የአሰልጣኞች አስተያየት | ባህር ዳር ከተማ 3-0 አዲስ አበባ ከተማ

የመጀመርያ ሳምንት የሦስተኛ ቀን ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ አዲስ አበባ ከተማን ካሸነፈ በኃላ አሰልጣኞቹ ተከታዮን አስተያየት ለሱፐር ስፖርት አጋርተዋል።

አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ – ባህር ዳር ከተማ

ለኦሲ ማውሊ የተሰጠው ሚና

እንደሚታወቀው ኤሲ ማውሊ አጨራረሱ በጣም ጥሩ ነው። ወደ መሐል እየገባ ጉልበት ከሚያባክን እዛው አካባቢ ቆይቶ የምናገኛቸውን ዕድሎች ቢጠቀም ቡድናችን የበለጠ ተጠቃሚ ይሆናል። በተጨማሪም ከጉዳት ስለመጣ ነጠል ብሎ ከአማካይ የሚመጡ ኳሶችን እንዲጠቀም ነበር የነገርነው፤ ያንን አድርጓል።

ስለ መጀመርያ ማጥቂያ መንገድ

የመጀመርያ ማጥቂያ መንገድ መስመሮች ነበሩ። ያ ብቻ ሳይሆን ከኃላ የሚነሱ የመስመር ተጫዋቾች ተጨማሪ ሀይል ሆነው አማካይ እንዲያግዙ ያደረግነው በግርማ በኩል ጥሩ ነበር። በመሳይ በኩል ግን እንደፈለኩት አላገኘሁም። ያው ከልምድ የሚመጣ ስለሆነ በቀጣይ ጥሩ ነገር ያደርጋል።

ስለ መከኑ ዕድሎች

አጥቂዎቺ የተገኙትን ዕድሎች በአግባቡ አልተጠቀሙም። ያገኘነውን የኃላ ክፍተት ሙሉ ለሙሉ ተጠቅመንበታል ብዬ አላስብም። በአጨራረስ ማነስ ያመከናቸው ዕድሎች አሉ። የመጀመርያ ጨዋታ እንደመሆኑ የገኘናቸውን ዕድሎች አለመጠቀማችንን እንደ ጉዳት አላየውም።

አሰልጣኝ እስማኤል አቡበከር – አዲስ አበባ ከተማ

የጨዋታው እንቅስቃሴ

በሁለታችንም በኩል ክፍት የነበረበት ጨዋታ ነበር። እነርሱ በኳስ ቁጥጥሩ የተሻሉ ነበሩ ትንሽም የብስለት ነገር ታያለህ በእኛ በኩል ደግሞ በመጀመርያው አርባ አምስት ተከላክለን ያገኘናቸውን ኳሶች ሄደን ጥቃት ለመፈፀም ነበር አልተሳካም። በሁለተኛው አርባ አምስት የተወሰነ የትኩረት ችግር በተከላካይ በኩል ነበር። በቀጣይ አስተካክለን እንመጣለን።

የተከላካዮች ክፍተት

እንዲህ ያለህ ነገር ይከሰታል። ያው ልጁ በጣም ፈጣን ነው። ጥሩም ችሎታ አለው። ዞሮ የሚመታቸው ኳሶች እራሱ በጣም የተሻሉ መሆናቸው እና ያንን መቆጣጠር ትንሽ ከብዶን ታይቷል። በዚህ ነገር ላይ ሰርተን እንመጣለን።

ስለሚቆራረጡ ኳሶች

አብዛኛውን ልጆቹን ስታያቸው ልጆች ናቸው። ያ ደግሞ ልምድ በጣም ይጠይቃል። የመጀመርያ ጨዋታ እንደመሆኑ መጠን በሊጉም የመጀመርያ ተሳትፎ ስለሆነ የልምድ ችግር ተስተውሏል። እየለመዱ ሲመጡ ጥሩ ነገር ያሳያሉ።