ሪፖርት | ጦሩ የፕሪምየር ሊግ ምልሰቱን በድል አድምቋል

ከከፍተኛ ሊጉ አብረው የመጡት ቡድኖች እርስ በእርስ ሲገናኙ በውጤቱ መከላከያ አርባምንጭን 1-0 መርታት ችሏል።

የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በመከላከያዎች ከፍተኛ የማጥቃት ጫና የጀመሩ ነበሩ። ጦሩ ረዘም ያሉ ኳሶችን ወደ አርባምንጭ ሳጥን ቶሎ ቶሎ በማድረስ የሳምሶን አሰፋ እና የተከላካይ ክፍሉን ሥራ አብዝቷል። በተለይም 5ኛው ደቂቃ ላይ ግሩም ሀጎስ በተከላካዮች መሀል ያሾለከለትን ኳስ ይዞ የፊት አጥቂው አማኑኤል ኦኩቱ ግብ አፋፍ ደርሶ የመታው ኳስ መረብ ላይ ከማረፍ የዳነው በሳምሶን ጥረት ነበር።

በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ወደ መረጋጋት የመጡት አርባምንጮች እንደተጋጣሚያቸው ሁሉ ኳሶችን በቀጥታ ወደ ፊት በመላክ የበላይነቱን ተረክበዋል። በተለይም 15ኛው ደቂቃ ላይ ከኋላ በረጅሙ የተላከውን ኳስ ፀጋዬ አበራ ሲጨርፍለት የግራ መስመር አጥቂው አሸናፊ ኤልያስ በግንባሩ አብርዶ ወደ ውስጥ ይዞ ቢገባም ከጠበበ አንግል ያደረገው ሙከራ ወደ ውጪ ወጥቷል።

ሌላኛው የአጋማሹ አደገኛ ሙከርም በአርባምንጭ በኩል የታየ ነበር። በዚህም 31ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዳንኤል ከግራ ወደ ሳጥን ውስጥ የላከውን ረጅም ኳስ በደረቱ ያበረደው ፀጋዬ አበራ ያደረግው የቅርብ ርቀት ሙከራ ወደላይ ተነስቷል። በቀሪዎቹ ደቂቃዎች አርባምንጬች በተሻለ ሁኔታ በተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ ሲታዩ የመከላከያዎች የመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶችም አስፈሪ ነበሩ።

ፍጥነት እና ዕልህን ቀላቅሎ የቀጠለው የቡድኖቹ ጨዋታ ለተመልካች ሳቢ የሆነ ፍልሚያን እያሳየ ቀጥሏል። የእንቅስቃሴያቸው ፍጥነትም ሀምሳ ሀምሳ ኳሶች ላይ አደገኛ ግንኙነቶችን ይፈጥር ነበር። በዚህም በጨዋታው ጉዳት የገጠመው ሱራፌል ዳንኤል ገና 35ኛው ደቂቃ ላይ በበላይ ገዛኸኝ ተቀይሮ ወጥቷል ፤ ጨዋታውም ኃይል እየቀላቀለ ወደ አጋማሹ ፍፃሜ አምርቷል። ሊጠናቀቅ ሲቃረብም የአርባምንጮቹ የመሀል ተከላካዮች ማርቲን ኦኮሮ እና አንድነት አዳነ በተከታታይ የቢጫ ካርድ ሰለባ ሆነዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር የቀደመ የፉክክር መንፈሱን ይዞ ቀጥሏል። በቶሎ ወደግብ የመድረስ ፍላጎት በሁለቱም በኩል ሲታይ መከላከያዎች የተሻለ ከሜዳቸው የውጣት ብልጫ ነበራቸው። ሆኖም አደገኛዎቹ አጋጣሚዎች በአዞዎቹ በኩል ነበር የታዩት። 54ኛው ደቂቃ ላይ አራት ለሁለት በሆነ የቁጥር ብልጫ በመልሶ ማጥቃት ጦሩ ሳጥን ውስጥ ቢደርሱም የአሸናፊ ተገኝ ከቀኝ የተሻማ ኳስ ተዛንፏል። ወዲያው በተገኘ የማዕዘን ምትም ፀጋዬ አበራ ግልፅ የግብ ዕድል አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። መከላከያዎች ግን ቀጥሎ ያገኙትን ዕድል አላመከኑትም።


58ኛው ደቂቃ ላይ ጦሩ በግራ መስመር በከፈተው ጥቃት በመከላከሉም በማጥቃትም በኩል በታታሪነት ሲጫወት የነበረው ግሩም ሀጎስ ከመስመር ያሻማውን ኳስ ጋናዊው ኢማኑኤል ኤኩቱ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሯል። ከግቡ በኋላ አርባምንጮች በቆሙ ካሶች እና ተሻጋሪ ኳሶች አቻ ለመሆን ጥረዋል። 77ኛው ደቂቃ ላይ በላይ ገዛኸኝ ወደ ሳጥን የተላከውን ኳስ ከጦሩ ተካላካዮች ጋር ታግሎ በአየር ላይ በመምታት ያደረገው እና ወደ ላይ የተነሳበት ሙከራም ቡድኑ ለግብ ከቀረበባቸው አጋጣሚዎች አንዱ ነበር።

መከላከያዎችም ሌላ ግብ የማከል ጥረታቸው አልቆመም። ወደ ማብቂያው ላይም ይበልጥ የማጥቃት ጥረታቸው አይሏል። 81ኛው ደቂቃ ላይ ሰመረ ሀፍተይ ያሻማው ኳስ በአርባምንጩ ተከላካይ አንድነት የግንባር ኳስ ግብ ሊሆን ተቃርቦ ነበር። ቢኒያም በላይ ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ከቅጣት ምት ያደረገው ሙከራም በግቡ ቋሚ ተጨርፎ ወጥቷል። ሆኖም አዝናኝ ፉክክር ያሳየን ጨዋታ ሌላ ግብ ሳይስተናግድበት በመከላከያ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ያጋሩ