የኢትዮጵያ እግርኳስ ደጋፊዎች ማኅበራት ጥምረት የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባዔውን ሊያካሂድ ነው

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች ደጋፊዎች ውህደት የተቋቋመው የኢትዮጵያ እግርኳስ ደጋፊዎች ማኅበራት ጥምረት ህጋዊ እውቅናውን ለማግኘት የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባኤውን ከነገ በስትያ ያካሂዳል።

ከሁለት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች መካከል የሚገኙ ደጋፊዎች የመሰረቱት የኢትዮጵያ እግርኳስ ደጋፊዎች ማኅበራት ጥምረት ኢ-መደበኛ በሆነ መንገድ የተለያዩ ሥራዎችን ሲሰራ እንደነበር ይታወሳል። በተለይ ኮቪድ የ2012 የውድድር ዓመትን ከማቋረጡ በፊት በስታዲየሞች የነበረውን የፀጥታ ችግር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ሲያስተካክል የነበረው ይህ ጥምረት ምንም እንኳን ዓምና በኮቪድ-19 ምክንያት በስታዲየሞች የሚፈጠሩ ነገሮችን ለማስተካከል ዕድሉን ባያገኝም ዘንድሮ በሊጉ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ መመለሳቸውን ተከትሎ የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶችን እየሰራ ይገኛል።

ከዚህ በፊት ህጋዊ እውቅና የሌለው ይህ ጥምረት ከወራት በፊት በኢፌዴሪ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ህጋዊ እውቅናውን ለማግኘት ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና ኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ጋር ንግግር ሲያደርግ ነበር። ይህንን ተከትሎም ጥምረቱ ሁሉንም መስፈርቶች በማሟላት የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባኤውን በማድረግ አመራሮቹን ለመምረጥ እና በኢፌዴሪ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ህጋዊ እውቅና ለማግኘት የፊታችን ቅዳሜ ሀዋሳ ላይ የመጀመሪያ ጉባኤውን እንደሚያደርግ ተገልጿል። በጠቅላላ ጉባኤው ላይ የሚሳተፉ የየክለቦቹ የደጋፊ ማኅበራት ተወካዮችም ነገ ሀዋሳ በመግባት ከሲዳማ ቡና ደጋፊዎች ማኅበር የተዘጋጀላቸውን ፎርም በመቀበል በሚዘጋጅላቸው ማረፊያ እንዲያርፉ እና ቅዳሜ ከ3 ሰዓት ጀምሮ በሚደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቧል።

ከጠቅላላ ጉባኤው መጠናቀቅ በኋላ ደግሞ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ከኮቪድ-19 ጋር ተያይዞ ደጋፊዎች ወደ ስታዲየም ሲገቡ ሊያደርጓቸው ስለሚገባ ነገሮች እና ስለ አደጋገፍ ሁኔታዎች የአንድ ሰዓት ስልጠና እንዳዘጋጀ ተነግሮናል።