የጦና ንቦቹን የዝግጅት እና የመጪው ውድድር ጊዜ መልክ በዚህ መልኩ ቃኝተናል።
2006 ላይ ወደ ሊጉ የመጣው ወላይታ ድቻ ዘንድሮ ስምንተኛ የውድድር ዓመቱን ይጀምራል። ያለፈው ዓመት ግን በውስን በጀት ለሚንቀሳቀሰው ድቻ ቀላል ሆኖ የጀመረ አልነበረም። ከአሰልጣኝ ደለለኝ ደቻሳ ጋር ጀምሮት በነበረውን ሊግ ተከታታይ ሽንፈቶችን አስተናግዶ አደጋ ላይ ወድቆ ነበር። ክለቡ በወሰነው ውሳኔ ከሰባተኛው ሳምንት በኋላ አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራውን ወደ ኃላፊነት በማምጣት እና በውድድሩ አጋማሽ ተጨማሪ ተጫዋቾችን በማስፈረም ከአደጋው ማገገም ችሏል። ከኮቪድ ጋር በተገናኘ በርከት ያሉ ተጫዋቾቹን መጠቀም ያልቻለባቸው የመጨረሻ ጨዋታዎች የነበሩ ቢሆንም ቡድኑ በአስገራሚ ተነሳሽነት ውድድሩን ሲያጠናቅቅ ከወራጅ ቀጠናው በአስር ነጥቦች ርቆ 8ኛ ደረጃን በመያዝ ጨርሷል። የዘንድሮው ወላይታ ድቻ ግን አምና ዓመቱን በዚህ መልኩ ከጨረሰው ቡድን በብዙ መልኩ ተቀይሮ የምናየው ይሆናል።
በአስተዳደራዊ ለውጥ ክረምቱን የጀመረው ወላይታ ድቻ አቶ ወንድሙ ሳሙኤልን በሥራ አስኪያጅነት ሾሟል። (ግለሰቡ በቡድን መሪነትም የሚያገለግሉ ይሆናል) ክለቡ በቀጣይ ባደረገው ያልተጠበቀ ለውጥም በሊጉ እንዲቆይ ካስቻሉት አሰልጣኙ ጋር በጥቅማ ጥቅም ጉዳዮች ከስምምነት ባለመድረሱ በጅማ አባ ጅፋር ዓመቱን የጨረሱት አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያምን በአንድ ዓመት ውል ወደ ኃላፊነት አምጥቷል። በምክትልነት አሰልጣኝ ጣሰው ታደሰን በግዛቸው ጌታቸው ምትክ የመደቡት ወላይታ ድቻዎች ከግብ ጠባቂዎቂዎች አስልጣኛቸው ዘላለም ማቲዮስ ጋር ግን በአዲሱ የውድድር ዓመትም አብረው የሚዘልቁ ይሆናል። የሀክምና ባለሙያዎቹ አበራ መና እና ባረካ ባካሎም ከቡድኑ ጋር የሚከርሙ አባላት ናቸው።
ወላይታ ድቻ በዝውውር መስኮቱ የመሸፈን ግዴታ ውስጥ የገባባቸው ክፍተቶች ቀላል የሚባሉ አይደሉም። ክለቡ ዐምና በሊጉ ለመቆየት በውድድሩ አጋማሽ ካስፈረማቸው ተጫዋቾች ውስጥ አሁን ላይ የቀረ የለም። በዋነኝነት ዳንኤል አጃዬ፣ ኢዙ አዙካ፣ ጋቶች ፓኖም፣ ነፃነት ገብረመድህን ፣ ዮናስ ግርማይ እና ዲዲዬ ለብሪ ከሶዶው ክለብ ጋር ተለያይተዋል። ከዚህም በላይ በቡድኑ ውስጥ ወሳኝ ሚና ኖሯቸው የዘለቁት እና ብዙ አገልግሎት ሊሰጡ ይችሉ የነበሩት የወጣት ቡድኑ ፍሬ የነበሩት ፀጋዬ ብርሃኑ፣ መሳይ አገኘሁ፣ በረከት ወልዴ እና ቸርነት ጉግሳም ወደተለያዩ ክለቦች አምርተዋል። በተጨማሪም መክብብ ደገፉ፣ ኢዮብ ዓለማየሁ እና ተመስገን ታምራትም ከክለቡ ጋር ፍቺ ፈፅመዋል። ይህ ሁኔታ ቀጥሎ ክለቡ ችግር ውስጥ ሊወድቅ ይችላል የሚል ስጋት የነበረ ቢሆንም ድቻ በቀጣይ ጊዜያት ባደረጋቸው እንቅስቃሴዎች በተደጋጋሚ በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ያካትታቸው ከነበሩት ደጉ ደበበ፣ ያሬድ ዳዊት፣ እንድሪስ ሰዒድ፣ አናጋው ባደግ፣ መልካሙ ቦጋለ እና ወደ ሀዲያ ሆሳዕና ለማምራት ከፃፍ ደርሶ የነበረው ስንታየሁ መንግሥቱን ውል በማራዘም ማቆየት ችሏል።
በለቀቁበት ተጫዋቾች ምክንያት የተፈጠሩትን ቀሪ ክፍተቶች ለመድፈን እስከ ሐምሌ አጋማሽ ዘግይቶ ወደ ገበያ የወጣው ወላይታ ድቻ የቀድሞው ግብ ጠባቂው ወንድወሰን አሸናፊ እና ጽዮን መርዕድን በብረቶቹ መሐል ሾሟል። በቦታው የወጣቱ ቢኒያም ገነቱ ውልም ታድሷል። ከዚህ ውጪ ሀብታሙ ንጉሤ፣ ምንይሉ ወንድሙ እና ቃልኪዳን ዘላለም የቡድኑ አዳዲስ አጥቂዎች ሲሆኑ አማካይ ክፍል ላይ ንጋቱ ገብረሥላሴ፣ አዲስ ህንፃ እና ፍሰሐ ቶማስ ከኋላ ደግሞ በረከት ወልደዩሐንስ እና ዘካሪያስ ቱጂን በስብስቡ ተካተዋል።
በ2013ቱ የውድድር ዓመት እንደ ወላይታ ድቻ የወደፊት ተስፋዎችን ያሳየን ቡድን አለ ለማለት ያዳግታል። በዚያ ስብስብ ውስጥ ከታች አድገው ውስን ዓመታትን በዋናው ቡድን ውስጥ የቆዩ ተጫዋቾች የአሰላለፉ ቀዳሚ ተመራጮች ሆነው መመልከት ስንችል አደጋ ላይ በወደቀባቸው ጨዋታዎች እንደ ቢኒያም ፍቅሩ፣ መልካሙ ቦጋለ፣ መሳይ ኒኮል፣ አበባየሁ አጅሶ መሰል ወጣቶች ከልምዳቸው በላይ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ተመልክተናል። ይህ ልምድ ያለው ክለቡ ዘንድሮም በበጀት ምክንያት ውድድር እስከማቋረጥ ከደረሰው ወጣት ቡድኑ ውስጥ ስምንት ተጫዋቾችን አሳድጓል። (አንዳንዶቹ ዐምና በዋናው ቡድን ጨዋታ አድርገዋል) በዚህም መሠረት ግብ ጠባቂው አብነት ይስሀቅ ተከላካዮቹ ዮናታን ኤልያስ፣ አዛርያስ አቤል፣ ቢኒያም አበበ፣ ኬኔዲ ከበደ እንዲሁም አማካዮቹ ውብሸት ወልዴ፣ ዘላለም አባቴ እና ሳሙኤል ጃጊሶ በ2014ቱ የቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ራሳቸውን የማሳየት ዕድሉ ያላቸው ወጣቶች ሆነዋል።
“ከወልቂጤ ጋር በነበረን የወዳጅነት ጨዋታ 21 ተጫዋቾችን ተጠቅመናል። በሁለተኛው ቡድን ውስጥም አብዛኞቹን ወጣት ተጫዋቾች ለመጠቀም ሞክረናል። የውዴታ ግዴታም ስለሆነ በአረንጓዴ እና በቢጫ ቴሳራ በበድኑ ውስጥ ተካተዋል። በፕሪምየር ሊጉ ሰፊ ልምድ ያላቸው 15 አካባቢ ነው የሚሆኑት። ስለዚህ ወጣቶቹ ተካተው የማይጫወቱበት ምክንያት አይኖርም፤ በስፋት ዕድል ያገኛሉ ብዬም ነው የምጠብቀው።” የሚለው የዋና አሰልጣኙ ሀሳብም እንደአምናዎቹ ሁሉ የዘንድሮዎቹም ወጣቶች ጎልተው የሚወጡበት ዕድል ከፊታቸው እየጠበቃቸው እንደሆነ የሚያሳይ ነው።
የወላይታ ድቻ የዝውውር ሂደት የለቀቁ እና አዲስ የመጡትን በማነፃፀር ከተመዘነ የጥራት ደረጃው ጥያቄ ያስነሳል። ” የለቀቁት ተጫዋቾች ብዛታቸው ብቻ ሳይሆን ለክለቡ ቁልፍ እና ወሳኝ ተጫዋቾች ነበሩ። ያ ግን አንዴ የሆነ ነገር ስለሆነ አሁን ያሉን ተጫዋቾችን ሞራል ጠብቀን እያነሳሳን በሥልጠና በማዳበር ለመጠቀም ነው የምናስበው።” የሚሉት አሰልጣኝ ፀጋዬም ይህንን እውነታ ይጋራሉ። ክለቡ አዳዲስ ተጫዋቾቹን ሲያስፈርም የሌላ ሀገር ዜግነት ባላቸው ተጫዋቾች ላይ ቀደም ሲል ወደነበረው አቋም ተመልሷል። ከዚህ በፊት በሀገር በቀል ተጫዋቾች ብቻ ይጠቀም የነበረው ድቻ ከ2019ኙ የአፍሪካ ኮፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፎ በፊት እንዲሁም ዐምና በሊጉ ለመሰንበት ባደረገው ጥረት ውስጥ ብቻ የውጪ ሀገራት ተጫዋቾችን አዘዋወሮ ነበር። አሁን ግን ሙሉ ስብስቡ በኢትዮጵያውያን የተሞላ ሆኗል።
አሰልጣኝ ፀጋዬ የክለባቸውን የዝውውር ሒደት በጥቅሉ ሲገመግሙ የአዳዲስ ተጫዋቾች ቁጥር ከሌሎች ክለቦች ጋር ሲነፃፀር ካለመጋነኑ በተጨማሪ የመጡት ተጫዋቾች በአመዛኙ በነበሩባቸው ክለቦች ቋሚ ተመራጮች ያልነበሩ መሆናቸውን ያነሳሉ። “ቡድኑ በዝውውር በኩል ዘንድሮ ለየት ብሎ ነው የቀረበው፤ ሙሉ ስብስቡን አልቀየረም። በፊት ከነበሩት ላይ የተወሰኑ በማካተት ነው የተከወነው። ያመጣናቸውም በፕሪምየር ሊጉ ብዙ ዕውቅና የሌላቸው አማካይ ደረጃ ላይ ያሉ ተጫዋቾችን ነው። በቁጥር ውስን ተጫዋቾች ናቸው። ከዚያ ውጪ ዘጠኝ ተጫዋቾች አሳድገን ነው ወደ ዝግጅት የገባነው።”
በሀሳብ ደረጃ የክለቡ ዝውውሮች ወጪ ከመቆጠብ እና በሀገር ውስጥ ወጣት ተጫዋቾች ላይ ከመመስረት አንፃር ይበል የሚያስብል ነው። ነገር ግን ያለፈው ዓመት ጠንካራ ጎኖቹን የሚያስቀጥል ስብስብ ወደ ዘንድሮው አላማሻገሩ ይበል የሚያሰኝ ተግባሩ አደጋንም ይዞበት እንዳይመጣ ያሰጋዋል። ይህንን ክፍተት በአስተማማኝ የቡድን ቅንጅት ከመሸፈን አንፃርም ቡድኑ በክረምት ውድድሮች ላይ ሳይካፈል መቅረቱ ፈተናውን ያከብደዋል። “ከባድ ነው እንደአዲስ የገቡ ተጫዋቾች ብዛት እና ጥራት ብቻ ሳይሆን የሚወስነው ቢያንስ ለማቀናጀት የወዳጅነት ጨዋታዎች ያስፈልጉ ነበር። አራት እና ከአራት በላይ ጨዋታዎችን ማድረግ ይፈልግ ነበር። ምክንያቱም ለመቀናጀት እና ለመዋሀድ ጊዜ ይፈጃል።” የሚለው የዋና አሰልጣኙ ሀሳብም ይህንን የሚያመለክት ነው።
ወላይታ ድቻ የቅድመ ውድድር ዘመን ዝግጅቱን ነሀሴ 17 በመቀመጫው ሶዶ ከተማ ነበር የጀመረው። እስከ ጳጉሜ 3 የመጀመሪያ ምዕራፍ ዝግጅቱን ሲከውን የአካል ብቃት እና የቅንጅት ሥራዎች ላይ ትኩረቱን አድርጓል። በእነዚህ ጊዜያት የሜዳ ችግር የነበረ በመሆኑ ከኳስ ጋር የነበሩ ልምምዶችን በአጫጭር ሜዳዎች ላይ ለመስራት መገደዱን አሰልጣኝ ፀጋዬ ጠቅሰዋል።
በበጀት መዘግየት ምክንያት የአዲስ አበባውም ሆነ የሀዋሳው ውድድሮች ያለፉት ድቻ “ከ 4-6 ጨዋታዎች ያስፈልጉን ነበር” ከሚሉት አዲሱ አሰልጣኙ ዕቅድ ጋር አልተጣጣመም። የቡድኑ የቅንጅት ሥራዎች ውጤት የተፈተነበት ብቸኛው የወዳጅነት ጨዋታ ሶዶ ላይ ከወልቂጤ ጋር የተደረገው እና ያለግብ የተጠናቀቀው ጨዋታ ነበር። ያ ጨዋታ የቡድናቸው የቅንጅት ደረጃ ገና መሆኑን ያሳያቸው አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ችግሩን ለማቃለል የሊጉን መቋረጥ ተስፋ አድርገዋል። “እግርኳስ በአጭር ጊዜ የምታመጣው ውጤት አይደለም ፤ እየገነባኸው የምትሄደው ነው። ከዚህ አንፃር ጊዜ እና ትዕግስት ያስፈልገዋል ባይ ነኝ። ውድድሩ ጀምሮ ሦስት ሳምንት ከተካሄደ በኋላ ወደ 25 ቀን ስለሚቋረጥ ቡድናችንን ይበልጥ አዋቅረን የምንመጣበት ሊሆን ይችላል። እንደዚያም ቢሆን ልዩ ትኩረት በማድረግ ሊጉ ላይ ጠንክሮ ለመቅረብ ማድረግ የሚገባንን እያረግን ነው። በታክቲክ አቀባበላችን ላይ ሠርተን በወሳኝ ጨዋታዎች ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ እንጫወታለን ብዬ አስባለሁ።”
አዳዲስ ፊቶችን ከመመልከት አንፃር የክለቡ የዝውውር ሒደት ለዘንድሮዎቹ ብቻ ሳይሆን ዐምና ፍንጭ ለሰጡትም በረከት ሊሆንላቸው ይችላል። እንደቢኒያም ፍቅሩ እና መልካሙ ቦጋለ ዓይነቶቹ ተጫዋቾች አጋጣሚውን ከተጠቀሙበት ዘንድሮ ይበልጥ ወሳኝ ወደመሆን የሚሸጋገሩበት አጋጣሚ ሊከፈት ይችላል። በግለሰብ ደረጃ ሌላው የሚነሳው ደጉ ደበበ ነው። የፅናት ምልክት የሆነው ደጉ አሁንም በቡድኑ ውስጥ መገኘት የተበራከቱት ወጣቶቹ በሜዳም ሆነ ከሜዳ ውጪ ላለው ስፖርታዊ ህይወታቸው ብሰለት የሚኖረው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ለቡድን ቅንጁቱም ቢሆን ሜዳ ላይ በእንቅስቃሴ ውስጥ አመራር የሚሰጥ መሰል ተጫዋች አስፈላጊ ነው።
በ2013ቱ ውድድር የትልቅነት ፍንጭ የሰጠው አጥቂው ስንታየሁ መንግሥቱ ሌላኛው የትኩረት ማዕከል ነው። ከጉዳት ጋር እየታገለ ባሳለፈው የውድድር ዓመት 14 ጨዋታዎችን ብቻ በቀዳሚ አሰላለፍ ውስጥ ተካቶ ቢጀምርም 11 ግቦችን አስቆጥሮ ሦስት ማመቻቸቱ እንደቀልድ ታይቶ የሚታለፍ አይደለም። ተጨዋቹ ከድቻ ባለፈ እንደ ሀገር የሚኖረው አበርክቶት በተስፋ እንዲጠበቀም ቀናቶች የቀሩት የዘንድሮው ውድድር በእግርኳስ ህይወቱ እጅግ ወሳኙ ይሆናል።
በእግርኳሳችን በወጣቶች ላይ ያለው ዕምነት ደካማነት ወደ ኋላ ለመቅረታችን ምክንያት ተደርጎ ሲነሳ ይሰማል። ይህንን ነጥብ በተግባር ለመፈተን ደግሞ የዘንድሮው የወላይታ ድቻ ስብስብ ጥሩ ማሳያ ይሆናል። ታድያ ድቻ ይህንን ሀሳብ በውጤት አጅቦት አሳማኝነቱን ያረጋግጣል ወይስ የሊጉን ፉክክር መቋቋም ይሳነዋል የሚለውን ጉዳይ አብረን የምናይ ሲሆን አሰልጣኝ ፀጋዬ ግን ይህንን ይላሉ።”ባለፉት ሦስት አራት ዓመታት የወላይታ ድቻ ቆይታ ይረጋገጥ የነበረው በመጨረሻ ጨዋታዎች ነበር። ዘንድሮ ደግሞ የገነባነው ቡድን በወጣቶች የተመሰረተ እንደመሆኑ አቅማችን በፈቀደው ቢያንስ ከስጋት ነፃ የሆነ ተፎካካሪ ቡድን ይዘን እንቀርባለን ብዬ አስባለሁ። ያ ሲባል ግን በሒደት እየተሠራ የሚሄድ ቡድን መሆኑ መታወቅ አለበት።” ይላሉ።
እስካሁን በመጣበት መንገድ በተጫዋቾች ታታሪነት ላይ የተመሰረተ ጥብቅ መከላከልን ተንተርሶ በቶሎ ወደ ግብ መድረስን ያማከለ አቀራረብ እንደሚኖረው የሚጠበቀው ወላይታ ድቻ የዓመቱን ጉዞ በመክፈቻው ቀን ጥቅምት 7 ድሬዳዋ ከተማን በመግጠም ይጀምራል።
የወላይታ ድቻ የ2014 ስብስብ
ግብ ጠባቂዎች
1 ቢኒያም ገነቱ
22 ፅዮን መርዕድ
30 ወንድወሰን አሸናፊ
33 አብነት ይስሃቅ
ተከላካዮች
4 በረከት ወልደዮሐንስ
5 ኬኔዲ ከበደ (U-23)
9 ያሬድ ዳዊት
12 ደጉ ደበበ
15 መልካሙ ቦጋለ
16 አናጋው ባደግ
24 አዛሪያስ አቤል (U-23)
26 አንተነህ ጉግሳ
27 ዮናታን ኤልያስ (U-23)
28 ዘካሪያስ ቱጂ
አማካዮች
6 ሳሙኤል ጃግሶ (U-23)
8 እንድሪስ ሰዒድ
14 መሳይ ኒኮል
18 ውብሸት ወልዴ (U-23)
19 አበባየሁ አጪሶ (U-23)
20 ሀብታሙ ንጉሤ
23 አዲስ ህንፃ
25 ንጋቱ ገ/ሥላሴ
አጥቂዎች
7 ፍስሃ ቶማስ
10 ስንታየሁ መንግሥቱ
11 ምንይሉ ወንድሙ
13 ቢንያም ፍቅሩ (U-23)
21 ቃል ኪዳን ዘላለም
29 ዘላለም አባቴ (U-23)
ተጨማሪ ምስሎች – ከWolaitta Dicha Sport Club የፌስቡክ ገፅ