የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ቡና 0-0 ሲዳማ ቡና

በመጀመሪያ የጨዋታ ሳምንት ሦስተኛ ቀን ውሎ ኢትዮጵያ ቡና ከሲዳማ ቡና ያለግብ ከተለያዩበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።

ካሣዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

ቡድኑን በጠበቀው መንገድ ስለማግኘቱ

“ከጨዋታው በፊት ጫናዎቹ እንደሚኖሩ ገምተን ነበር፤ ያንን ጫና ለመቋቋም በምናደርገው ሒደት ውስጥ ስህተቶች ነበሩ። ሜዳው ትንሽ አስቸጋሪ ነበር። በዚህ ላይ ኳሶቹን ተቆጣጥሮ ለማስቀጠል ትንሽ አስቸጋሪ ነበር። ነገርግን በተወሰነ መልኩ ከጨዋታ እንወጣ ነበር። ይህም ቢሆን እዛ ውስጥ ቆይተን ስህተቶቻችን ለማየት ነበር ስንሞክር የነበረው። በአጠቃላይ ግን ጥሩ ነበር።”

ቡድኑ ይሰራቸው ስለነበሩ ስህተቶች የማጥቃት መነሻ ስለመሆናቸው

“አንዳንዶቹ ኳሱ የሚፈለገው ሰው ጋር ከደረሰ በኃላ በሚመጣው ጫና የሚሰሩ ስህተቶች ናቸው ፤ አንዳንዶቹ ግን የሚፈለገው ሰው ጋር ኳሶቹ ሳይደርሱ መሀል ላይ የሚቋረጡ ናቸው እነሱን ግን ያው የምናርማቸው ይሆናል።”

ስለቀጣዩ የሸገር ደርቢ ጨዋታ

“እኔ እንግዲህ ሁሌም እንደምለው ለሁሉም ጨዋታ ተጋጣሚን የምንቋቋምበትን መንገድ ነው ይዘን የምንገባው። እርግጥ ነው ከጊዮርጊስ ጋር ያለን ጨዋታ በደጋፊው ዘንድ የተለየ ግምት የሚሰጠው ነው። ያ ስሜት እንደተጠበቀ ሆነ እኛ እንዴት ነው ልንቋቋም የምንችለው በሚለው በሌሎች ጨዋታዎች ይዘን የምንመጣውን ነገር ይዘን እንቀርባለን ግን ቢሆንም ስሜቱን እንረዳዋለን።”

ስለግብጠባቂያቸው መጋለጥ

“አንዳንዶቹ ነገሮች የሚሆኑት እኛ ለመጫወት ባለን ሂደት ውስጥ የኳስ ባለቤት ሆነህ ተጋጣሚን አትይዝም፤ እራስህን ነፃ ለማድረግ ነው። እነዛ ኳሶች ሲነጠቁ ተጋጣሚ ነፃ ሰው አለው። ስለዚህ እነዛን ነፃ ሰዎች ወዲያውኑ እየተጠቀሙ ነው አንዳንድ ሙከራዎች ያደረጉት። የመጀመሪያው እርምት በዛ መንገድ ተጋጣሚ ነፃ ሰዎችን ሊጠቀም ስለሚችል ኳሶች እንዳይበላሹ ማድረግ ነው። ከተበላሸ ደግሞ እንዳይጠቀም ማድረግ ነው። በዚያ መልኩ ነው ለተጫዋቾቻችን የመጀመሪያ የቤት ሥራ የሰጠነው።

ገብረመድኃን ኃይሌ – ሲዳማ ቡና

የተገኙ አጋጣሚዎችን መጠቀም ስላለመቻላቸው

“ብዙ አጋጣሚዎችን ፈጥረን ነበር፤ ነገርግን መጠቀም አልቻልንም። ይህም ዋጋ አስከፍሎናል። በመጀመሪያው አጋማሽ ማለቅ የሚገባው ጨዋታ ነበር። ነገርግን አጋጣሚዎቹን ለመጠቀም የነበረን ዝግጁነት ትክክል አልነበረም። ወደፊት እንደመጫወታችን እና እንደፈጠርናቸው እድሎች ማስቆጠር ነበረብን። በሁለተኛው አጋማሽ የመጨረሻ 15 ደቂቃዎች ጥሩ የሚባል አልነበረም፤ እኛ ላይ ጫናዎች ነበሩ። ከዚያ አንፃር ስታየው እኛ ላይ ጎል አለመግባቱም ጥሩ ነገር ነው። ከዛ አንፃር የሚያከሰፋ አልነበረም።”

በሁለተኛው አጋማሽ ስለነበራቸው እንቅስቃሴ

“የመጀመሪያውን አጋማሽ ማስቀጠል አልቻልንም ፤ በመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያዎቹ 25 ደቂቃዎች ጥሩ ነበርን። ከዛ የተወሰኑ መዘበራረቆች ነበሩ። ያንንም ለማስተካከል በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን እና የመጨረሻ ኳሶችን በመስጠት የተሻሉ ተጫዋቾችን ለማስገባት ሞክረናል። ነገርግን ከነበረው ውጥረት አንፃር ውጤቱን መቀየር ሳንችል ቀርተናል። ነገርግን የመጀመሪያ ጨዋታ እንደመሆኑ አለመሸነፍ በራሱ ጥሩ ነገር ነው።

ስለ ዳዊት ተፈራ

“ዳዊት ተፈራ ጉዳት ላይ ስለከረመ የተወሰነ የጨዋታ ፊትነሱን እንዲያገኝ ቀይረን አስገብተነዋል። ቅያሬው ታክቲካዊ ሳይሆን ዳዊት ከሁለት ወር ዝግጅት ከ10 ቀን ያልዘለለ ነው ልምምድ የሠራው። በመሆኑም ይበልጥ የጨዋታ ዝግጁነቱን እንዲያገኝ አልመን ነው ቀይረን ያስገባነው።”

ያጋሩ