የክለቦችን የክረምቱን የዝግጅት ጊዜ እና ቀጣዩን የውድድር ዓመት ገፅታ እየቃኘንበት የምንገኝበት ፅሁፋችን አሁን ኢትዮጵያ ቡና ላይ ያጠነጥናል።
የ2003ቱ የሊጉ ቻምፒዮን ኢትዮጵያ ቡና ከዚያ በኋላ በመጡ ዓመታት በሚፈለገው ደረጃ ለመፎካከር ተቸግሮ ቆይቷል። 2008 ላይ ካስመዘገበው የሁለተኝነት ደረጃ በኋላ ተመሳሳይ ውጤትን ያሳካበት የአምናው ውድድር ከዚህ አንፃር የተረጋጋ ነበር ለማለት ያስችላል። ቡድኑ በውጤት ተከታታይ ድሎችን በማሰዝገብ በወጥነት የቀጠለባቸው ሳምንታት ጥቂት ቢሆኑም የሰበስባቸው 41 ነጥቦች የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጨዋታዎች ተሳትፎን አስገኝተውለት ሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
ኢትዮጵያ ቡና ከቀድሞው ተጫዋቹ እና የአሁኑ አሰልጣኙ ካሣዬ አራጌ ጋር ሦስተኛ የውድድር ዓመቱን ይጀምራል። ከአሰልጣኙ ወደ ቡና መድረስ ጀምሮ በምክትል አሰልጣኝት አብሮ የነበረው የአሰልጣኝ ዘላለም ፀጋዬ ቆይታ ግን በክረምቱ አነጋጋሪ ከነበሩ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ነበር። የአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ፍላጎት አብረው እንዲቀጥሉ የነበረ ቢሆንም የክለቡ ሀሳብ መቃረን ለሳምንታት ርዕስ ሆኖ ሲያወዛግብ ቆይቷል። በሂደት ወደ ሥራው ይመለሳል ተብሎ ቢጠበቅም ጉዳዩ ተዳፍኖ የቀረ ሲሆን ክለቡ የቡድን መሪ ለመሾምም እንቅስቃሴ የጀመረው በቅርቡ መሆኑ ግርምትን ያጭራል። ከሜዳ ውጪ እንደክለብ የፋይናንስ አቅሙን በመገንባት አዳዲስ አጋሮችን እያገኘ ያለው ቡና ቴክኒክ ክፍሉ ላይ ክፍተቶችን በቶሎ ለመሸፈን ትኩረቱ ከዚህ የተሻለ እንዲሆን ይጠበቅ ነበር። ሌላው የቡድኑ ምክትል አሰልጣኝ ገብረኪዳን ነጋሽን አሁንም በስብስቡ ውስጥ ሲገኙ በህክምና ባለሙያዎች በኩልም ሰለሞን ኃይለማሪያም እና ይስሀቅ ሽፈራውም በቡናማዎቹ የቴክኒክ ክፍል ውስጥ እንዳሉ ናቸው።
ኢትዮጵያ ቡና ዓምና የተሻለ በወጥነት ሲጠቀምባቸው ከነበሩ ተጫዋቾቹ ውስጥ ከአቤል ከበደ፣ ሀብታሙ ታደሰ፣ ተክለማርያም ሻንቆ እና ምንተስኖት ከበደ ጋር ፍቺ ፈፅሟል። ዘካሪያስ ቱጂ፣ አዲስ ፍስሐ፣ እያሱ ታምሩ እና ዓለምአንተ ካሣም ከክለቡ ጋር አይቀጥሉም። ግብ ጠባቂው በረከት አማረ ተከላካዮቹ ሥዩም ተስፋዬ፣ ነስረዲን ኃይሉ እና ቴዎድሮስ በቀለ አጥቂዎቹ አቤል እንዳለ እና በየነ ባንጃ እንዲሁም በአረንጓዴ ቴሴራ የተካተቱት ተከላካዩ ገዛኸኝ ደሳለኝ እና አማካዩ ሱራፌል ሰይፉ ክፍተቶቹም ለመድፈን ቡድኑን የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ናቸው።
ባሳለፍነው የውድድር ዓመት ኢትዮጵያ ቡና በመጀመሪያ ተሳላፊነት ውስን ተጫዋቾችን ብቻ በመጠቀም ነበር ያሳለፈው። በዚህ ረገድ አንድ አራተኛ የሚሆኑት የቡድኑ አባላት በዓመቱ ምንም የጨዋታ ደቂቃ አልነበራቸውም። እንደዚሁ የቀሩት ሩብ ያህሉ ደግሞ በመጀመሪያ አሰላለፍ እና በተቀያሪነት የታዩባቸው ጨዋታዎች ብዛት ከአራት የዘለለ አልነበረም። በመሆኑም ቡና ግማሽ የሚሆነውን ስብስቡን ብቻ በርከት ያሉ ጨዋታዎች ላይ ጥቅም ላይ ማዋሉን እንረዳለን። በዚህ ውስጥ ከሚካተቱ ተጫዋቾች ውስጥ ደግሞ አራት ያህሉ ከቡድኑ ለቀዋል። በመሆኑም በአስተማማኝ ደረጃ የሚተኳቸው እና ለብዙ ጨዋታዎች በወጥነት የሚያገለግሉ በቀደመ ክለባቸው በዚህ ረገድ ጥሩ የጨዋታ ተሳርፎ ቁጥር ያላቸው ተጫዋቾችን እንደሚያስፈርም ይጠበቅ ነበር።
የኢትዮጵያ ቡናን አዲስ ፈራሚዎች ደረጃ ስናይ በዋነኛነት ሲጠቀማቸው ከቆዩ እና ከለቀቁት አንፃር የስብስቡን ጥራት እንዳይቀንሰው ያሰጋል። ያ ከሆነ ደግሞ ዘንድሮም እንደአምናው ዕምነቱን በተወሰነው የስብስቡ ክፍል ላይ ብቻ ጥሎ በርከት ያሉ ጨዋታዎችን ወደ ማድረግ ሊወስደው ይችላል። ይህም በውድድር ጊዜ ጉዳት እና መሰል አስገዳጅ ነገሮችን ጨምሮ ታክቲካዊ አማራጮችን በማስፋቱ በኩል የቡድን ጥልቀት የሚያስገኘውን ጥቅም ሊያሳጣው ይችላል።
በሌላ መልኩ ስንመለከተው ደግሞ አሰልጣኙ አምና በዊሊያም ሰለሞን ላይ እንዳሳዩን ሁሉ ከወጣቶቹ ውስጥ ሰብሮ የሚወጣ ተጫዋች የሚኖር ከሆነ በወጥነት ለመጠቀም ያላቸው ድፍረት የጠቃሚ ተጫዋቾቸን ቁጥር ከፍ ሊያደርግ ይችላል። በመርህ ደረጃ ስንመለከተው ግን ኢትዮጵያ ቡና በስዩም ተስፋዬ ዝውውር ላይ ካንፀባረቀው አቋም ውጪ ተጫዋቾች ከዚህ ቀደም በነበሩባቸው ቡድኖች ውስጥ ከነበራቸው ልምድ እና አቋም ይልቅ በግለሰብ ደረጃ ጠንካራ ጎናቸው ላይ ተመስርቶ በቡድኑ ውስጥ ከሚኖራቸው አስተዋፅዖ አንፃር የመዘነ ይመሳል።
ከስብስብ ጥልቀት አኳያ ይህ ጥያቄ ይነሳበት እንጂ የክለቡ አጠቃላይ የዝውውር ምልከታ ለብዙዎች ትምህርት የሚሆን ነው። ከላይ በተጠቀሰው መሰረት ከፍ ያለ አበርክቶት ከነበራቸው ተጫዋቾች ውስጥ የአቡበከር ናስር እና የሚኪያስ መኮንንን ረጅም ኮንትራቶች ጨምሮ ታፈሰ ሰለሞን፣ ኃይሌ ገብረትንሳይ፣ አሥራት ቱንጆ እና ሬድዋን ናስርን የመሰሉ ተጫዋቾችን ውል ማራዘሙ ይበል የሚያሰኝ ነው። ይህ በመሆኑም አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ እንደ ፋሲል ከነማው አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ሁሉ አዲስ ቡድን የማደራጀት ጣጣ የማይጠብቃቸው የሊጉ አሰልጣኝ ያደርጋቸዋል። በዚህ ረገድ ሜዳ ላይ የምናየው ቡና ከአምናው ያለው ቀጣይነት ውህደታቸው በጊዜ ሂደት እንዲሻሻል ከሚጠብቁ አብዛኞቹ ተጋጣሚዎቹ የተሻለ ሊያደርገው ይችላል።
ቡና የተቀረውን የስብስቡን ክፍል በወጣት ተጫዋቾች ለመሸፈን በመወስን በርከት ያሉ ታዳጊዎችን ከወጣት ቡድኖቹ በመጥራት እንደሚጠቀም ይጠበቃል። ከምድብ በተሰናበተበት የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ለእነዚህ ወጣቶች የጨዋታ ጊዜ መስጠቱ ለውድድር ዓመቱ ሊጠቀምባቸው እንደሚችል ፍንጭ የሚሰጥ ነው።
ኢትዮጵያ ቡና የዝግጅት ጊዜውን ቀደም ብሎ በወርኃ ሐምሌ መጨረሻ ላይ በቢሾፍቱ ከተማ ነበር የጀመረው። በአፍሪካ መድረክ የነበረበት ጨዋታ ደግሞ ለዚህ መነሻ ነበር። ከሩዋንዳው ዩ አር ኤ ጋር የነበረበት የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጨዋታ በ5-2 የድምር ውጤት ሲደመደም ክለቡ በአዲስ አባባ ከተማ ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎ ማድረግ ችሎ ነበር። በውድድሩም በሦስት የምድብ ጨዋታዎች በአመዛኙ የወጣት ተጫዋቾቹን አቋም መመልከት ችሏል።
ከአጨዋወት ምርጫ አንፃር ኢትዮጵያ ቡና በያዘው መንገድ መቀጠሉ የሚያጠያይቅ አይሆንም። ከግብ ጠባቂው ጀምሮ ሁሉም ተሰላፊዎች ኳስን ከራሳቸው ግብ ክልል ጀምሮ በቅብብል ማውጣት በጋራም እስከተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ በጥቅሉ የሚገለፅ የቡድኑ አቀራረብ ነው። በተጋጣሚዎች ጥንካሬ እና ድክመትም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች ይህ መሰረታዊ የቡድኑ አካሄድ ሳይለወጥ ይታያል። በዚህ ረገድ እንደማንኛውም አንድ ፍልስፍና ተኮር ቡድን የተገማችነት ችግር ዋነኛው የዚህ ዓመት የኢትዮጵያ ቡና ፈተና ይሆናል።
ፈተናው ዘንድሮ ብቻ ሳይሆን 2013 ላይም መታየት የጀመረ ነው። ይህንን ከውጤት ንፃሬ አኳያ ስንመለከተው ቡድኑ በመጀመሪያው ዙር አሸንፏቸው ከነበሩ አምስት ቡድኖች ውስጥ በቀጣዩ ዙር ሁለቱ ሙሉ ውጤት ሲወስዱበት ሦስቱ ደግሞ ነጥብ አስጥለውታል። ከአጨዋወት አንፃር እንመልከት ካልንም በጥልቀት ተደራጅቶ በጥንቃቄ መጫወትን የመረጠው ሀዋሳ ከተማ በሁለቱም ዙር ሲያሸንፈው በራሱ ሜዳ ኳስ እንዳይጀምር መጫንን የመረጠው ባህር ዳር ከተማ ደግሞ ሁለቴም ነጥብ ተጋርቶታል።
በመሆኑ ኢትዮጵያ ቡና በፍልስፍና ደረጃ ተለውጦ ባይመጣም እነዚህን ፈተናዎቹን የሚወጣባቸው መፍትሄ የሆኑ ስልቶችን በጨዋታ ዕቅዱ ውስጥ ይዞ መቅረብ የግድ ይለዋል። በተጨማሪነትም የተጫዋቾቹን የግል ብቃት መጨመር የስልቶቹን ስኬት ከፍ በማድረግ ተጨማሪ ነጥቦችን ማግኘት በውጤት ተሻሽሎ ለመገኘት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። በተለይም ተደጋጋሚ የግለሰብ ስህተቶቹ ከኋላ ኳስ መስርቶ ለመውጣት የሚያደርገው ጥረት ላይ መስዕዋትነት ሲያሳልፈው ሲታይ መቆየቱ ዘንድሮም ስጋት ሆኖ እንዳይቀጥልበት ያሰጋል። ከኋላ ክፍሉ ጋር በተያያዘ ክለቡ ያስፈረማቸው ተጫዋቾች ከሞላ ጎደል የተከላካይ ክፍሉ ላይ ያተኮረ መሆኑ ይህንን ክፍተት ለመሸፈን ያለመ ቢሆንም በተጫዋቾች መካከል ከፍተኛ ተግባቦት ማዳበር በውድድር ዓመቱ ይጠበቃል።
ወደ ትኩረት ሳቢ ተጫዋቾች ስንመጣ 2013 ላይ እንደ አቡበከር ናስር የደመቀ የውድድር ዓመት ያሳለፈ ተጫዋች በኢትዮጵያ ቡና አይደለም በአጠቃላይ በሊጉ ውስጥ ማግኘት ይከብዳል። ክለቡ በዓመቱ ከመረብ ካገኛቸውን ግቦች የ66 በመቶ የአስቆጣሪነት አበርክቶት የነበረው አቡበከር ከሀገር ውጪ የመውጣት ምልክቶች ታይተውበት ቢያልፍም ዘንድሮም በቡናማዎቹ ቤት ውስጥ መቀጠሉ እርግጥ ሆኗል። ሆኖም ከስኬታማ ዓመት በኋላ የሚጠብቅ ፈተና እንደዘበት የሚታይ አይደለም። የተጫዋቹ ክህሎት ልቆ መገኘት የተጋጣሚ ቡድኖችን ትኩረት የሚስብ ነው። ይህ ተገማችነትም የሚያገኛቸውን ክፍተቶች ከዓምናው የጠበቡ እንዲሆኑ ማድረጉ አይቀርም። በዚህ በኩል በማጥቃት አጨዋወቱ በርካታ ተጫዋቾቹን እስከተጋጣሚ ሳጥን ድረስ ዘልቀው እንዲገቡ ሲያደርግ የሚታየው ቡና ተጫዋቾቹ የመጨረሻ ዕድሎችን የመጠቀም ንቃታቸውን ጨምረው እንዲመጡ ማድረግ ይኖርበታል። ይህም አቡበከርን ለማቆም በሚደረግ ጥረት ውስጥ የሚፈጠሩ ክፍተቶችን ለመጠቀም እና አጠቃላይ የቡድኑን የግብ መጠን ከመጨመርም ሆነ የአጥቂውን ከፍተኛ የግብ ድርሻ ኃላፊነት ከመካፈል አንፃር ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።
አምና በግራ መስመር አጥቂነት ውድድሩን የጀመረው አቡበከር እጅግ በተሻሻለው ቀርቦ ቅብብሎችን የመከወን ክህሎቱ እና በቡድን ተጫዋችነቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ ቢታይም ግብ አነፍናፊነቱ ፈንድቶ የወጣው ወደ መሀል አጥቂነት ሲመጣ ነበር። በቀሩት ጊዜያትም ከሦስቱ አጥቂዎች የመሀሉን ተሰላፊነት በቋሚነት ይዞ ቀጥሏል። ነገር ግን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ግራ መስመር አጥቂነት ተመልሶ ከማየታችን በላይ በዩ አር ኤው የኮንፌዴሬሽን ቀዳሚ ጨዋታም ከመስመር መነሳቱ አነጋጋሪ ሆኗል። ጉዳዩ ከተጋጣሚ አንፃር በተቃኘ ታክቲካዊ ስትራቴጂ መነሻነት ብቻ አለመደረጉን ተጫዋቹ ከዋልያዎቹ ጋር የነበረ በመሆኑ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ ለመመልከት አልተቻለም። አዲሱ የውድድር ዓመት ሲጀምር አቡበከርን በየትኛው ቦታ ላይ እንመለከታዎለን እንዴትስ ወደ ተሻለ ውጤታማነት ያመራል የሚለው ጉዳይ እጅግ ተጠባቂ ነው።
የሥዩም ተስፋዬ የልምድ እገዛ እንዳለ ሆኖ በመስመር እና መሀል ተከላካይነት ማገልገል የሚችለው ቴዎድሮስ በቀለ ከመከላከያ ጊዜው በኋላ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆኖ ለመትየት ዕድሉን ሲያገኝ ሁለት አማራጭ መፍጠሩም ለቡድኑ ጥሩ እገዛ ይኖረዋል። ከአዲስ ፈራሚዎች መካከል አንዱ የሆነው አቤል እንዳለም በደደቢት ያሳየውን ተስፋ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታው ከጥቂት ጨዋታዎች የዘለለ አስተዋፅዖ ሳያደርግበት በመቅረቱ በሌላ ትልቅ በድን ውስጥ መልሶ የመታየት ዕድልን ያገኛል።
አጥቂ መስመር ላይ ከአቃቂ ቃሊቲ ውሰት የተመለሰው በየነ ባንጃ ሳይጠቀስ አይታለፈም። በአፍሮ ፅዮን እና በ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ያሳየውን ብቃት በቡና ዳግም የማሳየት ዕድሉን አግኝቷል። የሀብታሙ እና አቤልን መውጣት እንዲሁም የሚኪያስ ተደጋጋሚ ጉዳቶች ስጋትን ተከትሎ በሁለቱ መስመሮች ሁነኛ ተጫዋች ለሚፈልገው ኢትዮጵያ ቡናም የበየነ አበርክቶት እጅግ አስፈላጊ ነው።
በርካታ ወጣት ፊቶችን እንደሚያሳየን የሚጠበቀው በቡና ቡድን ውስጥ ገዛኸኝ ደሳለኝ እና ሱራፌል ሰይፉ በዕድሜ እርከን ቡድኖች ካሳዩት ተስፋ አንፃር በተከላካይ እና አማካይ መስመር ላይ ጥሩ ግልጋሎት እንደሚሰጡ ይጠበቃል። ከዚህ ባለፈም ስብስቡ ላይ የእግርኳስ ህይወታቸውን ጅማሮ ለማስፈንጠር አጋጣሚው የተከፈተላቸው ወጣቶች በየቦታቸው የሚኖራቸው የእርስ በእርስ ፉክክር ለአሰልጣኙ አዳዲስ አማራጮችን ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ይጠበቃል።
ይህን መሳይ ተስፋዎች እና ስጋቶችን ይዞ ወደ ውድድር የሚገባው ኢትዮጵያ ቡና የፊታችን ማክሰኞ የመጀመሪያ ሳምንት ፍልሚያውን ከሲዳማ ቡና ጋር እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ቡና የ 2014 ስብስብ
ግብ ጠባቂዎች
አቤል ማሞ
በረከት አማረ
እስራኤል መስፍን
ተከላካዮች
አሥራት ቱንጆ
ኃይሌ ገብረትንሳይ
አበበ ጥላሁን
ወንድሜነህ ደረጀ
የአብቃል ፈረጃ
ስዩም ተስፋዬ
ቴዎድሮስ በቀለ
ነስረዲን ኃይሉ
ገዛኸኝ ደሳለኝ
አማካዮች
አማኑኤል ዮሐንስ
ሬድዋን ናስር
ዊሊያም ሰለሞን
ታፈሰ ሰለሞን
ሰራፌል ሰይፉ
አቤል እንዳለ
ሮቤል ተክለሚካኤል
ናትናኤል በርሄ
አጥቂዎች
አቡበከር ናስር
ሚኪያስ መኮንን
አላዛር ሽመልስ
እንዳለ ደባልቄ
በየነ ባንጃ
ማስታወሻ
በሌሎች ክለቦች ዳሰሳችን ላይ እንዳደረግነው ሁሉ የቡድኑን ዋና አሰልጣኝ ሀሳቦች ለማካተት ያደረግነው ጥረት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ሳይሳካ መቅረቱን እናሳውቃለን።