ቅድመ ዳሰሳ | ሰበታ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

የመጀመሪያው ሳምንት ማሳረጊያ ጨዋታን እንዲህ ቃኝተነዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ዳግም ወደ ሊግ ድል አድራጊነት ለመመለስ የሚጀምረው የውድድር ዓመት ከነባር ተጫዋቾቹ ጋር የተለያየበት እና ስብስቡ ላይ ማሻሻያዎች ያደረገበት ሆኗል። ሰርቢያዊ ዋና አሰልጣኝ ዝላትኮ ክራምፖቲች ደግሞ ቀጣይ ኃላፊነቱን የተረከቡ አሰልጣኝ ሆነዋል። ከዝግጅት ጊዜ ውድድሮች አንፃር ቡድኑ ወደ ቀደመ ቀጥተኛ አጨዋወቱ ለመለስ ምልክት ሰጥቷል። የነገው ጨዋታም ይህንን ሀሳብ እንደሚያጠራ ይጠበቃል። አምስተኛ ደረጃን ይዞ የጨረሰው ሰበታ ከተማ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል ደረጃ በአዲስ ስብስብ ውድድሩን ይጀምራል። አምና በወላይታ ድቻ ጥሩ የግማሽ ዓመት ቆይታ የነበራቸው አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ የነሳው ስብስባቸውን የዘው ከበድ ባለ ጨዋታ ውድድርቻውን ይጀምራሉ።

ናሚቢያዊው የሰበታ ከተማ አጥቂ ጁኒያስ ናንጄቦ በሥራ ፍቃድ ምክንያት ሌላኛው አጥቂ መሀመድ አበራ ፣ ዘላለም ኢሳያስ እና አክሊሉ ዋለልኝ ደግሞ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ ሆነዋል። የዘካሪያስ ፍቅሬ እና ክሪዚስቶም ንታንቢ አገግሞ ብቁ መሆንም አጠራጥሯል። ከዚህ በተጨማሪ አምና በከፍተኛ ሊጉ ቅጣት ያለበት በኃይሉ ግርማም አይሰለፍም። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ሳላሀዲን በርጌቾ ፣ ጋቶች ፓኖም እና ናትናኤል ዘለቀ ጉዳት ላይ የሚገኙ ሲሆን የቡድኑ የውጪ ዜጋ ፈራሚዎች የሥራ ፍቃድ ጉዳይ ዝግጁ በመሆኑ የመጫወት ዕድል ይኖራቸዋል።

ቡድኖቹ በአጠቃላይ በሊጉ ስምንት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ አራቱን በማሸነፍ የበላይነት አለው። በሦስቱ አቻ ሲለያዩ በአንዱ ሰበታ አሸንፏል። በጨዋታዎቹ 15 ጎሎች ሲቆጠሩ አስሩን ጊዮርጊስ አምስቱን ሰበታ አስቆጥረዋል።

ጨዋታውን ፌደራል ዳኛ ማኔሄ ወልደፃዲቅ በመሀል ዳኝነት ይመሩታል።

የሁለቱን ክለቦች የክረምት ወቅት ዝግጅት እና በቀጣይ የሚኖራቸውን መልክ በሰፊው ያወሳንባቸውን ፅሁፎች ከዚህ በታች ያገኛሉ።

ሰበታ ከተማ

https://soccerethiopia.net/football/7162111

ቅዱስ ጊዮርጊስ

https://soccerethiopia.net/football/7179611