የክለቦች የውድድር ዘመን ቅድመ ዳሰሳ | ቅዱስ ጊዮርጊስ

የዘንድሮውን የውድድር ዘመን ዳሰሳችንን ቅዱስ ጊዮርጊስን በመመልከት እንፈፅማለን።


የሊጉን ዋንጫ በማንሳት ብዛት በረጅም ርቀት መሪ የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ለሦስት ዓመታት ያላየውን ይህንን ክብር መልሶ ለማግኘት አራተኛ የውድድር ዓመቱን ይጀምራል። ቁልፍ ዝውውሮችን ፈፅሞ ሆላንዳዊውን አሰልጣኝ ኤርነስት ሚደንድሮፕን በመቅጠር የገባበት የአምናው የ2013ቱ ቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግም ተመሳሳይ እንድምታ ነበረው። ነገር ግን ከአዲሱ አሰልጣኝ ጋር ከጅምሩ የተለያየው ክለቡ በምክትልነት ይዟቸው ከነበሩት ደቡብ አፍሪካዊው ማሒር ዴቪድስ ጋር ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ጊዜ ቢያሳልፍም በወጠነው መንገድ 15ኛውን ዋንጫ ለማንሳት በሚረዳ መልኩ ፉክክሩን መምራት አልቻለም። በመቀጠልም ዘጠኝ ጨዋታዎች ሲቀሩት እንግሊዛዊው ፍራንክ ናታልን በመቅጠር ወደ ዋንጫው ለመቅረብ የመጨረሻውን ጥረት ቢያደርግም ዓመቱን በ40 ነጥቦች ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ነበር የጨረሰው።

ለዘንድሮው የውድድር ዓመት ቅዱስ ጊዮርጊስ አምና ወደ ዋናው ቡድን የመለሳቸው አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታን በምክትል አሰልጣኝነት ይዞ ይቀጥላል። የቀድሞው የቡድኑ ኮከብ አዳነ ግርማን በቡድን መሪነት የሰየመው ክለቡ ዳግም ፊቱን ወደ ውጪ አሰልጣኝ በመመለስ የ2014 ምርጫው ያደረገው የ64 ዓመቱን ሰርቢያዊ ዋና አሰልጣኝ ዝላትኮ ክራምፖቲች ሆኗል። ከእርሳቸው ጋር በምክትልነት አሰልጣኝ ኒኮላ ኮሮሊጃን እንደሚያመጣ የተሰማ ቢሆንም ግለሰቡ በአዲስ አበባ ዋንጫ ጨዋታዎች የህክምና ረዳት ሆነው መታየታቸው አግራሞትን የጫረ ነበር። የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኙ ውብእሸት ደሰላኝ እና የቪዲዮ ተንታኙ አዲስ ወርቁ የቴክኒክ ክፍሉ አባላት ሆነው ይቀጥላሉ።


የዘንድሮው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ስብስብ ውስጥ ከዚህ ቀደም የተለመዱ ስሞችን አናገኝም። አምና በዲስፕሊን ምክንያት ታግደው የነበሩት አስቻለው ታመነ ፣ ጌታነህ ከበደ ፣ ሙሉዓለም መስፍን እና ጋዲሳ መብራቴን ጨምሮ ለዓለም ብርሀኑ ፣ አብዱልከሪም መሐመድ ፣ ምንተስኖት አዳነ ፣ ሳልዓዲን ሰዒድ ፣ አቤል እንዳለ እና የአብስራ ሙሉጌታ ከፈረሰኞቹ ጋር ተለያይተዋል።

ክለቡ እንደሁል ጊዜው ቀደም ብሎ ዝውውሮችን መፈፀም ሲጀምር በነበሩት ክፍተቶች ላይ ሁለት የውጪ ሀገር ዜግነት ያላቸውን ተጫዋቾችን ጨምሮ ስምንት ዝውውሮችን አጠናቋል። በዚህም ዩጋንዳዊውን ግብ ጠባቂ ቻርለስ ሉኩዋጎ እና ቶጎዋዊው አጥቂ እስማኤል ኦሮ-አጎሮ ፍሪምፖንግ ሜንሱን በመቀላቀል የቡድኑን የውጪ ተጫዋቾች ኮታ አሟልተዋል። ከሀገር ውስጥ በሦስቱ የመጫወቻ ቦታዎች ላይ ሁለት ሁለት ተጫዋቾች ሲፈርሙ ሱሌይማን ሀሚድ እና ምኞት ደበበ የተከላካይ ክፍሉን ጋቶች ፓኖም እና በረከት ወልዴ አማካይ ክፍሉን ቸርነት ጉግሳ እና ቡልቻ ሹራ ደግሞ የአጥቂ ክፍሉን ለማጠናከር ከፈረሰኞቹ ጎራ ተቀላቅለዋል። ክለቡ አዲሱን አሰልጣኝ ባስተዋወቀበት መርሐ ግብር ላይ ኃላፊዎቹ ተፈጥሯዊ የግራ መስመር ተከላካይ ቦታ ላይ ያልተጠበቀ ፈራሚ እንደሚያመጡ ጠቁመው የነበረ ቢሆንም በቦታው አዲስ ተጫዋች አልተካተተም። በተጨማሪም ለነባር የቡድኑ ስብስብ ውስጥ አማኑኤል ገብረሚካኤል
ናትናኤል ዘለቀ እና ሀይደር ሸረፋ ከክለቡ ጋር የሚያቆያቸው ሙሉ ተራዝሞላቸዋል።

 

የለቀቁ እና አዲስ የፈረሙ ተጫዋቾችን ስንመለከት ቅዱስ ጊዮርጊስ የስብስብ መልኩን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ የቀየረ ይመሳል። አራት ዓመታትን በተከታታይ የሊጉን ክብር ያነሳው የመጨረሻው ስኬታማ ቡድኑ ተጫዋቾች ወደ ጨዋታ ዘመናቸው ማብቂያ ሲቃረቡ እና ከክለቡ ስሊያዩ ቀጣዩን ጊዜ ያማከሉ ዝውውሮችን በተከታታይ ሲፈፅም እናስታውሳለን። ከዚህ አንፃር እንደ ሙሉዓለም መስፍን ፣ ለዓለም ብርሀኑ ፣ ሄኖክ አዱኛ ፣ አሜ መሀመድ ፣ አብዱልከሪም መሀመድ ዓይነት አሁን የሌሉ ተጫዋቾች መምጣት ለመጪው ጊዜ ቡድኑን የማዋቀር ምልክት የሰጠ ነበር። ነገር ግን ቀጣዮቹ ዓመታት ከውጤት አንፃር የታሰበውን ግብ የመቱ አልነበሩም። ዘንድሮ ቁልፍ ሚና የነበራቸው ተጫዋቾች ከስብስቡ ሲወጡ ከመታየቱ በተጨማሪ ከአዲሶቹ ውስጥ እንደቡልቻ ሹራ ፣ በረከት ወልዴ እና ቸርነት ጉግስ ዓይነቶቹ ከፊታቸው ረጅም የጨዋታ ዘመናት የሚጠብቃቸው ተጫዋቾች መሆናቸው ከግምት ሲግባ ክለቡ የስብስብ መልኩን የቀየረ የዝውውር ጊዜ ማሳለፉን ማሰብ ይቻላል። መተካካቱ ውጤታማ እንዲሆን ግን አዲስ መጪዎቹ ወደ ክለቡ እንዲመጡ ምክንያት የሆነው በከዚህ ቀደሙ የእግርኳስ ህይወታቸው ያሳዩትን አቋም መድገም እና ከዛም ከፍ ብሎ መታየት መቻላቸው ላይ ይወሰናል።

ጊዮርጊስ የስብስብ መልኩን የቀየሩ ዝውውሮችን ይፈፅም እንጂ አካሄዱ ከወትሮው የተለየ አልነበረም። ለመጪው የውድድር ዘመን የሚሆነውን አሰልጣኝ ከመወሰኑ በፊት አዲስ ተጫዋቾችን የሚያመጣበት ሂደት አሁንም ተደግሟል። የክለቡ ኃላፊዎች ጉዳዩን ከጊዜ እና በሀገር ውስጥ ያለው የተጫዋቾች ጥራት ውስን ነው ብለው ከማመናቸው ጋር ያገናኙታል። ከሌሎች ቀድሞ ገበያው ላይ አሉ የሚባሉትን ተጫዋቾች በእጅ ማስገባት አሰልጣኙ እስኪመጣ እና ምልመላ እስኪያደርግ ድረስ በሚወስደው ጊዜ ተጫዋቾቹን መነጠቅን እንደሚያስቀር ያስባሉ። ይህን አቋም ሊያስተካክል የሚችለውም ከአሰልጣኞች ጋር ከአንድ የውድድር ዓመት በላይ አብሮ በመቆየት በውድድር ውስጥ ተፈላጊ ተጫዋቾችን መልምሎ የቀጣዩን ዓመት ቡድን እንዲያዋቅሩ መፍቀድ ነው። ነገር ግን የክለቡ የአሰልጣኞች ለወጥ ድግግሞሽ አሁንም በተመሳሳይ አኳኋን ሄዶ ለተጫዋቾች ዝውውር ቅድሚያ እንዲሰጥ አድርጎታል።


ስድስቱን አዲስ ፈራሚዎች በሁለት ከፍለን መመልት እንችላለን። ሱለይማን ሀሚድ ፣ ምኞት ደበበ እና ጋቶች ፓኖም በልምድ ከፍ ያሉ ሆነው እናገኛቸዋለን። የመሀል ተከላካዩ የአስቻለው ታመነን ክፍተት ከመሸፈን አንፃር ጥሩ ምርጫ ይመስላል። ለቀጥተኛ አጨዋወት እና ለተሻጋሪ ኳሶች ምቹ የሆነው ሱለይማን ሀሚድ በተለይም በአዳማ ከተማ የነበረውን አቋም ማሳየት ከቻለ የቀኝ መስመር ተከላካይ ቦታውን ማስከበር ይችላል። ከግብፅ መልስ በወላይታ ድቻ የተመለከትነው ጋቶች ፓኖም በቦታው ካለው ልምድ አንፃር ቀዳሚ ተመራጭ የመሆን ዕድሉ የሰፋ ነው።

የቀድሞው የወላይታ ድቻ ተጫዋቾች የነበሩት በረከት ወልዴ እና ቸርነት ጉግሳ እንደ ተጫዋች ያደረጉት የክለብ ለውጥ ትልቅ እርምጃ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ያም ቢሆን በክህሎት ደረጃ የታየው ብቃታቸውን በወጥነት ማሳየት እንዲሁም በስብሱቡ ውስጥ ተመራጭ የመሆን ፈተና ይጠብቃቸዋል። በዚህ ረገድ በረከት በብቸኛ ተከላካይ አማካይነት በድቻ ያሳየው ብቃት የተሻለ ደረጃን የሚያሰጠው ሲሆን የመስመር አጥቂው ቸርነት ጉግሳ ግን ከሌላኛው አዲስ ፈራሚ ቡልቻ ሸራ ጋር የሚጋረው ነጥብ ይኖራል። ሁለቱ አጥቂዎች እስካሁን በመጡበት መንገድ ስንገመግማቸው ተፅዕኗቸው የወረዱባቸው ወቅቶች እንደነበሩ ማስታወስ የግድ ይላል። ከዛ ውጪ የብቃታቸውን ከፍታ ላይ ሲሆኑ ከመስመር ለሚነሱ ጥቃቶች የተመቸ ፍጥነት እና ጉልበት እንዳላቸው ዕሙን ነው።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በቢሾፍቱ በሚገኘው የክቡር ይደነቃቸው ተሰማ አካዳሚ ላይ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ሲከውን ቆይቷል። ከከተማ ተቀናቃኙ ኢትዮጵያ ቡና ጋር ካደረገው የወዳጅነት ጨዋታ ውጪም በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ውድድር ላይ ተሳትፎ አምስት ጨዋታዎችን ከውኗል። ሰርቢያዊው አሰልጣኝ በይፋ በተዋወቁበት ዕለት ለቅድመ ውድድር ጊዜ 42 ቀናት እንደሚያስፈልጋቸው አንስተው ነበር። ሆኖም ቡድናቸው እስከ አዲስ አበባ ዋንጫ ጨዋታዎች መዳረሻ ድረስ ብቻ ሲያዘጋጁ ቆይተው በመሀል የጤና ዕክል ምክንያት የሲቲ ካፑ ጨዋትዎች አልፈዋቸዋል። አሁን በመልካም ሁኔታ ላይ ሆነው ቡድኑ እየመሩ የሊጉን ውድድር መጀመር በመጠባባቅ ላይ ሲገኙ የቡድኑን የውድድር ቆይታ ለመግምግም የምክትል አሰልጣኞቻቸው እና የቪዲዮ ተንታኛቸው ሚና ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ የሊጉ ክብር ቢርቀውም ክለቡ ወደ አፍሪካ ውድድሮች ተመልሶ በአህጉራዊ መድረክ ያለውን ታሪክ ማሻሻል መቻል አሁንም ዋና አላማው መሆኑን ኃላፊዎቹ ይናገራሉ። ይህንን ለማድረግም ከአዲሱ አሰልጣኛቸው የሊጉን ቀዳሚ ሁለት ደራጃዎች ማሳካትን ይጠበቅባቸዋል። ከተጋጣሚዎች ይልቅ የራሳቸው ቡድን ላይ ማተኮርን የሚመርጡት አሰልጣኙ ማጥቃት ቀመስ የአጨዋወት ምርጫ እንዳላቸው በደፈናው ገልፀው ነበር። በአዲስ አበባ ዋንጫ ላይ ከተመለከትነው ቡድናቸው እና ከአዳዲሶቹ ዝውውሮች አንፃር ስንመለከተው ግን ጊዮርጊስ ወደ በፊቱ የሜዳ ላይ መልኩ ለመመለስ ያሰበ ይመስላል።


ባለፉት ሦስት የውድድር ዓመታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአሰልጣኝ ምርጫ እና የሜዳ ላይ ትግበራ አንፃር የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስዶ የመጫወት ፍላጎቱ የጠራ መልክ ሳይኖረው መሀል ላይ እንዲዋልል ሲያደርገው ይታይ ነበር። እጅግ ትዕግስት የሚጠይቀው የኳስ ምስረታ ሂደት ቡድኑ በፍጥነት ጎሎችን ለማግኘት ከሚያደርገው ጥረት ጋር እየተምታታ ከውጤትም ከጨዋታ ፍሰትም ውጪ ሲያደርገው ሲቀር ታዝበናል። አሁን ላይ ፈጣን ጥቃትን ይዞ ለመምጣት በስብስብ ደረጃም የተሻል ቁመና ላይ መገኘቱን ስናስተውል ግን 2014 ላይ ወደ ቀጥተኛነት ያመዘነ ጊዮርጊስን እንድንጠብቅ ያደርጋል።

በዚህ ረገድ ከላይ ከተነሱት ቸርነት እና ቡልቻ በተጨማሪ የአዲስ ግደይ ወደ ልምምድ መመለስ ለቡድኑ ተስፋ ነው። በሲዳማ የንግስና ጊዜው ተጫዋቹ ከግራ መስመር በመነሳት ይፈጥር የነበረው አስፈሪነት ሙሉ ጤና ላይ ከተገኘ በዚህ አጨዋወት ውስጥ ዳግም ሊያብብ እንደሚችል ይገመታል። ከታች ያደገው እና በወጣቶች ውድድር ላይ ግብ አስቆጣሪነቱን ያስመሰከረው እንዲሁም በአዲስ አበባ ዋንጫ ላይ ጎልቶ የወጣው ፀጋዬ መላኩም ተመሳሳይ ጠንካራ ጎን አለው።

ከነባር ተጫዋቾች ውስጥ በዋልያዎቹ ቀዳሚ ምርጫ ውስጥ እያየነው የምንገኘው አማኑኤል ገብረሚካኤል ዘንድሮ ከዓምናው የጊዮርጊስ ቆይታው የተሻለ ብቃት እንደሚያሳይ ይጠበቃል ። በክረምቱ ውድድር ጥሩ አቋም ያሳየው ሀይደር ሸረፋ እና ወጥ የሆነ አቋም በማስየት ብዙ መሻሻል የሚቀረው ከነዓን ማርክነህም በዘንድሮው ውድድር ዓመት የተሻለ ግልግሎት እንሰሚሰጡ ይገመታል። የስብስቡን ጥራት ከመጨመር እና እስካሁን በአስተማማኝ ደረጃ ያልተሸፈነውን የሮበርት ኦዶንካራን ቦታ ቻርለስ ሉኩዋጎ በአግባቡ እንደሚሸፍነውም ሰፊ ግምት አለ።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በድምሩ 28ኛ የሊግ ክብር እና የአፍሪካ መድረክ ተሳትፎን በማለም ወደ ውድድር ሲገባ በአንደኛው የጨዋታ ሳምንት የመጨረሻ ዕለት ሰበት ከተማን በመግጠም ጉዞውን ይጀምራል።

የቅዱስ ጊዮርጊስ የ2014 ስብስብ


ግብ ጠባቂዎች

ቻርለስ ሉኩዋጎ
ባህሩ ነጋሽ
ተመስገን ዮሐንስ

ተከላካዮች

ደስታ ደሙ
ምኞት ደበበ
ኤድዊን ፍሪምፖንግ
ሳላዲን በርጌቾ
ሱለይማን ሀሚድ
ሄኖክ አዱኛ
አማኑኤል ተርፉ

አማካዮች

ናትናኤል ዘለቀ
የአብስራ ተስፋዬ
ጋቶች ፓኖም
በረከት ወልዴ
ሀይደር ሸረፋ
ከነዓን ማርክነህ
ሀይደር ሸረፋ
አብርሀም ጌታቸው

አጥቂዎች

አቤል ያለው
ቸርነት ጉግሳ
አዲስ ግደይ
ቡልቻ ሹራ
አማኑኤል ገ/ሚካኤል
እስማኤል ኦሮ-አጎሮ
ዳግማዊ አርዓያ
ምስጋናው መላኩ
ፀጋዬ መላኩ