ላለፉት አራት ዓመታት የወንዶች ቡድኑን አፍርሶ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ ውድድር ለመመለስ እንዲያስችለው የኢኮሥኮ ቡድንን ለመረከብ መስማማቱ የሚታወስ ሲሆን በዛሬው ዕለት ይፋዊ የርክክብሥነ-ስርዓቱ ተከናውኗል።
ምሽት ላይ በራማዳ ሆቴል በተደረገው ሥነ-ስርዓት ላይ አቶ ኤፍሬም መኩርያ (የንግድ ባንክ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት) አቶ አሊ አህመድ (የንግድ ባንክ ስፖርት ማኅበር ፕሬዝዳንት) አቶ አመንቴ ዳዲ (የኢኮሥኮ ስፖርት ክለብ ፕሬዝዳንት)፤ አቶ ኢሳይያስ ጂራ (የኢ/እ/ፌ ፕሬዝዳንት) እንዲሁም የሁለቱ ስፖርት ክለብ የቦርድ አመራሮች ተገኝተዋል።
የንግድ ባንክ ስፖርት ማኀበር ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ዓሊ አህመድ በክፈቻ ንግግራቸው ቀደም ሲል ክለቡ ባስመዘገበው ውጤት ሳቢያ ተበትኖ እንዲቆይ ተወስኖ የቆየ ቢሆንም ስፖርት ቤተሰቡ እና ሠራተኞች የዘወትር ጥያቄን ምላሽ ለመስጠት በተደረገው ጥረት የዋናው ወጣት ቡድኖች በአዲስ አአሰራር እና አስተሳሰብ እንዲመለስ ውሳኔ መሰጠቱን ገልፀዋል። ” ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በተገኘ ሙያዊ ምክር እና ድጋፍ በከፍተኛ ሊግ የሚወዳደር ቡድን በማፈላለግ ውድድሩን ከከፍተኛ ሊግ መጀመር እንደሚቻል በተሰጠን ሀሳብ መሰረት የኢኮሥኮ ቡድንን ተረክበን የስም ለውጥ በማድረግ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወንዶች እግርኳስ ቡድን በሚል መጠርያ ለመሳተፍ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንገኛለን። ለዚህም ለኢኮሥኮ እና አስተዋፅኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቀርባለሁ።” ሲሉም አክለዋል።
ከማኅበሩ ፕሬዝዳንት ንግግር በመቀጠል የባንኩ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት አቶ ኤፍሬም መኩርያ ተቋማቸው ስፖርቱን ለረጅም ጊዜ ሲደግፍ የነበረ መሆኑን አውስተው በተለይ በሴቶች እግርኳስ ትልቁን ሚና የሚጫወት ቡድን መሆኑን ጠቁመዋል። ሆኖም በ2009 የወንዶች ቡድን ይዞ ለመቀጠል የሚያስችሉ ነባራዊ ሁኔታዎች በወቅቱ ስላልነበሩ ለማቋረጥ እና ፋታ አግኝቶ ለመመለስ ወስኖ የነበረ ቢሆንም ከውሳኔው በኋላ ከጠበቅነው በላይ ከስፖርት ቤተሰቡ ውሳኔውን ደግመው እንዲያጤኑ በርካታ አስተየየቶች እንደደረሳቸው ተናግረዋል። በዚህም ወደ ውድድር እንዲመለስ በርካታ ጥረቶች ሰደረጉ ቆይተው ቡድኑ ተመልሶ እንዲመጣ ውሳኔ መተላለፉን ገልፀዋል። ”ይህ ውሳኔ በእግርኳሱ አዎንታዊ ሚና ይጫወታል። በስፖርት መሰረተ ልማት ላይ ያለንን ተሳትፎ እንድናጠናክርም የሚያደርግ ነው። ለዚህ ሂደት መሳካት አስተዋፅኦ ያደረጉት የበላይ ጠባቂ የሆኑት እና የንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖን ማመስገን እፈልጋለሁ። የእግርኳስ ፌዴሬሽኑ እና ፕሬዝዳንቱ አቶ ኢሳይያስም በቅርበት በማገዝ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። ኢኮሥኮም አምኖብን ቡድኑን ለኛ ለማስተላለፍ በመወሰኑ ትልቅ ምስጋና አቀርባለሁ። አሁንም ቡድኑ የበለጠ ተወዳዳሪ ሆኖ ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲመለስ እንድታግዙን ጥሪ አደርጋለሁ።” ብለዋል።
ከአመራሮቹ ንግግር በኋላ ይፋዊ የፊርማ ስነስርዓት በአቶ ዓሊ እና አቶ አመንቴ አማካኝነት ከተከናወነ በኋላ የሰነድ ልውውጥ የተደረገ ሲሆን በመቀጠል ከዚህ ቀደም ከውሃ ስፖርት ቡድኑን ተረክቦ ሲወዳደር ቆይቶ አሁን ደግሞ ለንግድ ባንክ ያስተላለፈው ኢኮሥኮ ክለብ ፕሬዝዳንት አቶ አመንቴ ሀሳባቸውን አጋርተዋል። ” ቡድኑ በጠንካራ አሰልጣኝ እየተመራ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ ጥሩ ጎዳና ላይ ይገኝ ነበር። ሆኖም አሰልጣኛችን በሌላ ክለብ ተፈልጎ ከለቀቀ በኋላ ብዙም እድገት ማሳየት አልቻልንም። ይህ ቡድን ደግሞ ወደ ፕሪምየር ሊግ አድጎ ከፍ ባለ መድረክ እንዲወዳደር ያስፈልግ ነበር። ይህን ለማድረግ ብዙ አቅም የሚጠይቅ በመሆኑና ኢኮስኮ በሌሎች ሥራዎች ላይ የተጠመደ በመሆኑ ለሌላ ተቋም ማስተላለፍን እንደ አማራጭ ወሰስደን በምንንቀሳቀስበት ሰዓት ንግድ ባንክን አግኝተናል። ክለቡ ሲለየን የሚሰማን ስሜት ቦኖርም በጥሩ እጅ ላይ ስለወደቀ መልካም ምኞቴን መግለፅ እፈልጋለሁ።” ብለዋል።
በመጨረሻም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ባደረጉት ንግግር ኢኮሥኮ ቡድኑን ሜዳ ላይ ባለመበተኑ እና የፌደሬሽኑ ደንብ በሚፈቅደው መሰረት ቡድኑን ወደ ንግድ ባንክ በማዞሩ አመስግነው ክለቡ እንዳለ ሆኖ ንግድ ባንክ ደግሞ በተጨማሪነት ቢመጣ ግን ይበልጥ ምርጫቸው ይሆን እንደነበር አልሸሸጉም። “ጠንካራ ክለቦች በበዙ ቁጥር ጠንካራ የሊግ ውድድሮች እና ተፎካካሪ ብሔራዊ ቡድን ይኖራል ” ያሉት ፕሬዘደንቱ ከዚህ ቀደም በእግርኳሱ ትልቅ ስም የነበራቸው እና ፈርሰው የቀሩ ክለቦች እንደሚያስቆጯቸው በማንሳት ንግድ ባንክ ወደ ቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ቀርቦ እንደነበረው የሴቶቹ ቡድኑ ሁሉ በወንዶቹም ስኬትን ለማምጣት ከዚህ ቀደም ቡድኑን ሲበትን ያሳለፈውን ውሳኔ በመቀልበሱ በድጋሚ አመስግነዋል። አቶ ኢሳይያስ ንግድ ባንክ ወደ ወንዶች ቡድን ሲመለስ ከታች ከመጀመር ይልቅ የህጉን አግባብ ተከትሎ የመረጠውን መንገድ አንስተው በዋናው ሊግ ደረጃ የሚታየውን የክለቦች የፋይናንስ ችግር ደመወዝ ለመክፈል እስከመቸገር መድረሱን እና ንግድ ባንክ ግን ይህ ችግር እንደማይኖርበት እምነታቸውን አስቀምጠዋል። ከስምምነቱ ጋር በተያያዘም አሁን ላይ ውል ያላቸው የክለቡ ሰራተኞች መብት ሊከበር እንደሚገባው አሳስበዋል።