ኢትዮጵያዊያን ዳኞች የቻምፒየንስ ሊግ የማጣሪያ ጨዋታን ይመራሉ

አራት ኢትዮጵያዊያን ዳኞች የፊታችን ቅዳሜ በናይሮቢ የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪያ ጨዋታን እንደሚመሩ ታውቋል፡፡

የ2021 የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ የማጣሪያ ጨዋታዎች በያዝነው ሳምንት ጨዋታዎች ቀጥለው የሚካሄዱ ሲሆን በያዝነው ዓመትም በርከት ያሉ የሀገራችን ዳኞች በተለያዩ ሀገራት የሚደረጉ የሀገራት እና የክለብ ጨዋታዎች በብቃት ሲመሩ ይስተዋላል፡፡ የፊታችን ቅዳሜ በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ የማጣሪያ ጨዋታ የጅቡቲውን አርታ ሶላርን በድምር ውጤት 4ለ1 የረታው የኬኒያው ክለብ ተስካር በናይሮቢ ኒያዮ ስታዲየም ከቀኑ 9፡00 ላይ በመድረኩ ጠንካራ ተፎካካሪ የሆነው የግብፁ ክለብ ዛማሌክን ያስተናግዳል፡፡

ይህንን ጨዋታም አራት ኢትዮጵያዊያን ዳኞች እንዲመሩት በካፍ እንደተመረጡ እና ዳኞቹም ዛሬ አመሻሽ ወደ ስፍራው እንደሚያመሩ ሶከር ኢትዮጵያ ተገንዝባለች፡፡ በመሀል ዳኝነት በአምላክ ተሰማ ሲመራው በረዳት ዳኝነት ተመስገን ሳሙኤል እና ፋሲካ የኋላሸት በአራተኛ ዳኝነት ደግሞ ለሚ ንጉሴ የካፍ ጥሪ የደረሳቸው አራቱ ዳኞች ሆነዋል፡፡

ዛማሌክ ባሳለፍነው ዓመት በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ በዚሁ ኒያዮ ስታዲየም ጎርማሂያን 4ለ0 መርታቱ ይታወሳል፡፡

ያጋሩ