የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለክልሎችና ለከተማ መስተዳድሮች ከ15 ዓመት በታች ለሆኑ ወንድና ሴት ታዳጊ ወጣቶች የስልጠና ኘሮጀክቶች የመክፈቻ ይፋዊ ኘሮግራም በኢሊሊ ሆቴል አካሂዷል።
በጎ ዓላማ ይዞ በተነሳው በዚህ ትልቅ ፕሮጀክት የመክፈቻ ፕሮግራም ላይ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ፥ የሥራ አስፈፃሚ አባላት፥ የክልል የከተማ አስተዳደር እና የእግርኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች እና የስልጠናው አሰልጣኞች ታድመዋል። አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ከትግራይ ክልል ውጭ ሁሉም የክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች በተመረጡ ከተሞች በሴት እና በወንድ 750 በላይ ሰልጣኞች አቅፈው ለአራት ዓመት የሚቆይ ስልጠና ሲሆን አንድ ክልል በወንድና በሴት 30 ሰልጣኞች ሲይዝ ከ30 ሰልጣኞች መካከል አምስት የሴት አምስት የወንድ ግብጠባቂዎች ማቀፍ እንደሚገባ ተገልፆል።
በጥቅሉ 27 ፕሮጀክት የተከፈቱበት ይህ ፕሮጀክት ስያሜ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፓይለት ከ15 ዓመት በታች ፕሮጀክት ይሰኛል። ፌዴሬሽኑ ፕሮጀክቱ እንዲከፈት ከዓመታት በፊት አቅዶ የአሰልጣኞችን መረጣና ስልጠና ሲሰጥ ቆይቷል። በዛሬው የመክፈቻ ፕሮግራሙ ላይ የፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ዳሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ፍራንኮ የስልጠናውን ዓላማ በሰፊው ያብራሩ ሲሆን ፌዴሬሽኑ ለሰልጣኞች የተሟላ ትጥቆች እና የአሰልጣኞቹን ወርሀዊ ደሞዝ እንደሚከፍል እንዲሁም የተለያዩ የማሻሻያ ስልጠናዎችን የሚያዘጋጅ እንደሆነ፤ የቀረው በሰልጣኞች ወላጅ የሚሸፈን መሆኑን ገልፀዋል። ፕሮጀክቱ በሁሉም ቦታ አንድ ዓይነት የጨዋታ ዘይቤ “ኳስን መስርቶ መጫወት” መሠረት ያደረገ ስልጠና እንደሚሰጥ ሲታወቅ ፌዴሬሽኑ የስልጠናው ሒደት በታቀደለት መንገድ እየተከናወነ መሆኑን ክትትል ማሻሻያ ያደርጋል ተብሏል።
ስልጠናው በሳምንት ሦስት ጊዜ፤ ለሰማንያ ደቂቃ የሚሰጥ ሲሆን በምን መልኩ እየቀጠለ መሆኑን (የታሰበለትን ግብ እየመታ መሆኑ ለመገንዘብ) ሁሉም ፕሮጀክቱ ባለበት ከተማ እንደየ አስፈላጊነቱ የውስጥ ውድድር እንዲያደርጉ አቅጣጫ ተቀምጧል። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንም በዓመት አንድ ጊዜ በተመረጠ ቦታ የምዘናው በውድድር እንደሚያደርግ ታውቋል።
በመክፈቻው ፕሮግራም ላይ መልዕክት ያስተላለፉት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ” አውሮፓውያን በስድስት ዓመት ነው የታዳጊ ፕሮጀክት የሚጀምሩት። እኛ አሁን ቶሎ ጀመርን በማለት ከአስራ አምስት ዓመት በታች ፕሮጀክት ነው የምናወራው። ልዮነቱን እና ችግራችንን እናውቀዋለን። ይህን ችግር ለመፍታት ፌዴሬሽኑ ተገዶ የገባበት እና ለሀገር ማሰብ አለብን። የዛሬ አራት ዓመት በወንድም በሴትም ለኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን መድረስ የሚችል ትውልድ ለመፍጠር ይህ ፓይለት ፕሮጀክት አስበናል። በአራት ዓመት ውስጥ በሚሰጠው ስልጠና በአግባቡ የማይከውኑ ካሉ እነርሱን እያወጣን በአግባቡ የሚሰሩትን እየደገፍን እንሄዳለን። ይህን ደግሞ በተገቢው ሁኔታ የምንከታተል ይሆናል” ያሉት ፕሬዝደንቱ በመጨረሻም ”ሁሉም የክልል ስፖርት ኮሚሽን እና ፌዴሬሽን አመራሮች ይህን ፕሮጀክት እንደ ልጃቹ ተመልክታቹ የትውልድ ቅብብሎሹን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።” ብለዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአየር ኃይል እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች ጎላ ብርሀኑ ከአሜሪካ በመምጣት ለሁለት ፕሮጀክቶች ዓመታዊ ወጪን ለመሸፈን ቃል መግባታቸውን በቦታው በመገኘት አረጋግጠዋል።
በመጨረሻም ለሁሉም ፕሮጀክት የሚሆን የስልጠና ትጥቆች በአሰልጣኞቹ ተወካይ አማካኝነት ከአቶ ኢሳይያስ ጂራ እጅ ተረክበው መርሐግብሩ ተጠናቋል።