ኢትዮጵያ ቡና እና ቤቲካ የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ተፈራርመዋል

ኢትዮጵያ ቡና የስፖርት ውርርድ ኩባንያ ከሆነው ቤቲካ ጋር የአምስት ዓመታት የስፖንሰርሺፕ ስምምነት በዛሬው ዕለት ተፈራርሟል።

11፡00 ላይ በኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ በተካሄደው በዚህ የፊርማ ሥነስርዓት ላይ የቤቲካ የምስራቅ አፍሪካ ሪጅናል ዳይሬክተር ሚስተር ማዮ፣ የቤቲካ ኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ አቶ አብርሃም ተክለማርያም፣ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ እንዲሁም የክለቡ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ይስማሸዋ ሥዩም ተገኝነተዋል።

በፕሮግራሙ መጀመርያ ላይ የቤቲካ ኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አብርሃም ተክለማርያም ስለ ድርጅቱ ገለፃ የሰጡ ሲሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ በስምንትየአፍሪካ ሀገራት ላይ ቅርንጫፎችን ከፍቶ እየሠራ እንደሚገኝና በቀጣይ በማላዊ እና ሩዋንዳ ቅርንጫፎች ለመክፈት በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልፀዋል። በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነው ቤቲካ የቀድሞው የኳስ ጥበበኛ ሮናልዲንሆ ጋውቾን ብራንድ አምባሳደር አድርጎ እየሠራ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ አብርሃም ቀልጣፋ የክፍያ ስርዓት በመዘርጋት በሀገራችን የሚገኙ ፈጣን የክፍያ ስርዓቶችን ጥቅም ላይ ስለማዋሉ አውስተዋል። በመቀጠል ኩባንያቸው ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ለመሰሥራት ምርጫቸው ያደረጉበት ምክንያት ”ከፍተኛ የደጋፊ ቁጥር ያለው መሆኑ በብሔራዊ ሎተሪ ደንብ እና መመርያ መሰረት የተከፈቱ ወደ 70 የሚጠጉ ቅርንጫፎች አካባቢ የቡና ደጋፊዎች ጋር ተደራሽ ማድረግ ስለሚቻል፤ ውጤታማነቱ እና ህዝባዊ መሰረት ያለው መሆኑ” እንደሆነ አብራርተዋል።

ከአቶ አብርሃም ገለፃ በመቀጠል የቤቲካ የምስራቅ አፍሪካ ሪጅናል ዳይሬክተር ሚስተር ማዮ እንደ ቡና ካለ የደጋፊ መሰረት ካለው ክለብ ጋር ለመስራት መስማማታቸው ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነ ገልፀው ኩባንኣው ባለበት ሀገራት ሉ በስፖርት ልማት እና ማኅበራዊ ኀላፊነት ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ ሲደርግ እንደቆየ በምስል በታገዘ ገለፃ አብራርተዋል።

ከሁለቱ የቤቲካ አመራሮች ገለፃ በኋላ የፊርማሥነ-ስርዓት የተከናወነ ሲሆን በቤቲካ ነኩል አቶ አብርሃም በቡና በኩል አቶ ገዛኸኝ ስምምነቱን በይፋ ፈርመዋል።

ከፊርማ ሥነ-ስርዓቱ በመቀጠል አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ስምንት አንቀፆች ያሉት የስምምነቱን ዝርዝር አስረድተዋል። ለአምስት ዓመታት የሚቆየውና በክለቡ ማልያ ደረት ከአርማው ትይዩ ባለ ቦታ ላይ በሚሰፍረው ማስታወቂያ የሁለቱ አካላት ስምምነት የአከፋፈል ሁኔታውም በዚህ ዓመት (እስከ ነሐሴ 30 ድረስ) 6 ሚልየን ቤቲካ ለቡና ክፍያ የሚፈፅም ይሆናል። ሦስት ሚልየን ብሩ ውሉን በተፈራረሙበት ወቅት የተፈꬠፀመ ሲሆን ሁለተኛው ክፍያ ከአምስት ወር በኋላ እንደሚፈፀም አቶ ገዛኸኝ ገልፀዋል። ቀጣዩ ዓመት ያለው የአከፋፈል ሁነታ ግን በውላቸው መሠረት በድርድር እንደሚወሰን ተናግረዋል።

የክለቡ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ይስማሸዋ በበኩላቸው ስምምነቱ ሁለቱንም አካላት ያስደሰተ መሆኑን በመግለፅ ንግግራቸውን ጀምረዋል። እግርኳሱን ከመሰል የቢዝነት ሀሳቦች ጋር በማስተዋወቅ ኢትዮጵያ ቡና ፈር ቀዳጅ መሆኑን ያወሱት አቶ ይስማሸዋ ከዚህ ቀደም ከበርካታ ተቋማት ጋር በአጋርነት እንደሰሩት ሁሉ አሁንም ከቤቲካ ጋር እንደሚሰሩ እና በቀጣይም ህጉ እስከፈቀደ ድረስ ከሌሎች ተቋማት ጋር መስራት እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል። ”በቅርብ ጊዜም ሌላ ስፖንሰር ወደ ቡና ይመጣል። እሱንም በቅርቡ እናበስራለን ብለን እንገምታለን። ከቤቲካ ጋር የሚኖረን ግንኙነት. . . በግልም እንደምናውቃቸው የስፖርት ሰዎች ናቸው። ለስፖርቱ ድጋፍ ማድረግ የሚወዱ ናቸው። የኛ ክለብ ደግሞ ከሌሎች ለየት የሚያደርገው ስፖንሰር ላደረጉን ድርጅቶች ታማኝ መሆናችን ነው። ደጋፊዎቻችን ለስፖንሰሩ ደሙን ይሰጣል። ይህ ስለሚታወቅ አንዳንድ ቦታ እኛ ሳንደርስ ራሳቸው ይመጣሉ። በአጠቃላይ ቤቲካ ከእኛ እና ከደጋፊዎቻችን የሚፈልገውን ነገር ለማድረግ ዝግጁ ነን። ስምምነታችን የከአምስት ዓመት ቢሆንም ከዚያ በላይ እንደምናልፍ እምነቱ አለኝ።” ብለዋል።

ከአመራሮቹ ንግግር በኋላ ከጋዜጠኞች በርከት ያሉ ጥያቄዎች ተጠይቀው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል። በተለይም የሊጉ የስያሜ ባለመብት ከቤትኪንግ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ግጭት አይፈጥርም ወይ ተብሎ ለተነሳው ጥያቄ አቶ ገዛኸኝ በሰጡት ምላሽ ” ከቤቲካ ጋር አምና ጥር አካባቢ ነበር ድርድር የጀመርነው። ቤቲካ ሀሳቡን ሲያቀርብልን ‘ከቤቲካ ጋር ልንዋወል ስለሆነ ምላሽ ይሰጠን’ ብለን ለሚመለከተው አካል በደብዳቤ በጠየቅነው መሰረት ከተቀመጡ ገደቦች ጋር ከቤቲካ ጋር መስራት እንደምንችል ተፈቅዶልን ነው ይህን ስምምነት የተፈራረምነው። ” ብለዋል።