ቅድመ ዳሰሳ | ባህር ዳር ከተማ ከ አዲስ አበባ ከተማ

በነገው ቀዳሚ መርሐ-ግብር ዙሪያ እነዚህን ነጥቦች አንስተናል።

ነገ ሦስተኛ ቀኑን በሚይዘው የ2014 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ባህር ዳር እና አዲስ አበባ ይገናኛሉ። ሦስተኛ የውድድር ዓመቱን የሚጀምረው ባህር ዳር በአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ስር በኳስ ቁጥጥር ላይ መሰረት ያደረገ አቀራረብ እንደሚኖረው ይጠበቃል። በወጣቱ አሰልጣኝ ኢስማኤል አቡበከር የሚመሩት አዲስ አበባዎች በጨዋታው ፈጣን የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን በመጠቀም ለተጋጣሚያቸው ምላሽ እንደሚሰጡ ይገመታል።

የአዲስ አበባዎቹ ኤሊያስ አህመድ ፣ ቴዎድሮስ ሀሞ እና ፋይሰል ሙዘሚል ጉዳት ላይ በመሆናቸው የነገው ጨዋታ ያልፋቸዋል። በቡድኑ ውስጥ ያሉት የውጪ ዜጎችም የሥራ ፍቃድ ያላገኙ በመሆኑ ከነገው ጨዋታ ውጪ ናቸው። በተመሳሳይ የባህር ዳሩ አማካይ አብዱልከሪም ኒኪማ የሥራ ፍቃድ ጉዳይ ነገ ማለዳ ዝግጁ እንደሚሆን የሰማን ሲሆን ቡድኑ የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ ጉዳት ከገጠመው ዓሊ ሱለይማን ውጪ የሚያጣው ተጫዋች አይኖርም።

አዲስ አበባ ከተማ 2009 ላይ ከሊጉ ሲወርድ ባህር ዳር ከተማ በቀጣዩ ዓመት ሊጉን በመቀላቀሉ ሁለቱ ክለቦች ነገ በፕሪምየር ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ይገናኛሉ።

ጨዋታውን ፌደራል ዳኛ ባህሩ ተካ በመሀል ዳኝነት ይመሩታል።

የሁለቱን ክለቦች የክረምት ወቅት ዝግጅት እና በቀጣይ የሚኖራቸውን መልክ በሰፊው ያወሳንባቸውን ፅሁፎች ከዚህ በታች ያገኛሉ።

ባህር ዳር ከተማ

https://soccerethiopia.net/football/7153211

አዲስ አበባ ከተማ

https://soccerethiopia.net/football/7145311