ሪፖርት | የቆመ ኳስ ግቦች አዳማ እና ወልቂጤን አቻ አድርገዋል

የአዳማ ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ ጨዋታ 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ተመጣጣኝ ፉክክር ያስመለከተን የመጀመሪያው አጋማሽ በግብ የታጀበ ባይሆንም ጥሩ ፍልሚያ ታይቶበታል። ተጋጣሚዎቹ አንዳቸው የሌላኛቸውን የጨዋታ ሂደት ለመረዳት በሚመስል አኳኋን በመንቀሳቀስ ቀዳሚዎቹን ደቂቃዎች አሳልፈዋል። ወልቂጤም ሆነ አዳማ ኳስ የመቆጣጠር አዝማሚያን ያሳዩ እንጂ አዳማዎች ቀጥተኝነትን የቀላቀለ አካሄድ ነበራቸው። ዳዋ ሆቴሳን ያማከሉ ኳሶች አልፎ አልፎ ወደ ፊት ሲጥሉ ከጨዋታ ውጪ እየሆኑ እንዲሁም የሲልቪያን ግቦሆ ጊዜ አጠባበቅ ጥሩ መሆን ከሙከራዎች አግዷቸዋል።

አዳማ ከተማዎች ከቆሙ ኳሶችም የተሻሉ አደጋ ፈጣሪ ዕድሎችን ለማግኘት ይጥሩ ነበር። በዚህ ሂደትም 11ኛው ደቂቃ ላይ የማዕዘን ምት ባሻሙበት ጊዜ እስራኤል እሸቱ ሚሊዮን ሰለሞን ላይ በሰራው ጥፋት ምክንያት የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። በዳዋ ሆቴሳ የተመታውን ፍፀም ቅጣት ምት ግን ሲልቪያ ግቦሆ አድኖታል። ከአስር ደቂቃዎች በኋላም ወደ ግራ ያደላው የደስታ ዮሃንስ ቅጣት ምት ሲነሳ ሚሊዮን ሰለሞን ነፃ ሆኖ የመግጨት ዕድሉ የነበረው ቢሆንም ሙከራው ከኢላማ ውጪ ሆኗል።

ከተጋጣሚያቸው የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ትዕግስት የታየባቸው ወልቂጤዎች ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ሲደርሱ በእስራኤል እሸቱ እና አህመድ ሁሴን በሚመሩት ሁለቱ መስመሮች በኩል የመግባት አማራጭ ሲወስዱ ታይቷል። የወልቂጤ ቅብብሎች ወደ አደገኛ ዕድልነት ለመቀየር በተቃረቡበት 22ኛው ደቂቃ ላይ ከአብዱልከሪም ወርቁ እና በኃይሉ ተሻገር ተቀምሮ ተስፋዬ ነጋሽ ወደ ውስጥ ሰብሮ እንዲገባ አስችሎት የነበረ ቢሆንም ሴኮባ ካማራ ፈጥኖ በመውጣት አምክኖታል።


የአጋማሹ ሌላ መልክ ግጭቶች የበረከቱበት መሆኑም ነበር። ከሁለቱም በኩል ተደጋጋሚ ጉዳቶች ሲከሰቱ እና የአርቢትሩ ፊሽካ ደጋግሞ ሲሰማ አስተውለናል። ከሁሉም በከፋው አጋስጣሚ ግን 31ኛው ደቂቃ ላይ ዮናስ በርታ የማዕዘን ምት በመሻማት ሂደት ላይ ከቶማስ ስምረቱ ጋር በመጋጨቱ ባስተናገደው ካባድ ጉዳት በውሀብ አደም ተቀይሮ በቀጥታ ወደ ሆስፒታል ማምራቱ ነበር።

ከዕረፍት መልስ ሁለት ቅያሪዎችን ያደረጉት አዳማዎች የቆሙ እና ረዘም ያሉ ኳሶች ጥረታቸው ቀጥሎ ታይቷል። 52ኛው ደቂቃ ላይ ከቶማስ ስምረቱ የተነሳው ረጅም ኳስ በግራ በኩል አምልጦ በገባው አሜ መሀመድ ወደ ግብ ዕድልነት ሊቀየር ተቃርቦ ግቦሆ ነበር ያቋረጠው። የቆሙ ኳሶች ውጤታማነት ቀድሞ የታየው ግን በወልቂጤ በኩል ሆኗል። 59ኛው ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ ወደ ግብ የላከው የቅጣት ምት ኳስ ተቀይሮ በገባው ዮሴፍ ዮሀንስ ተጨርፎ ከመረብ አርፏል።

ከግቡ በኋላ ወልቂጤዎች ይበልጥ የመልሶ ማጥቃት ባህሪ እየታየባቸው አዳማዎችም ለቀጥተኛ ኳኮች እያደሉ ሲቀጥሉ ሙከራዎች ባይታዩም ፍልሚያው ለዓይን የማይሰለች ሆኗል። በዚህ አኳኋን የቀጠለው ጨዋታ 78ኛው ደቂቃ ላይ ጎል ሲያገኝ ምንጩ አሁንም የቆመ ኳስ ሆናል። ተቀይሮ የገባው የአዳማው አማካይ ኤልያስ ማሞ ያሻማው የማዕዘን ምት በሚሊዮን ሰለሞን ተገጭቶ ለአዳማ የአቻነት ግብ ሆኗል።

ደቂቃዎች ወደ መጨረሻው ሲቃረቡ የሚያስቆጭ የግብ ዕድል ተፈጥሮ ባንመለከትም ሁለቱም በቶሎ ወደ ግብ ለመድረስ ጥረታቸው አላቋረጡም። በእነዚሁ ደቂቃዎች ባልተጠበቀ ሁኔታ ተከታታይ ቢጫ ካርዶች የተመለከተው ረመዳን የሱፍ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። ጨዋታው ሊያበቃ ሰከንዶች ሲቀሩ አዳማዎች እጅግ የሚቆጩበትን ዕድል አምክነውል። ግብ ጠባቂው ግቦሆ አሳጥሮ የለጋውን ኳስ እየነዳ ከሳጥን ውስጥ የገባው አብዲሳ ጀማል የሞከረው ኳስ ከመረብ አረፈ ተብሎ ሲጠበቅ ወደ ውጪ ወጥቷል። ጨዋታውም ከዚህ ሙከራ በኋላ በ 1-1 ውጤት ተቋጭቷል።