በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ተሳታፊ የሆነውን ኢኮሥኮን ወደ ራሱ ያዞረው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሠልጣኝ ማግኘቱን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ የታወቀ ስም የነበረው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአራት ዓመታት በፊት የወንዶቹን ክለብ አፍርሶ ቆይቶ ነበር። አሁን ግን በአዲስ መልክ የወንዶቹን ክለብ ለመመለስ እንቅስቃሴ በመጀመር ባሳለፍነው ሳምንት በይፋ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የሚሳተፈውን ኢኮሥኮ ክለብ ተረክቧል።
ከርክክቡ ጎን ለጎን የአሠልጣኝ ቅጥር ለመፈፀም እንቅስቃሴ ላይ የነበረው ክለቡም አዲስ አሠልጣኝ አግኝቷል። በዚህም ክለቡን ለማሰልጠን 24 አሠልጣኞች ቢመዘገቡም 12 አሠልጣኞች ለኢንተርቪው ተመርጠው ዋናው አሠልጣኝ ተሹሟል። በዚህም ደጋረገ ይግዛው ባንክን ለአንድ ዓመት ለማሰልጠን ተመርጠዋል።
ከ2012 ጀምሮ ወልቂጤን ሲያሰለጥኑ የቆዩት እና ባለፈው የውድድር ዓመት አጋማሽ ከቡድኑ ጋር የተለያዩት አሰልጣኝ ደግአረገ ከዚህ ቀደም የአማራ ውሃ ሥራዎች (አውስኮድ) እና አሁን ወደ ንግድ ባንክ የዞረው ኢኮሥኮን ማሰልጠናቸው ይታወሳል።