የአሰልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 1-1 ወልቂጤ ከተማ

የሁለተኛ ቀን የመጀመርያ ጨዋታ የአቻ ውጤት በኋላ አሰልጣኞች ለሱፐር ስፖርት ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ- አዳማ ከተማ

በጨዋታው ስለተመዘገበው ውጤት

መጨረሻ ላይ ያገኘነውን ዕድል ካየሁ ሦስት ነጥብ አግኝተን ነበር። እንደመጀመርያ ጨዋታ መጥፎ አይደለም። ግን ጎሉ ከገባብን በኋላ የተወሰነ ሰዓት ወደ ጨዋታ ለመግባት ተቸግረን ነበር። መጨረሻ ላይ ሙሉ ለሙሉ የምንፈልገውን ውጤት አገኘን ባልልም አንድ ነጥብ አግኝተናል ጥሩ ነው።

ዳዋ ስላመከነው ፍፁም ቅጣት ምት

ዳዋ መንፈሰ ጠንካራ ተጫዋች ነው። ግን ማንኛውም ተጫዋች ፍፁም ቅጣት ምት አለመጠቀም ተፈጥሯዊ ነው። ለተወሰነ ደቂቃ ማሰቡ አይቀርም። እርሱ ብቻ አይደለም ቡድናችንም ወደ ጨዋታ እንቅስቃሴ ለመግባት ተቸግሮ ነበር። ይህ ተፈጥሯዊ ነው። ዕድሎች አግኝተናል አልተጠቀምንበትም። በእርግጥ በጣም ብዙ የምናሻሽላቸው በተለይ በእኛ ሜዳ የምናበላሻቸው ኳሶች ልናርም ይገባል።

በመጨረሻው ደቂቃ ስለመከነው የጎል ዕድል

በሁለተኛው አርባ አምስት በተለየ አቀራረብ ለመቅረብ ሞክረናል ተጨማሪ አጥቂዎችን በማስገባት ይህ ደግሞ ማጥቃት መፈለጋችንን ነው የሚያመለክተው። ግን የኳሱ ሂደት ትክክል አልነበረም። ግልፅ የጎል ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግረን ነበር። መጨረሻ ላይ አግኝተን ነበር። እግርኳስ እንደዚህ ነው። በዛ ሰዓት ጎል ብናገባ ለእኛ ደስታ ለእነርሱ ሀዘን ነው በእግርኳስ እንዲህ ያለ ነገር ይኖራል።

አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው – ወልቂጤ ከተማ

ስለጨዋታው

ያው እንደተመለከታቹሁት እንደመጀመርያ ጨዋታ መጥፎ ነገር የለውም። ወደ ጎል ቶሎ ቶሎ መድረስ ችለን ነበር። እንዳያችሁት ጨዋታው ጉሽሚያ በዝቶብት ነበር። ይሄ ደግሞ እኛ ጋር መሐል ሜዳ ያሉ ልጆች ባለ ክህሎት ናቸው። ኳስ ተቆጣጥረው እንዳይጫወቱ ብዙ ዱላ በዝቶባቸው ነበር። በዚህ ምክንያት እንዳሰብነው አልሆነም።

በጨዋታው ስለበዛው ጉሽሚያ

ከኋላ የነበረው የወልቂጤ መከላከል አምና እኔ ከመጣው በኃላ እጠቀምበት የነበረ እና ራሳቸውን አንድ አድርገው አደራጅተው የሚከላከሉ ስለነበሩ ዛሬም እንደታየው ቀይረን ያስገባነው ልጅ ምንንም መተማመን እንደሌለብህ ነው። ሃያ አምስት ሰው የምታሰለጥነው ለዚህ ስለሆነ ብዙ ነገር የለውም። ጉዳቱ የከፋ እንደሆነ እስካሁን አላወኩም ሄጄ ነው የማየው።

ስለውጤቱ

እንደመጀመርያ ጨዋታ አሸንፈን መውጣት ነበረብን። የራሳችን ትንሽ የጥንቃቄ ጉድለት ዋጋ አስከፍሎናል። ቡድናችን እንደታየው ከሆነ መጫወት የሚችል ነው። ስህተታችንን አርመን ለቀጣይ ጨዋታ እንመጣለን።

ያጋሩ