ኢትዮጵያ ቡና በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ በእንቅስቃሴያቸው ማሳመን የቻሉትን ሁለቱን ተስፈኛ ተጫዋቾችን በዋናው ቡድን ማስፈረሙ ታውቋል።
ወደ ፊት በትልቅ ደረጃ መጫወት እንደሚችሉ በአሰልጣኝ ካሣዬ አራጌ የታመነባቸው የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቹ ገዛኸኝ ደሳለኝ እና አማካዩ ሱራፌል ሠይፉ በዛሬው ዕለት በአረንጓዴ ቲሴራ ለዋናው ቡድን መፈረማቸውን አረጋግጠናል።
የመጀመርያው ፈራሚ አማካይ ሱራፌል ሠይፉ ሲሆን በአሰልጣኝ ደግፌ ስር የእግርኳስ ተጫዋችነት ህይወቱን በመጀመር በየጊዜው በሚያሳየው ዕድገት በ2011 በአዲስ አበባ ፕሮጀክት ውድድር አዲስ አበባ ዩናይትድን ቡድን ጋር ኮከብ ተጫዋች በመባል ተመርጧል። በ2013 ከአሰልጣኝ ደግፌ ጋር የኢትዮጵያ ቡና ከ17 ዓመት በታች ቡድን አባል በመሆን ጥሩ የውድድር ዓመት ያሳለፈው ሱራፌል የክለቡ የ17 ዓመት በታች ቡድን ኮከብ ተጫዋች በመባል መመረጡ ይታወቃል።
ሁለተኛው ፈራሚ ገዛኸኝ ደሳለኝ የእግርኳስ ህይወቱ መነሻው አስኮ ፕሮጀክት ሲሆን ከአሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ ስር ከ2010 ጀምሮ በተለያዩ አማራጭ ቦታዎች ከ20 ዓመት በታች ቡድን ሲጫወት የቆየ ጠንካራ ተጫዋች ነው። በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ አሰልጣኝ ካሳዬ የመሐል ተከላካይ በማድረግ ያጫወቱት ገዛኸኝ ባሳየው መልካም እንቅስቃሴ መፈረሙ ታውቋል።
ሶከር ኢትዮጵያ የተለያዩ የተስፋ ቡድን ጨዋታዎችን በምትከታተልበት ወቅት ሁለቱ ተጫዋቾች ወደፊት ተስፋ የሚጣልባቸው ተጫዋቾች እንደሚሆኑ ግምቷን አስቀምጣ እንደነበረ ይታወቃል።