የክለቦች የውድድር ዘመን ቅድመ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ

የአዳማ ከተማ የዝግጅት እና መጪው ጊዜ እንዲህ ይዳሰሳል።

2007 ላይ ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊግ ካደገ ወዲህ ደካማውን የውድድር ዓመት ያሳለፈው አዳማ ከተማ ወደ ከፍተኛ ሊጉ ከመሸኘት ከተረፈ በኋላ አዲሱን የውድድር ዓመት ይጀምራል። የዋንጫ ተፎካካሪነት ደረጃን የማያጣው አዳማ በተለይም ከ2009-2011 ድረስ በጥሩ ስብስብ ጠንካራ ቡድን መገንባት ችሎ ነበር። በአሁን ሰዓት በሊጉ በሌሎች ክለቦች ቁልፍ ቦታ ያላቸውን የያኔዎቹን ተጫዋቾቹን ካጣ በኋላ አምና በአዲስ መልክ ያዋቀረው ቡድን መጠንከር ሳይጀምር በውጤት አዘቅት ውስጥ ገብቷል። ከአሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤል ጋር የጀመረው ዓመት በደካማ ውጤት እና አሰልጣኙን በማሰናበት የተጋማሰ ነበር። ቀሪውን ጊዜም በርካታ ተጫዋቾችን በማስፈረም ከአሰልጣኝ ዘርዓይ መሉ ጋር ቀና ለማለት ቢጥርም በ14 ነጥቦች የሊጉን ግርጌ ይዞ ከማጠናቀቅ አልተረፈም። ሆኖም የትግራይ ክልል ክለቦችን ቦታ ለመተካት በተደረገው የክረምቱ መግቢያ ውድድር ላይ ዳግመኛ ዕድል ያገኘው ክለቡ ውድድሩን በአንደኝነት በማጠናቀቅ ለዘንድሮው ውድድር በሊጉ መቆየት ችሏል።

በመለያ ውድድሩ እንዲቆይ ካስቻሉት አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ጋር መቀጠል ያልቻለው አዳማ ከተማ በባህር ዳር ከተማ የሁለት ዓመት ውላቸውን ያጠናቀቁትን አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝን ሾሟል። በተጨማሪም ከሰበታ ጋር የነበራቸውን ውል ጨርሰው ወደ ባህር ዳር ለመሻገር ከጫፍ ደርሰው የነበሩት አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለን በረዳት አሰልጣኝነት ሲቀጥር አሰልጣኝ አብዲ ቡሊ ደግሞ በረዳትነት ቀጥለዋል። ከዚህ ሌላ የቀድሞው ተጫዋቹ መስፍን ነጋሽ የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ ሆኗል።

በስብስብ ደረጃ በብዙ ተለውጦ የሚመጣው አዳም ከተማ በተለምዶው ልምድ ያላቸውን ከወጣቶች ጋር በማጣመር የሚለውን አባባል ያማከለ ይመስላል። በለቀቁ ተጫዋቾች ምትክ ያስፈረማቸው አመዛኞቹ ተጫዋቾች በእግርኳሳችን ውስጥ ስማቸው ቆየት ያሉ ሲሆኑ ጎን ለጎን ደግሞ ወጣት ተጫዋቾችንም ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል። ታዳጊዎችን በማብቃት ብዙ የማይታማው ክለቡ ባለፈው የውድድር አጋማሽ ያሳደጋቸው ተከላካዩ ሙሀዝ ሙኸዲን ፣ አማካዩ አቤኔዘር ሲሳይ እንዲሁም አጥቂዎቹ ፍራኦል ጫላ ፣ ቢንያም አይተን እና ነቢል ኑሪ በተጨማሪ አሁን ደግሞ አራት ተጫዋቾችን ከወጣት ቡድኖቹ አሳድጓል። እነርሱም የተከላካይ መስመር ተሰላፊዎቹ ዳዊት ይመር እና በላይ ጌታቸው አጥቂዎቹ አብዲ ዋበላ እና አቤል ደንቡ ናቸው። ከዚህ ቀደም የክለቡ ወጣት ቡድን ፍሬዎች የነበሩት ጂብሪል አህመድ እና ዘካርያስ ከበደን የሙከራ ዕድል በመስጠትም ወደ ስብስቡ መልሷቸዋል። “ልምድ ያላቸው እና ወጣቶችን በማቀናጀት ቡድን ለመገንባት እየሞከርን ነው። ከታችኛው ሊግ ያስፈረምናቸው ተጫዋቾች አሉ ፤ አምና በቢጫ ቴሴራ ያደጉ ተጫዋቾች አሉ በተጨማሪም ሌሎች ሦስት ተጫዋቾች (2 ከ17 ዓመት በታች እና 1 ከ20 ዓመት በታች) ከታችኛው ቡድን አሳድገናል።ባለፈው ዓመት ያደጉትን እንዲሁም አዲስ ያደጉትን ተጫዋቾች ዕድገት ከፍ ለማድረግ በዚያ ውስጥ እንደ አስፈላጊነቱ ወጣቶችን እንጠቀማለን።” የሚለው የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አስተያየት ለወጣቶቹ ተስፋን የሚጭር ነው።

ባሳለፍነው ዓመት አጋማሽ መጥተው ቡድኑን በመለያ ውድድሩ ካገለገሉ እና ኮንትራታቸው ከተጠናቀቁ ተጫዋቾች ውስጥ ግብ ጠባቂው ሴኮባ ካማራ በአዳማ የሚቀጥል ይሆናል። ሚሊዮን ሰለሞን እና አብዲሳ ጀማልም በአዳማ ውላቸው ያራዘሙ ነባር ቁልፍ ተጫዋቾች ሆነዋል። የተቀሩ ክፍተቶቹን ለመሙላት በዝውውር መስኮቱ ላይ ሰፊ ተሳትፎ በማድረግ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው አዳማ ከተማ 14 ተጫዋቾችን አስፈርሟል። በዚህም ጀማል ጣሰው በግብ ጠባቂነት ሲፈርም ደስታ ዮሐንስ፣ አዲሱ ተስፋዬ እና ቶማስ ስምረቱ አዲሶቹ የቡድኑ ተከላካዮች ሆነዋል። አማካይ ክፍሉን ምንተስኖት አዳነ ፣ ዮናስ ገረመው ፣ ታደለ መንገሻ ፣ አማኑኤል ጎበና እና ዮሴፍ ዩሐንስን በማካተት ሲያጠናክር ዳዋ ሆቴሳ ፣ አሜ መሐመድ እና አቡበከር ወንድሙ የፊት መስመሩን የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ሆነዋል።

አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ከባህር ዳር ከተማ ቀጥሎ በዋና አሰልጣኝነት የያዙትን ቡድን በአዲስ መልክ የማዋቀር ኃላፊነት ወድቆባቸዋል። ባለፉት ዓመታት ያጎለበታቸውን ተጫዋቾች የሚገባውን ያህል ሳይጠቀም ማጣቱ አዳማን ዳግም ግንባታ ውስጥ እንዲገነባ አስገድዶታል። አዲሱን አሰልጣኙም ሁኔታው ከዝውውር ጊዜ አንስቶ ነገሮችን ቀላል እንዳላደረገላቸው ያነሳሉ። “አዳማ ከተማን ከምንም ነው ለመስራት የሞከርነው። ካለፈው ዓመት ሦስት አራት ተጫዋቾች ናቸው የነበሩን ፤ ታዳጊ ተጫዋቾች እንዳሉ ሆነው። ከዚያ ተነስተን በምንፈልገው መልኩ ተጫዋቾችን ለማሟላት ፈተና ነበር። በምንፈልገው ልክ ባይሆንም ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾች አግኝተናል። ልምድ ያላቸውን ከወጣቶች ጋር አቀናጅተን ለመስራት ጥረት እያደረግን ነው።”

ይህ ተመሳሳይ ሁኔታ አምናም በዚሁ ጊዜ ላይ በክለቡ ውስጥ ተንፀብርቆ ነበር። በወቅቱ ቡድኑን ለመገንባት ከአሁኑ ያነሰ ቁመና ላይ ይገኝ የነበረው አዳማ የተጫዋች ፍላጎቱን በአመዛኙ ከከፍተኛ ሊግ አሟልቶ ነበር የተዳከመበትን የውድድር ዓመት የጀመረው። ለውጤቱ መጥፋትም ይሄው ነጥብ በምክንያትነት ሲጠቀስ ቆይቷል። የዘንድሮውን ለየት የሚያደርገው የስብስብ ጥራቱ የተሻለ ሆኖ መገኘቱ ነው። አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝም “ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ዘንድሮ በጥራትም በልምድም የተሻሉ ተጫዋቾች ወደ ቡድኑ ተካተዋል። በሊጉም ጠንካራ ተፎካካሪ ያደርጉናል ብለን እናስባለን። ከእኛ በጣም የተሻለ ስብስብ ያላቸው ቡድኖች አሉ። እኛም ደግሞ በተወሰነ ደረጃ የምንሻልበት አለ። በተቻለ መጠን ተመጣጣኝ ለማድረግ ሞክረናል። የእኛ ችግር የነበረው ቡድኑን ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል መልኩ ለመለወጥ በሚደረግ ጥረት ውስጥ በየቦታው በምንፈልገው ደረጃ ተጫዋቾችን አግኝተናል ብዬ አላስብም። እንዴትም ቢሆን ግን የሚያፎካክር ቡድን አለን።” በማለት ስብስባቸው ያለውን ደረጃ ያስረዳሉ።

አዲስ ስብስብን መፍጠር ፈተናው በዝውውር ሽሚያው ላይ ብቻ አይሆንም። ከዚያ ቀጥሎ የሚመጣው እንደ ቡድን የማጣመር ሂደት ይበልጥ አስቸጋሪ ይሆናል። ይህ የየአሰልጣኞቻችን ፈተና በአሰልጣኝ ፋሲል አንደበት ሲገለፅ ደግሞ ይህንን ይመስላል። “እሱ ነው ከባዱ ፈተና ፤ በመጀመርያው የዝግጅት ምዕራፍ የተጫዋቾቹን የአካል ብቃት ደረጃ ከተመለከትን በኋላ በፍጥነት ነው ወደ ጨዋታ ዝግጅት ለመግባት የሞከርነው ። ሁሉም ተጫዋቾች ከሌላ ክለብ የመጡ አዳዲስ መሆናቸው እንዲሁም እኔም ለቡድኑም ለተጫዋቾች አዲስ እንደመሆኔ ቶሎ በሊጉ የቅንጅት ችግር እንዳይገጥመን የተቻለንን ጥረት አድርገናል። እንግዲህ ቡድኑን ምን ያህል አዘጋጅተናል የሚለው በውድድሩ የሚታይ ይሆናል። ነገርግን ትልቁ ፈተና ይህን አዲስ ቡድን በተቀናጀ መልኩ ተጫዋቾች አቅማቸውን ጠብቀው ለውድድር እንዲቀርቡ ማድረግ ነው”

አዳማ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ከነሀሴ 22 ጀምሮ በመቀመጫ ከተማው ሲያደርግ ቆይቷል። በመጀመሪያው የቡድኑ የዝግጅት ምዕራፍ ከአዲስ ዓመት በፊት ቴክኒክ እና ታክቲኩ እንዳለ ሆኖ የተጨዋቾቹን አካል ብቃት እና የሥነ ልቡና ደረጃ ከፍ ማድረግ ላይ ያተኮረ ልምምዶችን በመስራት አሳልፏል። በቀጣዩ ምዕራፍ ከጨዋታ ጋር የሚገናኙ ስብስቡን የሚያሰናዱ ሥራዎች ተከውነዋል። በዚህ ምዕራፍ ቡድኑ ሊጫወት ከሚያስበው አጨዋወት ጋር የተጫዋቾችን የታክቲክ አረዳድ ክፍ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል። በሦስተኝነት አዳማ ከወጣት ቡድኑ እና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን አድርጎ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ጨዋታዎች በማምራት ሦስት ግጥሚያዎችን ከውኗል። ቅዱስ ጊዮርጊስን በሲቲ ካፑ ላይ መልሶ ማግኘቱ ከግምት ሲገባም ከሦስት የሊጉ ቡድኖች ጋር እንደተጫወተ መረዳት ይቻላል።

በመዲናዋ ውድድር አዳማ ከውጤት አንፃር ስኬት ባያስመዘግብም አሰልጣኙ የውድድሩ ዋና አላማ የሆነው ራስን መገምገብ ግቡን እንደመታ ያምናሉ። በሲቲ ካፕ ውድድሩ ላይ ስለተመለከቷቸው ነገሮች ሲያስረዱም “በግልፅ መናገር የምችለው ወደ ሲቱ ካፕ ስንገባ ውጤትን አላማ አድርገን ባይሆን በጣም የተማርንበት ነበር። በሦስቱም ጨዋታዎች ተጫዋቾች ለመሞከር ጥረት አድርገናል ፤ የተለያዩ ጥምረቶችን በተለያዩ የሜዳ ክፍሎች ለመመልከት ሞክረናል። በተለይ በሁለተኛ እና ሦስተኛው ጨዋታ ወደ 80% የሚሆኑ ተመሳሳይ ተጫዋቾችን ለመጠቀም ሞክረናል። እንደ አሰልጣኝ በውድድሩ ብዙ ተምረናል፤ እንደ ቡድን በሦስቱ ጨዋታዎች መሻሻል እና ዕድገቶችን ተመልክተናል። ይህንንም ለማስቀጠል በነበሩን ቀጣዮቹ ቀናት ሥራዎችን ሰርተናል።” በማለት ነበር።

አዳማ ከተማ በዘንድሮው ስብስቡ ውስጥ የአጥቂ ክፍሉ ትኩረትን ይስባል። የዳዋ ሆቴሳ ፣ አብዲሳ ጀማል እና አሜ መሐመድ ፍጥነት ቡድኑ በቀጥተኛ አጨዋወት በፍጥነት ወደ ጎል ለመድረስ በሚያቅድባቸው ጨዋታዎች ላይ ምቹ ሁኔታን ይጨምራል። በዚህ ላይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ታዳጊ ቡድን የተገኘው እና ለአዲስ አበባ ከተማ ወደ ሊጉ መምጣት ጥሩ ሚና የነበረው የመስመር አጥቂው አቡበከር ወንድሙ በሲቲ ካፑ ያሳየው አቋም የፊት መስመሩን አስፈሪነት ይበልጥ የሚጨምር ነው። አብዲሳ ጀማልም ከአምናው በተሻለ ቡድን እና በጠንካራ አጣማሪዎች ሲታጀብ በግብ ፊት ያለው ስኬት ጨምሮ እንደሚታይ ይጠበቃል።

አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በመጨረሻ ከአጨዋወት ምርጫ እና ከውጤት ዕቅድ አንፃር በመጨረሻ በሰጡት አስተያየት “በ2014ቱ የሊጉ የመጀመሪያው አላማችን የተረጋጋ ቡድን እንዲኖረን ማድረግ ነው” አምና አዳማ በሚመጥነው ደረጃ ላይ አልነበረም። በቀዳሚው ዕቅዳችን አምና የነበረውን ያንን አስተሳሰብ ቀይረን ጠንካራ ተፎካካሪ የሆነ ደጋፊዎች የሚደሰቱበት ቡድን ለመገንባት የሚቻለንን ሁሉ ጠንክረን እየሰራን ነው። በሊጉ እንደየጨዋታው ተለዋዋጭ መንገድ ልንከተል እንችላለን። ነገር ግን በአብዛኛው ከኋላ ኳሱን ተቆጣጥሮ በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ለመግባት የሚሞክር ቡድን እንዲኖረን እናስባለን። አንዳንድ ጊዜ ግን እንደተጋጣሚያችን አቀራረባችን ልንቀያይር እንችላለን።” ብለዋል።

አዳማ ከተማ በመጪው ሰኞ የዓመቱ የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታ ከወልቂጤ ከተማ ጋር እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

የአዳማ ከተማ የ2014 ስብስብ

ግብ ጠባቂዎች

ጀማል ጣሰው
ሴኩምባ ካማራ
በቃሉ አዱኛ

ተከላካዮች

አዲሱ ተስፋዬ
ቶማስ ስምረቱ
አሚን ነስሩ
ኢዮብ ማቲዮስ
ሚሊዮን ሰለሞን
ደስታ ዩሐንስ
ጀሚል ያዕቆብ
ሙአዝ ሙኸዲን
ዳዊት ይመር
በላይ ጌታቸው

አማካዮች

ምንተስኖት አዳነ
ዮናስ ገረመው
ታደለ መንገሻ
አማኑኤል ጎበና
ዮሴፍ ዩሐንስ
ዘካርያስ ከበደ
ኤልያስ ማሞ
አቤኔዘር ሲሳይ
ነቢል ሙዲ
ብሩክ መንገሻ

አጥቂዎች

ዳዋ ሁቴሳ
አሜ መሐመድ
ጂብሪል አህመድ
አብዲሳ ጀማል
ቢኒያም አይተን
ፍሬኦል ጫላ
አቡበከር ወንድሙ
ዮሴፍ ታረቀኝ
አብዲ ዋበላ
አቤል ደንቡ