ከምሽቱ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ሱፐር ስፖርት ተከታዮቹን አስተያየቶች ከአሰልጣኞች ተቀብሏል።
አስልጣኝ ዘማሪያም ወልደጊዮርጊስ – ድሬዳዋ ከተማ
ስለቡድናቸው የዕለቱ አቋም
የመጀመሪያ ጨዋታ አይመስልም ነበር ዛሬ። ሙሉ ቡድኑ ኮከብ ነው ማለት ይቻላል። ውድድር ውስጥ ያለ ቡድን ነበር የሚመሰው። እንጫናለን ግን አጨራረስ ላይ ችግር ስለነበር ያንን ለመቀየር ሞክረናል። ያም ተሳክቶልን አግብተን አሸንፈን ልንወጣ ችለናል። ዛሬ ተጫዋቾቼን በጣም ነው የማመሰግናቸው።
በእንየው በኩል ማጥቃት ስለመምረጣቸው
እንየው ባለፈውም ዓመት ፋሲል ቻምፒዮን ሲሆን እዛ ቦታ ላይ ትልቁን ድርሻ ተወጥቷል። መስመር ላይ በትክክል ነው የሚመላለሰው ፤ ስለዚህ በእሱ አቅም መጠቀም አለብን ብለን ነው ያሰብነው። ስለዚህ በተደጋጋሚ በዚያ በኩል እንሄድ ነበር። በተጨማሪ ደግሞ ኳሱን ለመቆጣጠርም እንሞክር ነበር ። ምክንያቱም እነሱ ረጅም አጥቂ ስላላቸው ረጅም ኳስ ነበር የሚጥሉት። ስለዚህ እኛ ኳሱን ተቆጣጥረን በቁጥር ብልጫ እየወሰድን ወደ ፊት ለመጠጋት እየሞከርን ነበር ፤ ብዙ አልተሳካልንም። መጨረሻ ላይ ግን የቀየርነው ቅያሪ ተሳክቶልን ልናስቆጥር ችለናል። ስለዚህ አጅማመራችን ጥሩ ነው ፤ ብዙ የሚሰሩ ሥራዎች እንዳሉም የሚያሳይ ነበር።
ስለሄኖክ አየለ ቅያሪ
ብዙ ኳስ ይሄድ እና የእነሱ አንድ ሦስተኛ ጋር ስንደርስ ነው የሚበላሸው። ስለዚህ እዛ ቦታ ላይ ለውጥ እንደሚያስፈልገን ተረድተን ነበር። ስለዚህ ለውጥ አድረግን አጋጣሚው ተሳክቶልን አስቆጠርን። ሄኖክ ከዚህ በፊትም የጭንቅላት ተጫዋች ነው። ብዙ የሚሮጥ ብዙ ጉልበተኛ ተጫዋች አይደለም ። ነገር ግን ዕድሎች ካገኘ መጨረስ እንደሚችል እናውቅ ነበር እና ስለዚህ ገባ እና ጨረሰልን።
ስለጋዲሳ መብራቴ
ጋዱሳ ብዙ አቅም የነበረው ልጅ ነው። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግን ባክኗል ፤ ያን የመሰለ አቅም ይዞ። ስለዚህ እኛ ጋዲሳ ላይ የምንሰራው ከፊታችን የአፍሪካ ዋንጫ ስላለ ብሔራዊ ቡድናችንን ሄዶ ማገልገል እንዲችል ነው። እንደመጀመሪያ ጨዋታ ጥሩ ነው። በቀጣይ ጨዋታዎች ላይም በደንብ ካገለገለ ክለቡን አይደለም ሀገሩን ማገልገል የሚያስችል አቅም አለው።
አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም – ወላይታ ድቻ
ስለቡድናቸው የዕለቱ አቋም
በመጀመሪያው እና በሁለተኛው አጋማሽ የተለያየ ፎርሜሽን ይዘን ነው የገባነው። መጀመሪያ ላይ በቡድናችን አለመረጋጋት ይታይ ነበር። በተለይ መሀል ላይ እና ወደፊት ስንሄድ የመቀናጀት ችግር ይታይብን ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ግን የፎርሜሽን ለውጥ አድርገን አጥቅተን ለመጫወት ምክረን ነበር። የቡድኑ ቅንጅት ገና ይቀረዋል። ከወልቂጤ ጨዋታ ካየነው ይሻላል። ማንሰራራት በማንችልበት ሰዓት ነው የተቆጠረብን። ግብ ጠባቂያችን በቀላሉ ማራቅ የሚችልበት አጋጣሚ ነበር። ያው በእግርኳስ የሚጠበቅ ነው። እንደመጀመሪያ ጨዋታ ግን ልጆቹ ያደረጉት ተጋድሎ ጥሩ ነው። በውጤት ደረጃ ባንረካም በእንቅስቃሴ የነበራቸው ታታሪነት በጣም ጥሩ ነበር። በዚህ አጋጣሚ ላመሰግናቸው እፈልጋለህ።
ስለተቆጠረባቸው ግብ
የገባብን ጎል በተጋጣሚያችን ጥንካሬ የተገኘ አልነበረም። በተከላካዩ እና በግብ ጠባቂው መሀል የነበረውን ክፍተት በቀላሉ መቆጣጠር ይቻል ነበር። ወደ ጎን ቢሆን ያወጣው ቢያንስ አጥቂው በተረጋጋ ሁኔታ ኳሱን የሚያገኝበት መንገድ አልነበረም። ዞሮ ዞሮ የተከላካይ እና የግብ ጠባቂ አለመናበብ ዋጋ አስከፍሎናል። በከፍተኛ ጥረት የተገኘ አይደለም ፤ እንደስጦታ ነው ማለት ይቻላል። እነዚህን ነገሮች በልምምዶች አስተካክለን መጥተን ጠንካራ ቡድን ይዘን ለመቅረብ ጥረት እናደርጋለን።
ስለስንታየሁ መንግሥቱ
ስንታየሁ የጎል ፍላጎት ሳላለው እንጂ ፊትነሱ ትክክል አልነበረም። አራት እና አምስት ልምምዶች አልፈውታል። በወልቂጤው ጨዋታ በ 20 ደቂቃ ተጎድቶ ነው የወጣው። ለቡድኑ ፍቅር ስላለው እንጂ ሙሉ ልምምድ ሰርቷል ማለት አይቻልም። ነገር ግን የዚህን ያህል ጥረት ማድረጉም ቀላል የሚባል አይደለም። እዛ የተሳተች ኳስ ናት እዚህ መጥታ የገባችው። ሙሉ ጤነኛ ሲሆን ከኪህ በተሻለ እንደሚያገለግለን ባለሙሉ ተስፋ ነኝ።