የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሚያስተዳድራቸው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ እና አንደኛ ሊግ ውድድሮች የሚጀመሩበት ቀን ይፋ ሲሆን የዝውውር ጊዜውም ተራዝሟል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በስሩ ከሚያወዳድራቸው ሊጎች መካከል የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ እና አንደኛ ሊግ ውድድሮች ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡ በሦስት ምድቦች ተከፍሎ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚያድጉ ክለቦችን ለመለየት የሚካሄደው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ2014 የውድድር ዘመን ኅዳር 20 – 2014 እንጂመር ፌዴሬሽኑ ያሳወቀ ሲሆን ከሀምሳ በላይ ክለቦች አቅፎ በስድስት ምድቦች ተከፍሎ የሚካሄደው የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ውድድር ከኅዳር 18 ጀምሮ በተመረጡ ከተሞች እንዲደረግ መወሰኑን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡
ከሁለቱ ውድድሮች ጋር በተያያዘ ቀደም ብሎ ከነሐሴ 10 እስከ ጥቅምት 10 – 2014 ድረስ የሁለቱ ሊጎች የዝውውር ወቅት መሆኑን ፌዴሬሽኑ ይፋ አድርጎ የነበረ ቢሆንም ፌድሬሽኑ የክለቦችን የይራዘምልን ተደጋጋሚ ጥያቄን ተከትሎ እስከያዝነው ወር መጨረሻ ጥቅምት 30 ድረስ ዝውውር ማድረግ እንዲችሉ መወሰኑንም ጭምር ሰምተናል፡፡ በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የአንደኛ እና የሁለተኛ ዲቪዚዮን የዝውውር ቀናትም ስለ መራዘማቸው ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።