ትናንት በድምቀት በጀመረው የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የሚሳተፉት ክለቦች በቀጣይ ጨዋታዎቻቸው የውጭ ተጫዋቾቻቸውን አገልግሎት ያገኙ ይሆን ?
በዘንድሮው የዝውውር ገበያ የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾችን የሊጉ ክለቦች በስፋት ማስፈረማቸው ይታወቃል። አስቀድሞ የመኖርያ እና የሥራ ፍቃድ የተጠናቀቀለት የሀዋሳ ከተማው ላውረንስ ላርቴ ብቻ ተሰልፎ የተመለከትን ሲሆን በዛው በሀዋሳ የሚገኘው መሐመድ ሙንታሪ እንዲሁም በጅማ በኩል ሚላ ሮጀር፤ በምሽቱ ጨዋታ ደግሞ በድሬዳዋ በኩል አዲስ ፈራሚዎቹ ማማዱ ሲዲቤ፥ አውዱ ናፊዩ እና አብዱለጢፍ መሐመድን ሳይጠቀሙ መቅረታቸውን ታዝበናል።
ከዚህ በቀጣይ ጨዋታዎቻቸውን የሚያደርጉት ሀድያ ሆሳዕና፤ ሰበታ ከተማ፤ አርባምንጭ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ከሥራ ፍቃድ ጋር በተያያዘ የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾቻቸውን ያለመጠቀም ግዴታ ውስጥ እንደገቡ ሠምተናል። ዛሬ የበዓል ቀን በመሆን ፈፃሚ አካሉ የኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽን እና አሰሪና ሠራተኘ ጉዳይ ቢሮ ሥራ ዝግ መሆናቸው ጉዳያቸውን በፍጥነት ለመጨረስ የሚቸገሩ ይመስላል። ምን አልባት ከነገ ጀምሮ ባሉት ሁለት ቀናት የሚጠናቀቅ ከሆነ የአንዳንድ ቡድኖች ተጫዋቾች በአንደኛው ሳምንት ጨዋታዎች የሚደርሱ ሲሆን ካልሆነ ግን በሁለተኛው ሳምንት ጨዋታ ግልጋሎታቸውን ሊያገኙ ይችላሉ።
ዛሬ ጨዋታ ከሚያደርጉት መካከል መከላከያ እና ወልቂጤን በዚህ ጉዳይ ዙርያ ጠይቀን በሰጡን ምላሽ ተጫዋቾቻቸው ፈቃዳቸውን እንዳገኙ የገለፁልን ሲሆን የአዳማ ግብ ጠባቂም የፈቃድ ቀነ ገደቡ ባለመጠናቀቁ መሰለፍ እንደሚችል ሰምተናል። ነገ የሚጫወተው ባህር ዳር ደግሞ ኦሴ ማውሊ መሰለፍ እንደሚችል የተገለፀ ሲሆን የኒኪማን ነገ በመጨረስ ለማድረስ ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ታውቋል። ረቡዕ የሚጫወተው ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾቹ ለጨዋታው ብቁ እንደሆነሉትም ሰምተናል።