየሙም በትናንትናው ዕለት ከካፍ በተላኩ ባለሙያ አሁናዊው ሁኔታ ምልከታ ተደርጎበታል።

መሐመድ ሲዳት የተባሉት ካፍ የላካቸው ሞዛምቢካዊው ባለሙያ በትናንትናው ዕለት የስታዲየሙን የመጫወቻ ሜዳ፣ የተጫዋቾች መቀመጫ፣ የቪ አይ ፒ ማረፊያዎች፣ የሚዲያ ክፍሎች፣ የመልበሻ ክፍሎች፣ የተመልካች መቀመጫዎች እና የፀጥታ መቆጣጠሪያ ክፍሎቹን እንደተመለከቱ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል። ከኮቪድ ጋር በተገናኘ እስካሁን ወደ ኢትዮጵያ ባለሙያ በመላክ የስታዲየሙን እድገት ያልተመለከተው ካፍም መሐመድ ሲዳት ወደ ግብፅ ተመልሰው በሚያቀርቡት ሪፖርት ምላሹን እንደሚያሳውቅ ሰምተናል።