ሪፖርት | ድሬዳዋ በመጨረሻ ደቂቃ ግብ ድቻን ረትቷል

ያለግብ ሊጠናቀቅ ተቃርቦ በነበረው የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ የሄኖክ አየለ ጎል ድሬዳዋን ሦስት ነጥብ አስጨብጣለች።

ቀዳሚው አጋማሽ በጨዋታ እንቅስቃሴም ሆነ በሙከራዎች የተቀዛቀዘ ነበር። ኳስ መስርተው ለመውጣት የወጠኑት ድሬዳዋዎችም ሆኑ በቀጥተኛ ኳሶች ወደ ግብ ለመድረስ የጣሩት ድቻዎች በፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውስጥ የተገኙባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት ነበሩ።

ወላይታ ድቻዎች መጀመሪያ አካባቢ በቀኝ በኩል ወደተሰለፈው ምንይሉ ወንድሙ አድልተው ሰብረው ለመግባት ሲጥሩ ታይቷል። የድሬዳዋዎች ቅብብልም በአመዛኙ ወደ መስመር የሚያመራ እና ወደ ውስጥ የሚላክ ዓይነት ነበር። ሆኖም የተሻጋሪ ኳሶቻቸው ጥራት መውረድ ሁለቱንም አደጋ ከመፍጠር አግዷቸው ቆይቷል። ከቆሙ ኳሶች የተሻሉ የሚባሉ ቅፅበቶችን የፈጠሩት ድቻዎች ከእንድሪስ ሰዒድ በተሻማው እና በመስይ ጳውሎስ በተጨረፈ የቅጣት ምት ኳስ ለግብ የቀረቡበት አጋጣሚ ቢኖርም ፍሬው ጌታሁን በአስደናቂ ሁኔታ አምክኖባቸዋል።


ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር ሁለቱ ተጋጣሚዎች ሦስት ቅያሬዎችን አድርገው ተመልሰዋል። ያም ሆኖ ነገሮች ከቀደመው የተለዩ አልሆኑም። አንዳቸው የአንዳቸውን የማጥቃት እንቅስቃሴ እያቋረጡ ሲቀጥሉ ጨዋታው በጠሩ የግብ ዕድሎች ሊታጀብ አልቻለም።

ከቀደመው በተለየ ድሬዎች ጀርባቸው ላይ ያለው ክፍተት መስፋቱን ተከትሎ የወላይታ ድቻዎች ጥቃት ፍጥነት ጨምሮ ታይቷል። ቡድኑ ከቆሙ ኳሶችም ዕድል ለመፍጠር ሲሞክር ቢታይም ከባድ ሙከራ ለመሰንዘር ብዙ ደቂቃ ወስዶበታል። 68ኛው ደቂቃ ላይ ድቻዎች በቀኝ ከምንይሉ በተነስ ኳስ ጥራት ያለው የግብ ዕድል ቢፈጥሩም ኳሱን ሳጥን ውስጥ ተቀብሎ የሞከረው ስንታየሁ መንግሥቱ አምክኖታል።

ወደፊት ገፍቶ የመሄድ ፍላጎት በሁለቱም በኩል እየተንፀባረቀበት የቀጠለው ጨዋታ ቀጣይ ሙከራ የታየበት 86ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። የድቻው አጥቂ ስንታየሁ መሀል ለመሀል የተሰነጠቀለትን ኳስ ተከትሌ በመድረስ ቢጨርፍም ፍሬው ደርሶ አድኖበታል። ይህ በሆነ ሁለት ደቂቃ ውስጥ ግን ድሬዎች ወሳኝ ግብ አግኝተዋል።

 

ግብ ጠባቂው ጽዮን መርዕድ በረጅሙ የመጣን ኳስ ለማራቅ ያደረገው ጥረት ሳይሰምር በጋዲሳ መብራቴ ወደ ጎል ሲሞከር ያገኘው ተቀይሮ የገባው አጥቂ ሄኖክ አየለ አግኝቶ ወደ ግብነት ቀይሮታል። ግቧም ድሬዳዋን ባለድል አድርጋ ጨዋታው ተቋጭቷል።