የ2013 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ክለብ የሆነው ፋሲል ከነማ በልዩ ይዘት የተዘጋጀውን ዋናውን ዋንጫ የሚረከብበት ቀን ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች።
አስራ ሦስት ክለቦች በተሳተፉበት የ2013 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 54 ነጥቦችን በመሰብሰብ የበላይ ሆኖ ያጠናቀቀው ፋሲል ከነማ በልዩ ሁኔታ የተዘጋጀውን ዋንጫ እስካሁን ድረስ እንዳልተበረከተለት ይታወቃል። በተለያዩ ምክንያቶች ዘግይቶ ወደ ሀገራችን የገባው ሀገራዊ ይዘት ያለው ዋንጫም በአሁኑ ሰዓት በከፍተኛ ጥበቃ ስሙ ባልተገለፀ ባንክ እንደሚገኝ ሲታወቅ ለሊጉ አሸናፊ ፋሲል ከነማም መቼ እንደሚሰጠው አውቀናል።
በዚህም የዘንድሮ የሊጉ የውድድር ዘመን የፊታችን እሁድ በሀዋሳ ከተማ የሚጀመር ሲሆን ፋሲል ከነማ ደግሞ የመጀመሪያ ጨዋታውን ረቡዕ ያደርጋል። ክለቡም ረቡዕ ጥቅምት 10 በ9 ሠዓት ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ዓምና ሊጉን ያሸነፉበትን ዋንጫ እንደሚረከብ አረጋግጠናል። ዋናውን ዋንጫ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ከተረከበ በኋላ ወዲያው እንደሚመልስ ያወቅን ሲሆን ሬፕሊካው ግን ተዘጋጅቶ እንዳለቀ በቋሚነት እንደሚሰጠው ተነግሮናል።