ለሴቶች ቡድኑ አሰልጣኝ ለመቅጠር ከወራት በፊት ማስታወቂያ አውጥቶ የነበረው አዳማ ከተማ ቅጥሩን ወደ ጎን በመተው የቀድሞው አሰልጣኙን ሾሟል፡፡
በ2011 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮን ካደረገው አሰልጣኝ ሳሙኤል አበራ ጋር የተለያየው እና አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር ማስታወቂያ ከወራት በፊት አውጥቶ የነበረው አዳማ ከተማ በቅጥር ማስታወቂያው መሠረት በርካታ አሰልጣኞች የተመዘገቡ የነበረ ቢሆንም አሰልጣኙ አወዳድሮ ለመቅጠር አውጥቶት የነበረው ማስታወቂያ በመሰረዝ የቀድሞውን አሰልጣኝ በድጋሚ ዋና አሰልጣኝ አድርጎ ሾሟል፡፡ አሰልጣኝ ኤፍሬም እሸቱም ለቀጣዩ አንድ ዓመት የአዳማ ከተማን የሴቶች ክለብ የሚያሰለጥነው አሰልጣኝ ነው፡፡
በ2005 የአዳማ ሴቶች ቡድን ሲቋቋም አሰልጣኝ ሆኖ ከዚህ ቀደም የሠራው አሰልጣኙ በመቀጠል የአዳማ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ቡድንን በማሰልጠን ውጤታማ ዓመታትን አሳልፏል፡፡ በመቀጠል የአዳማ ከተማ የዋናው ቡድን ሦስተኛ ረዳት አሰልጣኝ በመሆን እስከ 2010 ድረስ መስራት የቻለው ኤፍሬም በመቀጠል ያለፉትን ሦስት ዓመታት የአንደኛ ሊጉ ክለብ ዱከም ከተማን እያሰለጠነ ቆይቶ ወደ ቀድሞ ክለቡ አዳማ ተመልሶ ዋና አሰልጣኝ ተደርጎ መሾሙን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ አስረድቷል፡፡