ቅድመ ዳሰሳ | ፋሲል ከነማ ከ ሀዲያ ሆሳዕና

የነገውን ቀዳሚ ጨዋታ የተመለከቱ ነጥቦችን እነሆ !

ፋሲል ከነማ የሊጉን ዋንጫ ካነሳ በኋላ በተጠባቂነት የተሞላውን የድል ማግስት የውድድር ዓመት ነገ ይጀምራል። በጥቂት ዝውውሮች ራሱን ያጠናከረው ፋሲል ዘንድሮም ከአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ጋር ወደ ውድድር ይመጣል። ቡድኑ አብሮ ያቆየው ስብስቡ ዘንድሮ በምን ዓይነት የጥንካሬ ደረጃ ወደ ጨዋታ እንደሚመለስ ተጠባቂ ሆኗል። ከዚህ ፍፁም በተለየ ሁኔታ ስር ነቀል ለውጥ ያደረገው ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ እንደ አዲስ ተዋቅሮ ከአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ጋር ብቅ ብሏል። የአምናው አይረሴ የመከላከል ቁመናው ዘንድሮ በምን አይነት ሁኔታ መልኩን ይቀይራል ? የቡድኑስ የአጨዋወት እንዴት ይቃኛል ? ለሚለው ጥያቄ የነገው ጨዋታ ምላሽ እንደሚኖረው ይጠበቃል።

የነገው ጨዋታ ሜዳ ላይ ከሚደረገው ፍልሚያ ባሻገር ትኩረት ሳቢው ጉዳይ የዐምናው ቻምፒዮን ፋሲል ከነማ አዲሱ ዋንጫን በይፋ የሚያነሳበት መሆኑ ነው። ባለፈው ዐመት ለመጀመርያ ጊዜ በልዩ ሁኔታ ዑሰራው ዋንጫ ባለመድረሱ ጊዜያዊ ዋንጫ ተቀብሎ የነበረው ቡድኑ የነገው ጨዋታ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ባለ መሶብ ቅርፁን ዋንጫ ከፍ የሚያደርግ ይሆናል።

በጨዋታው የፋሲል ከነማው ይሁን እንዳሻው ጉዳት ላይ በመሆኑ ተሳትፎ የማይኖረው ሲሆን የኦኪኪ አፎላቢ መድረስም እርግጥ አልሆነም። በሌላ በኩል የሀዲያ ሆሳዕናው ግብ ጠባቂ ሶሆሆ ሜንሳህ የሥራ ፍቃድ ባለመጨረሱ ከስብስቡ ውጪ ሲሆን ጉዳት ያለበት ሄኖክ አርፊጮ መድረስም አጠራጣሪ ሆኗል።

የነገው የቡድኖቹ ጨዋታ በሊግ ታሪካቸው ሦስተኛ ግንኙነት ይሆናል። አምና ፋሲል የመጀመሪያውን ዙር ጨዋታ 1-0 ሲያሸንፍ ቀጣዩ በ1-1 ውጤት ተለያይተው ነበር።

ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት የመምራቱ ኃላፊነት ለፌደራል ዳኛ ዳንኤል ግርማይ ተሰጥቷል።

የሁለቱን ክለቦች የክረምት ወቅት ዝግጅት እና በቀጣይ የሚኖራቸውን መልክ በሰፊው ያወሳንባቸውን ፅሁፎች ከዚህ በታች ያገኛሉ።

ፋሲል ከነማ

https://soccerethiopia.net/football/7139611

ሀዲያ ሆሳዕና

https://soccerethiopia.net/football/7147911