የአሰልጣኞች አስተያየት | አርባምንጭ ከተማ 0-1 መከላከያ

ሁለቱ ከታችኛው ሊግ ያደጉትን ቡድኖች በምሽት ያገናኘው ጨዋታ በመከላከያ አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኃላ አሰልጣኞቹ ተከታዩን አስተያየት ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳሕሌ – መከላከያ

የዛሬው ውጤት ስለሚኖረው ትርጉም

በመጀመርያ አርባምንጭን በዚህ ዓይነት ሁኔታ የመቶ ሜትር ውድድር ነው የምትለው (… ሳቅ) እንደዚህ አይነት ከባድ ጨዋታ ነው። አርባምንጭ ቀላል ቡድን አይመስለኝም፤ ጠንካራ ቡድን ነው። ሁለታችን ከታች የመጣን ስንሆን እንደ ዋንጫ ጨዋታ ነው ያየነው። እኛ ትንሽ መረጋጋት በሚባለው በተወሰነ መልኩ የተሻልን ነበርን። የመጀመርያ አስራ አምስት ደቂቃ ሁለታችንም በፈጣን ሩጫ ወደፊት የመሄድ ነገር ለእኛ ይህ ጥሩ ነው ለእነርሱም። የዛሬው ጨዋታ ከሠላሳ እርምጃ አንድ እንደማለት ነው። ማራቶን ነው፤ መሀል ላይ ማቋረጥ ይመጣል። ስለዚህ ለአርባ ምንጭም አንድ ጨዋታ ምንም ማለት አይደለም። ለእኛ ለተነሳሽነት ጥሩ ነው። ግን የሚያዘናጋን እና ከሌላው ቡድን እንበልጣለን የምንለው ነገር አይደለም።

ስላልተጠቀሙበት የጎል ዕድሎች

የአርባምንጭ አጨዋወት በጣም አስቸጋሪ ነበር። እኛ ከሠራነው አሰራር ጋር በጣም በአካል ብቃቱ ከፍ ያሉ ናቸው። በጣም ሸርታቴ ያደርጋሉ። በጣም ይዘላሉ። ሀምሳ ሀምሳ ኳስ ላይ በጣም ጎበዞች ናቸው። እኛ ደግሞ ሁለት ወጣቶች አሰልፈን ስለነበር ይህንን መቋቋም መቻላቸው በራሱ ለእኛ ትልቅ ነገር ነው። ልምድ ካላቸው ተጫዋቾች የምንፈልገውን ነገር አግኝተናል። ልምድ የሌላቸው ተጫዋቾች ልምድ እስኪያገኙ ድረስ ጊዜ መስጠት አለብን። ዞሮ ዞሮ ሦስት ነጥብ አግኝተናል።

አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ – አርባምንጭ ከተማ

ስለ ሊጉ የመጀመርያ ጨዋታ

ሲጀመር የመጀመርያው አስር ደቂቃ እነርሱ ብልጫ ወስደው ዕድል መፍጠር ችለው ነበር። እኛም ከዛ በኃላ የጎል አጋጣሚዎችን ከዕረፍት በኃላ እና በፊት መፍጠር ችለናል። በተወሰነ መልኩ አጨዋወታችን የመመሳሰል ባህሪ አለው። እነርሱ ቶሎ ከሜዳቸው ለመውጣት ባህሪ ነበራቸው። እኛም በዛ መልኩ ቶሎ ቶሎ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ለመድረስ ጥረት ስናደርግ ነበር። እነርሱ ተሳክቶላቸው አሸንፈዋል እንኳን ደስ አላቹሁ ማለት እፈልጋለው።

መስመሩን ለመጠቀም ስለማሰባቸው

ሁለቱንም መስመሮች ለመጠቀብ አስበናል። በተለይ ቶሎ ቶሎ ወደ ፊት በመሄድ የነርሱ ተከላካይ ላይ ጫና ለመፍጠር አቅደን ነበር። ተሻጋሪ ኳሶችንም ለመጠቀም አስበን ነበር። በቂ ባይሆንም የተወሰነ አጋጣሚ ፈጥረን ነበር። ከዚህ በኃላ ተረጋግተን የምንሠራቸው ሥራዎች አሉ። ያልተመጠኑ ኳሶች እንለቅ ነበር። በቀጣይ ከጨዋታ ጨዋታ እያሻሻልን እንሄዳለን።

ስሜታዊ ስለመሆናቸው

ሁለት ዓመት ሠላሳ ስድስት ጨዋታ አልተሸነፍንም። ዛሬ ነው የተሸነፍነው። ያን ነገር ለማስቀጠል ነበር አንዱ ዓላማችን። የጨዋታ ቁጥር ከፍ ለማድረግ ከነበረን ፍላጎት አንፃር ስሜቶች አሉ። ግን ፈጣሪ የፈቀደው ነው የሚሆነው። በቀጣይ ሠርተን አሻሽለን እንመጣለን።