የክለቦች የውድድር ዘመን ቅድመ ዳሰሳ | ጅማ አባ ጅፋር

ቀጣዩ የውድድር ዘመን ዳሰሳ ትኩረታችን የሚሆነው ጅማ አባ ጅፋር ነው።


ጅማ ከተማ ከከፍተኛ ሊጉ ባደገበት 2010 ዓመት ስያሜውን ወደ ጅማ አባ ጅፋር ቀይሮ በተሳተፈበት ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮን ሆኗል። በቀጣዩ የውድድር ዓመት ከፍተኛ የስብስብ ለውጥ አድርጎ ከደካማ የአህጉራዊ ተሳትፎ በኋላ በሊጉ ቢያንስ ስጋት ሳይጋረጥበት አምስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። በተሰረዘው የ2012 ውድድር ዓመት ላይ መጉላት የጀመሩት ችግሮቹ ግን መባባሳቸውን ቀጥለው ዓምና ዳግም ወደ ከፍተኛ ሊግ እንዳይመልሱት ያደረገው የትግራይ ክልል ክለቦች በሊጉ ያለመቀጠል አጋጣሚ ብቻ ነበር። በአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ጀምሮ በአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም በተጠናቀቀው ዓመት ጅማ ከውጤት መጥፋት በተጨማሪ ስሙ ከተጨዋቾች ደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅም ክፍያ ጋር እየተያያዘ በሜዳም ከሜዳም ውጪ ሲፈተን ቆይቷል። በውጤት ሲታይ 15 ነጥቦች ይዞ 12ኛ የወራጅ ቀጠና ደረጃ ላይ ቢጨርስም በማሟያ ውድድሩ ሦስተኛ ሆኖ በማጠናቀቅ ዘንድሮም በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለመታየት በቅቷል። 2014 ላይ በስብስብ እና በአሰልጣኝ ለውጥ የምንመለከተው ጅማስ ምን መልክ ይኖረዋል? የሚለውን ጉዳይም እንዲህ ተመልክተነዋል።

የማሟያ ውድድሩ ከተጠናቀቀ በኋላ ለቀጣዩ ዓመት በቶሎ መሰናዳት የጀመረው ጅማ አባ ጅፋር ከሌሎች ክለቦች ቀደም ብሎ አዲሱን አሰልጣኙን አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን አስተዋውቋል። አሰልጣኙ በሀዲያ ሆሳዕና ረዳታቸው ከነበሩት አሰልጣኝ ኢያሱ መርሐፅድቅ (ዶ/ር) እንዲሁም ከነባሩ ምክትል አሰልጣኝ የሱፍ ዓሊ እና ከግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ መሀማድ ጀማል ጋር አብረው የሚሰሩ ይሆናል። በተጨማሪ ሰናይ ይልማ በህክምና ባለሙያነት እንዲሁም ናስር አባዲጋ በበድ መሪነት ከክለቡ ጋር እናያቸዋለን።

ለጅማ አይረሴ ከነበረው የቻምፒዮንነት ዓመት በኋላ ቁልፍ ሚና ኖሯቸው የቀጠሉት አምበሉ ኤልያስ አታሮ እና አማካዩ ንጋቱ ገብረሥላሴን ጨምሮ በርካታ ተጫዋቾች ከምዕራቡ ክለብ ጋር ተለያይተዋል። ይህም ጅማን በቁጥር የበዙ ተጫዋቾችን በማስፈረም ቀዳሚ ያደረገውን ክረምት እንዲያሳልፍ አድርጎታል። ከዝውውሮቹ ውስጥ አዲሱ ግብ ጠባቂ አባላቱ ዮሐንስ በዛብህ፣ ለይኩን ነጋሽ እና ታምራት ዳኜ ይጠቀሳሉ። ተስፋዬ መላኩ፣ ሚኪያስ ግርማ፣ ሸመልስ ተገኝ፣ አስናቀ ሞገስ እና የአብስራ ሙሉጌታ በተከላካይ መስመር መስዑድ መሐመድ፣ ዳዊት እስጢፋኖስ፣ ኢዮብ ዓለማየሁ ፣ አድናን ረሻድ ፣ አልሳህሪ አልማህዲ እና ካሜሩናዊው ሮጀር ማላ በአማካይነት ጅማን ሲቀላቀሉ ዳዊት ፍቃዱ፣ መሐመድኑር ናስር፣ በላይ ዓባይነህ እና ዱላ ሙላቱ ደግሞ የፊት መስመሩን ለመምራት ጅማ ደርሰዋል። በዐምናው እና በዘንድሮው የጅማ ስብስብ ውስጥ የሚናገኛቸው ተጫዋቾች ወንድምአገኝ ማርቆስ፣ ኢዳላሚን ናስር፣ ሱራፌል ዐወል፣ ሮባ ወርቁ እና ቤካም አብደላ ብቻ ሆነዋል። ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ በወጣቶች እና ስፖርት አካዳሚ ልምምዱን እየሰራ በነበረበት ወቅት የሙከራ ዕድል ይገኙ የአካዳሚው ታዳጊዎች (ፎቶ ከታች) ጥሩ ጊዜ የሚኖራቸው ከሆነ በቡድኑ ውስጥ የመካተት ዕድል ይኖራቸዋል።

አዲሱን ስብስብ እንደ ቡድን አዋህዶ ለፉክክር የማብቃት ኃላፊነት የተጣለባቸው አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ስለክረምቱ ዝውውሮች ሲናገሩ “ክለቡ ውስጥ የነበሩ አብዛኞቹ ተጫዋቾች በብቃት ማነስም በኮንትራት ማለቀም ምክንያት ለቀዋል። በእኛም በኩል ሦስት የተቀነሱ ተጫዋቾች ነበሩ። ስለዚህ ከአዲስ ፈራሚዎቹ ውስጥ ወጣቶችም ልምድ ያላቸውም አሉ። በዛ መልኩ ቡድኑን ለማጠናከር ተሞክሯል።” ይላሉ።

አሰልጣኙ በሊጉ ውስጥ ብዙ እንደመቆየታቸው በየዓመቱ አዲስ ቡድን ማዋቀር ከባድ መሆኑ አይጠፋቸውም። ከአስተያየታቸውም የክለቦች ዕቅድ ጤናማ ሆኖ በተረጋጋ አኳኋን ቡድን መስራት ቀጠል አድርጎም በጎደለው ላይ መጠነኛ ጥገና እያደረጉ ወደ መጨረሻ ግብ መቀጠል ምኞታቸው ይመስላል። ይህንን በሚጠቁመው ሀሳባቸው እንዲህ ሲሉ የችግሩን መነሻ እና መፍትሄ ጠቆም አድርገዋል። “ከባድ ነው !ብዙ ጊዜ ይሄ ጉዳይ የሚነሳው ከአሰልጣኞች አጭር ቆይታ ጋር ተያይዞ ነው። በተመሳሳይ ተጫዋቾችም የሚፈርሙት አንድ ወይ ሁለት ዓመት ነው። ያ ደግሞ ክለቡን ተጠቃሚ አያደርግም። አሁን ጥሩ መስመር እየያዘ ያለው ኢትዮጵያ ቡና ነው። ሁሉም ክለቦች በዛ መንገድ ቢቀጥሉ ይህንን ችግር ይቀርፋሉ ብዬ አስባለሁ።”

የዘንድሮው የቡድን ስብስብ ሲታይ ልምድ ያላቸውን ከወጣቶች ከማካተት አንፃር መልካም የሚባል ነው። ለአብነት ከፊት ዳዊት ፍቃዱን መሀመድኑር ናስር እና ቤካም አብደላ መሀል ላይ በቡና እና ሰበታ የሚታወቀው የዳዊት መስዑድ ጥምረት ከአድናን እና ኢዮብ ጋር ከኋላም ተስፋዬ መላኩ፣ ሽመልስ ተገኝን ከእነ ኢዳላሚን ናስር ጋር ማሰባጠሩ ማሳያ ይሆናል። አሰልጣኝ አሸናፊ ይህንን ስብጥር ስለሚጠቀሙበት አግባብ ሲያነሱ “ሁሉንም ልምድ ያላቸውን በአንዴ ላንጠቅምባቸው እንችላለን። እንደጨዋታው ሁኔታ እንገለገልባቸዋለን። ሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ወጣቶቹም አብረው ልምድ እያገኙ ሲሄዱ እነሱንም የማሳተፍ ሀሳብ ነው ያለኝ።” በማለት ሀሳባቸውን ያስቀምጣሉ።

ከስብስቡ ጋር በመልካም ጎኑ ከሚነሳው የዕድሜ ስብጥር በተቃራኒው የጥልቀት ጉዳይ ትኩረት የሚያሻው ነጥብ ነው። አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በአሁኑ ሰዓት በስብስባቸው የሚገኘው የተጫዋች ቁጥር 22 ብቻ መሆኑ፤ በተለይም ተፈጥሯዊ የመሐል ተከላካይ እጥረት መኖሩ ሲታይ ቢያንስ እስከ ውድድር ዘመኑ አጋማሽ የዝውውር መስኮት ድረስ ሊቸገሩ እንደሚችሉ ይገመታል።

ከዚሁ ሀሳብ ተነስተን ግብ ጠባቂዎችን ክፍል ስንመለከት ግን ጅማ ክፍተት ሊኖርበት እንደሙችል እንረዳለን። በቡድኑ የዓምና ደካማ ጊዜ ውስጥ ደምቆ የወጣው አቡበከር ኑሪን ያጣው እና በመጨረሻ ሰዓት ሮበርት ኦዶንካራን ለማግኘት ያደረግው ጥረት ያልተሳካለት ጅማ የግብ ዘብ ስብጥሩ ከልምድ አኳያ ሲፈተሽ አስተማማኝ አይመስም። ዮሀንስ በዛብህ ጥሩ ክህሎት ቢኖረውም ለረጅም ጊዜ በነበረባቸው ክለቦች ዋና ተመራጭ ሳይሆን መቆየቱ በሲዳማ ቡና የምናውቀው ለይኩን ነጋሽ እና በ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ለመመረጥ በቅቶ የነበረው ታምራት ዳኜ ልምድ አናሳነት ለክፍተቱ በምክንያትነት የሚነሳ ነው።

ጅማ አባ ጅፋር የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ነሀሴ 28 ላይ በቢሾፍቱ ነበር የጀመረው። አካልብቃት እና የውህደት ሥራዎች ላይ ትኩረቱን አድርጎ ሲሰራ ቆይቶም ለአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ጨዋታዎች ወደ መዲናዋ እና ወደ ባህር ዳር ያቀናባቸው አጋጣሙዎች ተፈጥረዋል። በውድድሩም አምስት ጨዋታዎችን አድርጎ በአራተኛ ደረጃነት አጠናቋል።

በክረምቱ የዝግጅት ውድድር ላይ የተመለከትነው ጅማ አባ ጅፋር ከራሱ የግብ ክልል በጣም ርቆ መከላከልን የማይመርጥ ግን ደግሞ በቶሎ ኳሶችን ወደፊት በማድረስ ጥቃት ለመሰንዘር የሚሞክር ዓይነት ነበር። አሰልጣኝ አሸናፊ አጨዋወታቸው እንደተጋጣሚ አቀራረብ ሊወሰን እንደሚችል ያነሱልን መሆኑ እና አማካይ ክፍሉ ላይም ለኳስ ቁጥጥር የተመቹ ተጫዋቾችን መያዙ ደግሞ ቡድኑ ሌላ ኳስ መስርቶ ለመጫወት የመሞከር አዝማሚያ ሊኖረው እንደሚችል ያመለክታል። በጥልቀት መከላከልን ስናነሳ ግን ቡድኑ በመሀል ተከላካይ ቦታ ላይ ያሉት አማራጮች በቁጥር ማነስ እንቅፋት እንዳይሆንበት ያሰጋል። የሊጉን ርዝማኔ እና በሌሌች ክለቤች ስብስብ ውስጥ ያሉ ምርጫዎችን ከግምት ስናስገባ ደግሞ አሰልጣኝ አሸናፊ እንደ አሳሪ አልማህዲ እና ኢዳላሚን ናስር ያሉ ከአንድ በላይ ሚና ያላቸው ተጫዋቾችን በመጠቀም ቦታውን የመሸፈን አማራጭን ሊጠቀሙ ይችላሉ።

ቀናት በቀሩት የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ነጥረው ሊወጡ የሚችሉ ተጫዋቾችን ስናስብ ጅማን ከግምት ማስገባት የግድ ይላል። አምና ብልጭ ብለው ከነበሩ ወጣቶች ውስጥ የሚጠቀሰው ቤካም አብደላ ደግሞ አንዱ የትኩረት ነጥብ ነው። ከዕድሜው ለጋነት አንፃር በብዙ መለኪያዎች ተሻሽሎ እንዲመጣ የሚጠበቅበት ቤካም ከብልጭታነት ያለፈ ዓመት እንዲኖረው ይጠበቃል። ከአካል ብቃት ዕድገት ባለፈ አምና ተቀይሮ በገባባቸው ጨዋታዎች ላይ ጎልቶ የመውጣቱን ያህል በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ሲካተት ተዕዕኖው አለመታየቱ ዋነኛ የመሻሻል መመዘኛው ሊሆን ይችላል።

ከኢትዮጵያ መድን የተገኘው መሀመድኑር ናስርም ሌላው ተጠባቂ ተጫዋች ነው። ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊያደርገው የነበረው ዝውውር ሳይሳካ የከፍተኛ ሊግ ክለብን ውል በማፍረስ ወደ ጅማ ያቀነው አጥቁው በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ ጥሩ ተስፋን አሳይቷል። በሊጉ በቦታው የመጀመሪያ ተመራጭ ሆኖ መገኘት ዕድሉን ተጠቅሞ ድንቅ ግብ አስቆጣሪነቱን ዳግም ማስመስከርም ከተጫዋቹ የሚጠበቅ ስኬት ይሆናል።

የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የቅርብ ዓመታት ቡድን አዳማ ከተማ እና የአምናውን ሀዲያ ሆሳዕናን ለተመለከተ ጅማ አባ ጅፋርን በአካል ብቃት እና በመከላከል አደረጃጀት ተሻሽሎ እንደሚቀርብ መናገር ይችላል። አዳማ እና ሆሳዕናን በውጤት ከመዘንናቸው ደግሞ አሰልጣኙ ጅማን ወደ ዋንጫ ፉክክሩ ሊያስጠጉት ይችላሉ የሚል ዕምነት ያሳድራል። በዛው ልክ የስብስቡን አዲስነት እና ዓምና የነበረበትን ሁኔት ከግምት ላስገባ ደግሞ ክለቡን በሊጉ ማቆየት በራሱ ስኬት እንደሆነ ይረዳል። የአሰልጣኙ ሀሳብም የሚያደላው ወሰ ሁለተኛው ፍምት ነው። “በተከታታይ በወራጅ ቀጠና ውስጥ የነበረ ቡድን ነው። ከዚህ ለማትረፍም ነው የምሰራው። ያው ክለቡ የሚፈልገው ነገር አለ። እርግጠኛ ነኝ ይወርዳል ብዬ አልጠብቅም። ዋናው አላማ ቡድኑን ከመውረድ ማትረፍ ነው።”

ይህ ውጥን ዕውን ሆኖ እንዲታይ ግን የሜዳ ላይ ቡድኑ ጨዋታዎችን አሸንፎ እንዲወጣ መጠበቁ ብቻውን በቂ አይደለም። ነገሮች ሰምረው ተፎካካሪ ቡድን ቢቦን እንኳን ያለፉት ዓመታት የፋይናንስ ችግሩ ካልተስተካከል በዓመቱ ጉዞው ላይ የሚኖረውን አሉታዊ ተፅዕኖ መገመት አያዳግትም። ይህ ሁኔታ አሁን ላይም እየተናፈሰ መገኘቱ ደግሞ ስጋቱን ይበልጥ ያጠናክረዋል። የጅማ አባ ጅፋር የ 2014 ዓመት በየትኛው አቅጣጫ ይጓዛል የሚለውን ጥያቄ የሚመልሱት ቀናት ግን በቁጥር ጥቂት ናቸው። ቡድኑ የውድድሩን መክፈቻ ጨዋታ ጥቅምት 7 ላይ ከሀዋሳ ከተማ በማድረግ ሩጫውን ይጀምራል።

የጅማ አባ ጅፋር የ2014 ስብስብ

ግብ ጠባቂዎች

1 ዮሐንስ በዛብህ
16 ለይኩን ነጋሽ
90 ታምራት ዳኜ

ተከላካዮች

2 ወንድማገኝ ማርቆስ
15 ተስፋዬ መላኩ
18 የአብስራ ሙሉጌታ
20 በላይ አባይነህ
21 ኢዳላሚን ናስር
19 ሽመልስ ተገኝ
33 አስናቀ ሞገስ
99 ሚኪያስ ግርማ

አማካዮች

4 አሳሪ አልማሀዲ
3 መስዑድ መሐመድ
7 እዮብ አለማየሁ
8 ሱራፌል ዐወል
10 ዳዊት እስጢፋኖስ
12 ሮጀር ማላ
14 አድናን ረሻድ

አጥቂዎች

9 ዱላ ሙላቱ
11 ቤካም አብደላ
17 ዳዊት ፍቃዱ
24 መሐመድኑር ናስር
27 ሮባ ወርቁ