ጅማ ዩኒቨርሲቲ ሜዳ ከካፍ ባለሙያ ምክረ ሀሳብ ተቀበለ

ባሳለፍነው ዓመት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግን ማስተናገድ የቻለው የጅማ ዩኒቨርስቲ ሜዳ በካፍ በተወከሉ ባለሙያ ጉብኝት ተደርጎበታል።

ለመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ዓመታዊ ውድድር እንዲያስተናግድ ታስቦ በኦሊምፒክ ስታንዳርድ የተገነባው የጅማ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም በአንፃራዊነት ደረጃቸውን ጠብቀው ከተገነቡ የዩኒቨርስቲ ሜዳዎች መካከከል አንዱ ነው። በ2013 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአምስት ሳምንታት መርሐ-ግብሮችን (ከ5ኛ እስከ 10ኛ ሳምንት ድረስ) አስተናግዶ የነበረው የጅማ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም በዘንድሮ ዓመትም ውድድሩን ለማዘጋጀት ፍላጎት ማሳየቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበርም ወደ ጅማ በማምራት የስታዲየሙ ያለበትን ሁኔታ እንደተመለከተ ይታወሳል።

ትናንት ቀትር ላይ ደግሞ የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየምን አሁናዊ ሁኔታ ቅኝት ያደረጉት ሞዛምቢካዊው መሐመድ ሲዳት ከፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ዳሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ፍራንኮ እና ከጅማ ክለብ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሱልጣን ዛኪር እንዲሁም ዩኒቨርስቲው ባለሙያ አቶ አማን ኤባ በጋራ በመሆን የስታዲየሙን ነባራዊ ሁኔታን ተዟዙረው መመልከታቸውን አውቀናል።

የጉብኝታቸው መሠረታዊ ምክንያት የጅማ ዩኒቨርስቲ ሜዳን ወደ ፊት ኢንተርናሽናል ስታዲየም እንዲሆን እና የካፍን ስታንዳርድ ለማሟላት ምን ማድረግ እንደሚገባቸው ከባለሙያው ምክረ ሀሳብ ለመቀበል እንደሆነ ሰምተናል።

የጅማ ዩኒቨርስቲው የቦርድ አመራሮች እና የከተማው አስተዳደር ከወዲሁ ስታዲየሙ ኢንተርናሽናል ሜዳ እንዲሆን አቅደው ለመስራት በካፍ ባለሙያ ምክረ ሀሳብ መቀበላቸው መልካም ጅምር ሲሆን የተቀበሉትን ምክረ ሀሳብ መነሻ በማድረግ በቅርቡ ደረጃ በደረጃ ወደ ትግበራ እንደሚገቡ ለማወቅ ችለናል።