ሪፖርት | ሲዳማ እና ቡና ነጥብ ተጋርተዋል

ሲዳማ ቡና እና ኢትዮጵያ ቡናን ያገናኘው የምሽቱ ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ቡና እንደወትሮው ኳስ መስርቶ ለመውጣት ጥረት ማድረግ ሲዳማ ቡና ደግሞ ለተጋጣሚው አጨዋወት ፊት ላይ ጫና በመፍጠር ክፍተት አሳጥቶ ምላሽ መስጠት የመጀመሪያው አጋማሽ መልክ ነበር። በዚህ ሂደት የተሻለ የተሳካላቸው ሲዳማዎች ሆነዋል። ከጅምሩ በቀኝ መስመር አጥቂው ብሩክ ሙሉጌታ ፈጣን ጥቃት መሰንዘር የጀመሩት ሲዳማዎች 10ኛው ደቂቃ ላይ ከባድ ሙከራ አድርገዋል። ቡናዎች መሀል ላይ ካባከኑት ቅብብል በቴዎድሮስ ታፈሰ አስጀማሪነት በቶሎ ሳጥን ውስጥ ደረሰው በሀብታሙ ገዛኸኝ ያደረጉት ሙከራ በአቤል ማሞ ጥረት ድኗል። ፍሬው ሰለሞንም ከርቀት ሙከራ አድርጎ አቤል ይዞበትል።

ሲዳማዎች ከወገብ በላይ በነበራቸው ታታሪነት የቡና የኳስ ፍሰት ቀዳዳዎችን እንዳያገኝ የሚያደርጉት ጥረት ጨዋታውን ለቡና አክብዶታል። የቡናማዎቹ ቅብብሎች መሀል ሜዳውን የሚያልፉበት አጋጣሚም ጥቂት ሆኖ ታይቷል። ሲዳማ በዚህ ረገድ ጥሩ ሆኖ ቢታይም የማጥቃት ሽግግሩ ሳጥን ውስጥ ሲደርስ የተጫዋቾች ውሳኔ መዛነፍ ከግብ አርቆታል። ከቆሙ ኳሶችም ጭምር አጋጣሚዎችን ይፈጥር የነበረው ቡድን 28ኛው ደቂቅ ላይ በቴዎድሮስ ታፈሰ ቅጣት ምት መነሻነት ሰለሞን ሀብቴ በግንባር ከሞከረው ኳስ ሌላ አደገኛ ዕድል ፈጥሮ ነበር። ከደቂቃዎች በኋላ ብሩክ ሙሉጌታ በቀኝ ሰብሮ ገብቶ ወደ ውስጥ ያሳለፈውም ኳስ ሥራ በዝቶበት በነበረው አቤል ተይዟል።


የኢትዮጵያ ቡና ቅብብሎች ነፍስ እየዘሩ በመጡባቸው የመጨረሻ 15 ደቂቃዎች ቡድኑ ወደ ግራ አድልቶ ሳጥን ውስጥ የደረሰባቸው አጋጣሚዎች ታይተዋል። 37ኛው ደቂቃ ላይ አስራት ቱንጆ በግል ጥረቱ በግራ በኩል ሰብሮ ሳጥን ውስጥ የገባበት አጋጣሚ ወደ ሙከራነት ሳይቀየር ሲቀር 39ኛው ደቂቃ ላይ ታፈሰ ሰለሞን ከግራ ወደ ውስጥ የላከውን ኳስ አቤል እንዳለ አብርዶለት እንዳለ ደባልቄ ያደረገው ሙከራ ወደ ውጪ ወጥቷል። ሲዳማዎች ከሙከራ ርቀው ቢቆዩም 41ኛው ደቂቃ ላይ ሰለሞን ሀብቴ ያሻማውን ኳስ ብሩክ ሙሉጌታ ያለጫና መግጨት ቢችልም ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል።


መሀል ተከላካዩ ጊትጋት ጉት 52ኛው ደቂቃ ላይ የሰነጠቀው ኳስ በአማኑእል እንዳለ ተሻምቶ በግቡ ብረት እስኪጨረፍ ድረስ የቡድኖቹ የሁለተኛ አጋማሽ ጅማሮ ቀዝቀዝ ብሎ ንነበር የጀመረው። ከሁለት ደቂቃ በኋላም ቴዎድሮስ ታፈሰ ከርቀት ያደረገው አደገኛ ሙከራ በአቤል ማሞ ሲድን የጨዋታው መንፈስ ነቃ ብሏል። በቡና በኩል በተሰጠው ምላሽም 57ኛው ደቂቃ ላይ ታፈሰ ሰለሞን የተክለማሪይም ሻንቆን መውጣት ተመልቶ ከመሀል ሜዳ ወደ ግብ የላከው ኳስ ግብ ጠባቂው መልሶ ቦታው ላይ በመገኘቱ ድኗል።

ከዕረፍት መልስ ዊሊያሞንን በሮቤል ተክለሚካኤል የቀየሩት ቡናዎች የአማካይ ክፍላቸው የማጥቃት አካሄድ ለማስተካከል ያደረጉት ጥረት እምብዛም ውጤት አላመጣም። የቡድኑ ቅብብሎች እንደመጀመሪያው ሁሉ ከመሀል ማለፍ ሲከብዳቸው ታይቷል። ከሳጥን ውጪ ሙከራዎችን ማድረግን እንደ አማራጭ ወስደውም በታፈሰ እና ሮቤል አማካይነት ያደረጓቸው ጥረቶች ከጥሩ ሙከራነት መዝለል አልቻሉም። ሲዳማዎችም ቢሆኑ ተጋጣሚየቸውን መቆጣጠሩ ላይ ጥሩ ቢዘልቁም በግብ ፊት የነበራቸው አተገባበር ደካማ ነበር። ለዚህም ይመስላል አዱስ አጥቂያቸው ኬኒያዊው ፍራንሲስ ካሀታን 65ኛው ደቂቃ ላይ በሀብታሙ ቦታ ለውጠው አስገብተዋል።


ጨዋታው ወደ ፍፃሜው እየቀረበ ሲሄድ ሲዳማዎች በጥሩ ሁኔታ ከኋላ በመነሳት ማጥቃትን ያስጀምሩ የነበሩባቸው ኳሶች ጥራት እየወረደ ግለሰባዊ ስህተቶችም እየጨመሩ ሲሄዱ ታይቷል። በረንፃሩ ቡናዎች ቅብቦቻቸው ወደ ሳጥኑ እየቀረቡላቸው ሄደዋል። 85ኛው ደቂቃ ላይ በድጋሚ ከሳጥን ውጪ የተደረገው የኃይሌ ገብረትንሳይ ሙከራ ኢላማውን ቢጠብቅም በተክለማሪያም ድኗል። ሲዳማዎች ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ከቡናዎች በተቀማ ኳስ በቁጥር በልጠው ሳጥኑ መግቢያ ላይ የሰረሱበት የሚያስቆጭ አጋጣሚ በፍሬው ሰለሞን ወደ ግብ ቢላክም አቤልን የሚፈትን አልሆነም። ቀላል የማይባል ፍልሚያን ያስተናገደው ጨዋትም በዚህ መልኩ ሲጠናቀቅ 2014 ያለግብ የተጠናቀቀ የመጀመሪያው የሊጉ ጨዋታ ሆኗል።